Items filtered by date: Monday, 16 April 2018

እግር ጥሎዎት ወደ አንድ ሆቴል ለመዝናናት ገቡ እንበል። ታዲያ ያረፉበት ሆቴል ያጋጠመዎ መስተንግዶ አላረካ ይልዎታል። በተለይ የተመገቡት ምግብ እርስዎ እንደፈለጉት አልሆነለዎ ትም። አጠቃላይ የሚፈልጉትን መረጃዎች በሚፈልጉት መንገድ አላገኙም። የሆቴሉ ትልቅነት እና ዘመናዊነት ግን ካገኙት አገልግሎት ጋር የተቃረነ ይሆንብዎታል። ታዲያ ይህን ጉዳይ ሆቴሉን ከሚያስተዳድረው ሰው ጋር ተገናኝተው ለመነጋገር ፈልገው የሚመለከተው ሰው ጋር ይገናኛሉ።
አሁንም አይበለውና አገልግሎቱን ከሰጠዎት ባለሙያና ዋናው አስተዳዳሪ ያገኙት ምላሽ ከበሉት ምግብ በላይ ጨጓራ የሚያደብን፤ ከሙያ ሥነ ምግባር ጋር የሚጋጭ ሥርዓት የለሽ ባህሪ ይሆንብዎታል። ታዲያ «ለማን አቤት ይባላል?» እንዲሉ ጭንቅላትዎን እያወዛወዙ «እዚህ ሆቴል ድጋሚ ድርሽ አልልም» ብለው ምለው ተገዝተው መውጣትዎ አይቀርም። ነገሩ ግን ወዲህ ነው። ይሄ ችግር እርስዎ በገቡበት ሆቴል ብቻ ያስተዋሉት እንዳይመስልዎ። በእርግጥ በመስተንግ ዷቸው የተመሰገኑ፣ ሆቴላቸውን በዘመናዊ መንገድ የሚመሩ ባይጠፉም፤ በስፋት ከላይ የተጠቀሰው ዓይነት ችግር የሚስተዋልባቸው በርካታ ኢንተርናሽናልና ባለ ኮከብ የሚል ቅጽል ያለባቸው የሀገራችን ሆቴሎች ናቸው። «ለመሆኑ ምን ይሆን ችግሩ?» ብለው ጠይቀው ያውቃሉ?
በአደጉት አገሮች የሆቴል ኢንዱስትሪው እንደ ዋንኛ የኢንቨስትመንት ዘርፍ በትኩረት ይታያል። ምክንያቱ ደግሞ በቀዳሚነት ለቱሪዝም ዕድገት መቀላጠፍ የሆቴሎች ዘመናዊነት እና በስፋት መኖሩ አስፈላጊ መሆኑን ስለሚያምኑበት ነው። ወደ አንድ አገር በጉብኝትም ሆነ በተለያየ ምክንያት የሚያቀኑ ሰዎች ተመጣጣኝ ክፍያ እና አርኪ አገልግሎት መኖሩን ለማረጋገጥ ቅድሚያ ሲሰጡ ይስተዋላል። ሆቴሎቹም ቢሆኑ በብቁ ባለሙያ ዎች፣ በተመጣጣኝ ክፍያ ታግዘው መልካም ስምና ዝናቸውን ለመጠበቅ ተግተው ይሰራሉ። «እከሌ ከከሌ» ብለው ሳይለዩ እግረ መንገዳቸውን ከተማቸውን ጥሩ የቱሪስት መዳረሻ ያሰኛሉ።
ወደ አገራችን ስንመለስ ከላይ ያወሳነው ጉዳይ የተገላቢጦሽ ሆኖ እናገኘዋለን። ትናንሽ ሆቴሎችን ጨምሮ ከፍተኛ አቅም እስካላቸው ባለኮከብ ሆቴሎች የተለያዩ ክፍተቶች ይስተዋልባቸዋል። በተለይ ዘርፉን በባለሙያ የመምራት ችግር ለዘመናት አነጋጋሪ ችግር ሆኖ እንደዘለቀ ነው። ጉዳዩን ጠንቅቀው የሚያውቁት ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ከጊዜ ወደ ጊዜ ሆቴሎችን ለመገንባት ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ቢያፈሱም፤ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ በርካታ ክፍተቶች እንደሚያስተውሉ ይናገራሉ። በተለይም አገልግሎት አሰጣጡ በባለሙያ አለመታገዙን ልብ ይሏል። ሆኖም ግን ባለሙያዎቹ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ያላቸው ወይም በተለምዶ «ብራንድ» ተብለው በሚጠሩት ሆቴሎች ይህ ዓይነት ችግር እንደማይስተዋልባቸው ይገልፃሉ።
አቶ ቁምነገር ተከተል ይባላሉ። የኦዚ ቢዝነስ እና ሆስፒታሊቲ ግሩፕ የአማካሪ ድርጅት ዋና አማካሪ እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት የአስተዳደር ችግር በስፋት አገር በቀል በሆኑ ሆቴሎች ውስጥ ይታያል። ይሄ ችግር የሚመጣው ደግሞ በቀጥታ የባለቤቱ ጣልቃ ገብነት ሲኖር ነው። በዚህ የተነሳ ደግሞ ሆቴሉ በባለሙያ እንዳይተዳደር እና ደንበኞችም ተገቢውን ግልጋሎት እንዳያገኙ ያደርጋል ይላሉ።
«በአገር ውስጥ ባለሙያ በጥቅል የለም ማለት አይቻልም» በማለት የተማረ የሰው ኃይል እጥረት የፈጠረው ችግር ብቻ አለመሆኑን ይገልፃሉ። ነገር ግን ባለሙያዎቹ ከሆቴሉ ባለቤቶች ቀጥተኛ ተፅዕኖ ስለሚያድርባቸው በሥራው ላይ ላይቆዩ ይችላሉ። አንዳንዴም ሠራተኞቹ ሙያው ኖሯቸው የተግባር ልምምድ ስለማያገኙ እና በቂ ክህሎት ስለማይኖራቸው ቀጣሪዎቹ ፍላጎት የሚያጡበት ሁኔታ መኖሩን አስተውለዋል።
ከፅንሰ ሃሳብ የዘለለ የተግባር ትምህርት አለመኖሩ ሌላኛው እንቅፋት መሆኑን የሚናገሩት አቶ ቁምነገር ፤ ከዚህ ቀደም በአገር ውስጥ የነበሩት ሆቴሎች ደረጃ ያልወጣላቸው ነበሩ። ይህ ከህንፃ ግንባታ እና ዘመናዊነት ውጪ። አስተዳደራዊ ጉዳይንም ይጨምራል። በመሆኑም ጥሩ ሆቴል ገምብቶ ጥሩ አስተዳደር ከሌለው ሥራው ሁሉ ድካም ይሆናል። የሆቴል ባለቤቶች ለባለሙያ ትልቅ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ያሳስባሉ።
ዶክተር አያሌው ሲሳይ የሆቴል ማኔጅመንት እና የቱሪዝም ዘርፍ መምህር ናቸው። የሆቴል ዘርፍ ከባለሙያ ውጪ የሚመራ ከሆነ በሥነ ሥርዓት አይጓዝም የሚል አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። የአቶ ቁምነገርን ሃሳብ በመጋራትም በዋናነት ችግሩ የሚስተዋለው በአገር በቀል ሆቴሎች ላይ መሆኑን ይጠቁማሉ። በዚህ መነሻ ደንበኞችም የሚፈልጉትን ግልጋሎት እንደማያገኙ ይናገራሉ።
«በሆቴል ኢንዱስትሪው ያሉ ችግሮች ተነቅሰው ወጥተው ለችግሮቹ መፍትሄ ይሆናሉ በተባሉ ጉዳዮች ላይ መምከር እና ተገቢውን መፍትሄ ማበጀት ቀዳሚ ሥራ ሊሆን ይገባል» የሚሉት ዶክተር አያሌው፤ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርቱን በንድፈ ሃሳብ ከመስጠት ባሻገር የተግባር ልምምድ የሚያገኙበትን ሁኔታ ሊያመቻቹ እንደሚገባ ይጠቁማሉ። በሆቴል ኢንዱስትሪው በሀገሪቱ የሚታየውን ብቁና፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግር ለመፍታት ሆቴሎችና በዘርፉ ያሉ የትምህርት ተቋማት ተቀናጅተው የመስራት ችግር እንዳለባ ቸውም ያምናሉ። ተማሪዎቹን ለተግባር ልምምድ የሚቀበሉ ሆቴሎችም አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ስልጠናው በትክክል እንዲሰጥ የበኩላቸውን ድጋፍ የማድረግ ችግር እንዳለባቸው አስተውለዋል።
አቶ አብዱልፈታህ ተማም የኤቲኤ ቱሪዝም ኮሌጅ ባለቤት ናቸው። ኮሌጁ የሆቴል ማኔጅመንትን ጨምሮ በቱሪዝም ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን ይሰጣል። እንደ እርሳቸው እይታ በመስኩ ላይ የበቃ የሰው ኃይል እጥረት አለ። ይሄ ደግሞ በአገሪቷ ላይ ሙያውን የሚያስተምሩ ተቋማት አነስተኛ በመሆናቸው የተፈጠረ መሆኑን ነው ለአብነት የጠቀሱት በመሆኑም ዘርፉ በባለሙያዎች እንዲመራ ከፍተኛ የግንዛቤ ሥራ መስራት ይገባል። ብቁ ባለሙያዎችን ከማፍራት ባሻገር የትምህርት ተቋማት በስፋት ሊቋቋሙ እንደሚገባ ያሳስባሉ።
«በርካታ ሆቴሎች የአስተዳደሩ ሥራ በባለሙያዎች እንዲመራ ለማድረግ ከትምህርት ተቋማት የእናስተምርላችሁ? ጥያቄ ሲቀርብላቸው ምላሽ አይሰጡም» የሚሉት አቶ አብዱልፈታህ አብዛኞቹ አገር በቀል ሆቴሎች በተለምዶ አሰራር ነው የሰው ኃይል የሚቀጥሩት። ይሄ ደግሞ አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ያመጣል የሚል እምነት አላቸው። ዘመናዊ ሆቴሎችን ገምብቶ ዘመናዊ የአስተዳደር ባለሙያዎችን ማግኘት ካልተቻለ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል አስቸጋሪ ይሆናል። በመሆኑም የሆቴል ባለቤቶች ከማሰልጠኛ ተቋማት ጋር ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም በአንድ ወቅት የሆቴል ማኔጅመንት ተማሪዎችን ሲመርቁ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሰጥተው ነበር። በወቅቱም አገሪቱ ለሰለጠነ የሰው ኃይል በሰጠችው ትኩረት በርካታ የመንግሥትና የግል የትምህርት ተቋማት ተቋቁመው በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ እያሰለጠኑ እንደሚገኙም ተናግ ረዋል። በዚህ የውድድር ዘመን ተገልጋዮች በእውቀት ላይ ለተመሰረተ አገልግሎት ከፍ ያለ ዋጋ ይሰጣሉ ብለዋል። በመሆኑም በሰለጠነ ባለሙያ የማይመሩ ሆቴሎች ለኪሳራ እንደ ሚዳረጉ ገልፀው አስተዳደራቸውን ማዘመን እንደሚገባቸው አሳስበው ነበር። በተለይም በአገራችን የሚገኙ ሆቴሎች በሰለጠነ የሰው ኃይል በመምራት ረገድ ክፍተት እንዳለባቸው በጥናት መረጋገጡን አመላክተዋል።
በዚህ የውድድር ዘመን ተገቢውን እውቀት ያልተላበሰ ባለሙያ በዘርፉ ማሰማራት ተመራጭ ሊሆን እንደማይችል የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ የሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ መሻሻል እያሳየ መምጣቱን ጠቅሰው በሰለጠነ የሰው ኃይል የመምራቱን ጉዳይ የሆቴል ባለቤቶች ሊያስቡበት እንደሚገባ አስገንዝበው ነበር።

ዜና ሀተታ
ዳግም ከበደ

Published in የእለቱ ዜና
Page 2 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829513
TodayToday1143
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7233
This_MonthThis_Month29693
All_DaysAll_Days2829513

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።