Items filtered by date: Monday, 16 April 2018

የሀገራችንን የኋላ ታሪክ ስንመለከት የተለያዩ ተቃርኖዎችን እናገኛለን፡፡ በአንድ በኩል የሰው ልጅ መገኛና የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት፣ ለውጭ ወራሪ ሃይሎች ያልተንበረከከችና ነፃነቷን አስከብራ የቆየች፤ በሌላ በኩል ደግሞ በሂደት ከነበረችበት የሥልጣኔ ደረጃ እየተንሸራተተች የድህነትና የኋላ ቀርነት መገለጫ መሆናችን የኋላ ታሪካችን ያስታውሰናል፡፡
ባሳለፍነው የአንድ ምዕተ ዓመት ጊዜ ውስጥ የነበረውን ታሪክ ስንመለከት ኢትዮጵያ በአብዛኛው ለህዝቦቿ ያልተመቸችና ድህነት መገለጫዋ የሆነች ጊዜ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ከ19ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ በአንድ በኩል የከተሞች መስፋፋትና የህዝብ ቁጥር እየጨመረ መሄድ በሌላ በኩል ደግሞ ለህዝብ ፍላጎት ተገቢውን ትኩረት ባልሰጡ መሪዎች የተነሳ የህዝብ ቅሬታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣበትና ለጦርነት ብሎም ለኢኮኖሚ ችግር የተዳረግንበት ዘመን አሳልፈናል፡፡
ያለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ደግሞ አገራችን ከቆየችበት የጦርነትና የኋላቀርነት ታሪክ ወጥታ ፊቷን ወደ ልማት ያዞረችበትና ህዝቦቿም የሠላም አየር መተንፈስ የጀመሩበት ወቅት ነው፡፡ ባለፉት አሥራ አምስት ዓመታትም ኢትዮጵያ በጀመረችው የልማት ትግል ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ለዘመናት የተንሰራፋውን ድህነት የኋላ ታሪክ ለማድረግ ተጨባጭ ፍንጭ አሳይታለች፡፡
ያም ሆኖ ግን አገራችን የጀመረችው የልማት ጎዳና ለዘመናት ተንሰራፍቶ ከኖረው ድህነትና ኋላቀርነት እንዲሁም በየጊዜው እያደገ ከመጣው የህዝብ ፍላጎት ጋር ተዳምሮ ህብረተሰቡን በሚፈለገው ደረጃ ሊያረካ አልቻለም፡፡ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የኅብረተሰቡ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች በወቅቱና በተገቢው ሁኔታ ምላሽ ባለማግኘታቸው ህብረተሰቡን ለቅሬታና ለአመፅ ዳርጎታል፡፡
በአንድ በኩል ገና ከወደቀበት ቀና ማለት የጀመረው የአገራችን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣውን የህዝቡን ፍላጎት ለማርካት የሚያስችል አቅም አለመገንባቱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን የህዝብ ፍላጎት ተረድቶ በቁርጠኝነት ለማስፈፀም አቅሙንና ጉልበቱን ለዚህ ብቻ ማዋል የሚችል አስፈፃሚ ሃይል በሚገባው ደረጃ አለመፈጠሩ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማርካት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የራሱን አሉታዊ ጫና ፈጥሮ ሁከቱን ይበልጥ አባባሰው፡፡
በዚህ የተነሳም ኅብረተሰቡ በተለይ ወጣቱ በየአካባቢው በመንግሥት ላይ ቅሬታ ማሰማት ብቻ ሳይሆን ለተጀመረው የልማት እንቅስቃሴ ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል፡፡ አጋጣሚውን መጠቀም የፈለጉ ሃይሎችም በተነሳው እሳት ላይ ቤንዚን በማርከፍከፍ አገራችን ወደ እርስ በርስ ጦርነትና ወደማያባራ የእርስ በርስ ግጭት እንድትገባ የበኩላቸውን ግፊት ሲያደርጉ ሰነበቱ፡፡
ያም ሆኖ ግን አገሪቱን ከድህነት ማላቀቅ ዋነኛ ዓላማው አድርጎ የተነሳው የኢትዮጵያ መንግሥት ለዓመታት በልማቱ ሥራ ላይ ያካበተውን ልምድና ተሞክሮ በመጠቀም በሃገሪቱ ሰላምን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ አቋም ወስዶ በመንቀሳቀስ ስኬት አስመዝግቧል፡፡ መንግሥትም በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከአንድም ሁለት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ቢገደድም ችግሩን በራሱ አቅም ለመፍታት ለህዝቡ በገባው ቃል መሰረት መንስኤውን በጥልቀት ከመረመረ በኋላ በበሰለ የአመራር ጥበብ በመፍታት ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል፡፡
ያም ሆኖ ግን ባለፉት ሁለት ዓመታት የተነሱት ግጭቶችና የተከሰተው ውድመት “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው ገና ዳዴ ማለት ለጀመረው የአገራችን ኢኮኖሚ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ በተለይ በነዚህ የግጭት ወቅቶች የታየው የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን የማውደም፣ ፋብሪካዎችን የማቃጠልና የዜጎችን ንብረት የማጥፋት እንቅስቃሴ በአገርም ሆነ በዜጎች ህይወት ላይ ያሳደረው ተፅእኖና ጫና ቀላል አይደለም፡፡
ለአመታት ላባቸውን አንጠፍጥፈው ያፈሩት ሃብትና ንብረት በድንገት የወደማቸው ዜጎች ጉዳት የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጉዳት ሆኖ ሊሰማን ይገባል፡፡ መንግስት ከህዝብ በሚሰበስበው ግብር የሚገነቡና ነገ ራሳችን የምንጠቀምባቸው የጋራ ሃብቶቻችን መጥፋትም የሁላችንም ጉዳት በመሆኑ ሊቆጨን ይገባል፡፡
ይህ ቁጭታችን ግን ባለፈው ለመፀፀት ብቻ ሆኖ መቅረት የለበትም፡፡ ዋናው ቁምነገር ካለፈው ስህተት ተምሮ ነገን የተሻለ ማድረግ ነው፡፡ ከትላንት ይበልጥ ነጋችን የተሻለ እንዲሆንም መስራት ብልህነት ነው፡፡ ስለዚህ ያለፈውን ስህተት እንደትምህርት ወስደን ለነገዋ ኢትዮጵያ የተሻለች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ያለፈውን ጥፋት በማካካስና የባከነውን ጊዜያችንን ማካካስ ይጠበቅብናል፡፡
ትላንት የአባቶቻችን ነው፣ ነገ ደግሞ የልጆቻችን ነው፤ ዛሬ ግን የኛ ነው፡፡ ስለዚህ የኛ የሆነውን ዛሬ በአግባቡ መጠቀም የኛ ሃላፊነትና ግዴታም ጭምር ነው፡፡ የበሰለ ማህበረሰብ ከራሱም በላይ ለልጆቹ የተሻለ ነገር ትቶ ለማለፍ ይጥራል፡፡ ለነገው ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማውረስ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና ካስቀመጥነውም ጊዜ ፈጥነን ከድህነት እንድንወጣ መትጋት ይገባል፡፡ ለዚህም በአንድ በኩሉ ከባለፈው ተምረን ዳግም የሰላም መደፍረስ እንዳይከሰት ተግተን መጠበቅ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ፊታችንን ወደ ልማት በማዞር በመደበኛ የስራ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከእንቅልፍና ከእረፍት ጊዜያችን ጊዜ ቀንሰን ለስራ እንጠቀምበት፡፡

Published in የእለቱ ዜና

የኢትዮጵያ ሐይቆች የሚሰጡትን ግልጋሎት ያክል ጥበቃ ስለማይደረግላቸው ለአደጋ እየተዳረጉ መሆኑን የዘርፉ ምሑራን ይናገራሉ፡፡ ሰዎችም በሐይቆቹ ላይ ባደረሱት ጉዳት ተመልሰው ለጉዳት እየተዳረጉ በመሆኑ ተገቢው እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባም ይመክራሉ፡፡

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ዝናቡ ገብረማርያም እንደሚገልጹት፤ አብዛኛዎቹ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች በፍጥነት እያደጉ ካሉ ከተሞች አካባቢ ያሉ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ከከተሞች በሚወጡ በካይ ነገሮች ጫሞ፣ ዓባያ፣ ሐዋሳ፣ ዝዋይ እና ቆቃን የመሳሰሉ ሐይቆች ለብክለት እየተዳረጉ ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ የብክለቱን መጠን መጨመር ያህል ችግሩን ለመከላከል እየተደረገ ያለ እርምጃ ባለመኖሩ ሐይቆቹ እጅግ አስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡
በአርሲና ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲዎች ጥምረት እአአ በመጋቢት 2017 ትኩረቱን በዝዋይ ሐይቅ ላይ አድርጎ በባቱ ከተማ በተካሄደ መድረክ ላይ የቀረበ ጥናት፣ በስምጥ ሸለቆ ያሉ በርካታ ሐይቆች የደህንነት ስጋት የተጋረጠባቸው መሆኑን ያሳያል፡፡ በዚህ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የከተሞች እድገት፣ ሐይቆች ላይ የተመሰረተ የመስኖ ልማት መስፋፋት፣ የደን መጨፍጨፍና የአፈር መከላት፣ የኢንዱስት ሪዎችና የእርሻ ግብዓት ኬሚካሎች እንዲሁም ከከተሞች የሚለቀቁ ቆሻሻዎች ለሐይቆች ደህንነት ስጋት ላይ መውደቅ ተጠቃሽ መሆናቸውንም አስፍሯል፡፡
ከ25 ዓመት በፊት የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዝዋይ ሐይቅ ላይ ማከናወናቸውን የሚያስታውሱት በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል የውሃ ሳይንስ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ግርማ ጥላሁን፤ በድጋሚ ከ10 ዓመት በፊት የሐዋሳ ሐይቅና የጫሞ ሐይቅን ጨምሮ በዚሁ ሐይቅ ላይ የዶክትሬት ዲግሪ ጥናታቸውን ማከናወናቸውን ይናገራሉ፡፡ በዚህም በተለይ የዝዋይ ሐይቅ ፊዚካላዊ /የመጠን/፣ ኬሚካላዊና ሥነ ሕይወታዊ ለውጥ ማሳየቱን በመጠቆም፤ ይሄም በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት እንደደረሰበት አመላካች መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም እነዚህ ሐይቆች ከጥቅማቸው አንጻር ጉዳታቸውን ለመከላከል የሚወሰድ እርምጃ አለመኖሩን ይገልጻሉ፡፡
እንደ ዶክተር ግርማ ገለጻ፤ በሰው ልጆች እንቅስቃሴ ከከተሞች ከሚለቀቁ ቆሻሻዎች ጀምሮ ከኢንዱስትሪዎች እስከሚወጡ ኬሚካሎች የውሃውን ይዘት እየበከሉት ይገኛል፡፡ በሐይቆቹ አካባቢ ያሉ ደኖች በመመንጠራቸውም ሐይቆች በደለል እየተሞሉ መጠናቸው እየቀነሰ ነው፡፡ ሆኖም ለጥፋቱ የተዘረጉ እጆች፤ ችግሩን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ሐይቆቹን ለማልማት በሚገባው ደረጃ አልተንቀሳቀሱም፡፡ ይህ ደግሞ ካለው ከፍተኛ የሕዝብና የከተሞች እድገት፤ እንዲሁም የፋብሪካዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ሐይቆቹን በከፍተኛ ደረጃ የሚጎዱ ሁኔታዎች አብረው እንዲያድጉ፤ በብዝሃ ሕይወትም ሆነ በሰው ላይ ጉዳት እንዲደርስ ያደርጋል፡፡ ከችግሩ ስፋትና ፍጥነት አንፃርም ሐይቆቹን የመታደግ ሥራው ተዘንግቷል፡፡
ዶክተር ዝናቡ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ማንኛውም የውሃ አካል ሲበከል መጀመሪያ የሚጎዳው በውሃ አካል ውስጥ ያለው ብዝሃ ሕይወት ነው፡፡ ከዚያም ወደ ሰውና አካባቢ ይሄዳል፡፡ ለምሳሌ ውሃው ሲበከል የሐይቆቹ መጠን ይቀንሳል፤ በሳር ይወረራሉ፤ አሁን ላይ ለሐይቆች እጅግ እያስፈራ ያለው የእምቦጭ አረምም ስጋት ይሆናል፡፡ ከሐይቁ የሚወጡ ወንዞች ካሉም መጠናቸው ይቀንሳል፡፡ በውስጡ ያሉትንም ፍጥረታት ይጎዳሉ፡፡ የተበከለ ዓሣ ካለ ደግሞ የሰውን ጤና ይጎዳል፡፡ ስለዚህ የሐይቆች መበከል ከብዝሃ ሕይወት ጀምሮ እስከ ሰው ጤና ድረስ ተጓዳኝ የሆኑ ችግሮችን ይፈጥራል፡፡
«አንድ ሰው መርዝ ቢጠጣ የጉዳት መጠኑ የሚለካው በጠጣው መርዝ መጠን ሳይሆን በመርዙ ጥንካሬ ነው፤» የሚሉት ዶክተር ዝናቡ፤ የሐይቆች ብክለት ሰዎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በብክለቱ መጠን ሳይሆን በበካይ ነገሩ ጥንካሬ ላይ የሚመሰረት እንደመሆኑ ሐይቆችን የመጠበቅ ሥራው ቸል ሊባል አይገባውም ይላሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም የዝዋይ እና የሐዋሳ ሐይቆች እጅጉን ለተወሳሰበ ችግር የተጋለጡ በመሆናቸው ከሐይቆቹ መጠቀም ብቻ ሳይሆን ሐይቆቹን መጠበቅ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
እንደ ዶክተር ግርማ ገለጻ ደግሞ፤ ለሐይቆች እንደሚደረገው ጥበቃና እንክብካቤ ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ውሃው ውስጥ ባለው ነገር ይጠቀማሉ ወይም ይጎዳሉ፡፡ ምክንያቱም የተፈጥሮ ሚዛኑ ባልተዛባበትና ብክለት በሌለበት ሁኔታ ላይ ያሉ ሐይቆች ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ የሚፈልጉትን ነገር ስለሚያገኙበት ጤናማ ይሆናሉ፡፡ የተፈጥሮ ሚዛናቸው ካልተጠበቀ ውሃውን የሚጠቀሙት ሁሉ አደጋ ላይ ይወድቃሉ፡፡ ሰዎችም በሐይቆ ላይ ባደረጉት ነገር ተጎጂ ይሆናሉ፡፡
በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት ከተፈለገ ችግሩ መፈጠሩን ከማመን ይጀምራል፡፡ ችግሩን ለሕዝቡ ከማሳወቅ ጀምሮ ጉዳዩን ወደውሳኔ እስከማምጣት ሊሰራበትም ያስፈልጋል፡፡ የሐይቆች ጥቅምም ሆነ ጉዳት ለሁሉም እኩል የሚደርስ ስለሆነም ሥራው ለአንድ ወገን ብቻ ሳይተው በጋራ መስራትንም ይጠይቃል፡፡
ዶክተር ዝናቡም እንደሚናገሩት፤ እነዚህን ሐይቆች ከችግር ለመታደግ ሥራው የእከሌ ተብሎ የሚተው ባይሆንም፤ የሚመለከታቸው አካላት በኃላፊነት ስሜት ተቀናጅተው ከመስራት ይልቅ ኃላፊነታቸውን ቸል ማለት ይታይባቸዋል፡፡ በተመሳሳይ በአገሪቱ «የኢትዮጵያ የውሃ ሀብት አስተዳደር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ_ ቁጥር ፻፲፭/፲፱፻፺፯»ን ጨምሮ የአዋጅ፣ የደንብና መሰል ወረቀት ላይ የተቀመጡ ሕጎችና እነዚህን የሚያስፈጽሙ ተቋማት ያሉ ቢሆንም፤ የተቋማቱ ተቀናጅቶ አለመስራት እና ሕጉን ተፈጻሚ ያለማድረግ ለሐይቆቹ መጎዳት አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ችግሩን ከመከላከል አኳያ በተግባር የተተረጎመ ሕግ ባለመታየቱም፤ ሕጎች ተግባራዊ በሚሆኑበት ዙሪያም ከትላልቅ የመንግሥት ተቋማት ጀምሮ በሐይቆቹ አካባቢ እስከሚኖረው ኅብረተሰብ ችግሩን ለመከላከል በቅንጅት መስራትና ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡
በዝዋይ ሐይቅ ዙሪያ የተከናወኑ ጥናቶች፣ እንደሚያሳዩት፤ እአአ እስከ 2017 መጀመሪያ ባለው ጊዜ ከአበባ ማሳዎችና ሌሎች ቦታዎች ወደ ሐይቁ ከሚገቡ በካይ ኬሚካሎችና ቆሻሻዎች ባሻገር፤ ከመቂ ወንዝ ጋር ብቻ በሊትር 0.28 ሚሊ ግራም ማዳበሪያ ወደ ሐይቁ ይቀላቀላል፡፡
«ከየትኛውም ሐይቅ በላይ በሰው የተነካካ ሐይቅ ቢኖር ዝዋይ ሐይቅ ነው፡፡ ይሄም በግልጽ ይታያል፤» የሚሉት ዶክተር ግርማ፤ «ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል» እንዲሉ የሐይቁ ውሃ ከመበከል አልፎ ያለ እየመሰለ ሊደርቅ እንደሚች ልም ይገልጻሉ፡፡
ከላይ የተጠቀስነው ጥናትም የተለያዩ የጥናት ውጤቶችን ዋቢ በማድረግ፣ የሐይቆቹ የደህንነት ችግር በዚህ መልኩ ከቀጠለም በ2021 የዝዋይ ሐይቅ በ25 ስኩዬር ኪሎሜትር እንደሚቀንስ፤ አቢጃታም ሊደርቅ እንደሚችል ጥናቱ አመልክቷል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታም ለሐይቆቹ ሕልውና ሳይሆን ጥፋት እየተሰራ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ግርማ በበኩላቸው፤ ይህን ተገንዝቦ የመፍትሄ እርምጃዎች ካልተወሰደ የሐሮማያ ሐይቅ እንደመድረቁ፤ የአቢጃታ ሐይቅም 40 በመቶው እንደመጥፋቱና ወፎች ጭምር እንደመሰደዳቸው በሌሎች ተመሳሳይ ችግር ላለመድረሱ ዋስትና አለመኖሩን ይገልጻሉ፡፡ ወደፊት የኢትዮጵያን እድገት ጠፍሮ ይይዛት የሚባለው የውሃ ችግርም በከተሞች እድገት ውስጥ አሁንም እየታየ መሆኑን በመጠቆምም፤ አደጋውን ለመቀነስ በየመድረኩ የሚገቡትን ቃል ጥናቶችን መሠረት አድርጎ ወደተግባር መቀየር የግድ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ለትውልድ ተሻጋሪ የሆነ ሥራ መስራት ከወዲሁ እንደሚያስፈልግም ይመክራሉ፡፡

ዜና ትንታኔ
ወንድወሰን ሽመልስ

 

Published in የእለቱ ዜና

ዕለቱ እሁድ የዳግማዊ ትንሳኤ ቀን ነው፡፡ ይህ በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከሚከበሩ በዓላት አንዱ ቢሆንም፣ የአደባባይ በዓል አይደለም፡፡ ቦሌ አካባቢ ግን ምን በዓል አለ? በሚያስብል ድምቀት በየተለያዩ የአገር ባህል አልባሳ ትና በሰንደቅ ዓላማ ባሸበረቁ ቲሸርቶች የደመቁ በርካታ ዜጎች መንገዱን አጨናንቀውታል፡፡ 

እኛም የሚሌኒየም አዳራሽ መግቢያ ከሚገ ኝበት መንገድ አሳብረን ወደ ውስጥ ዘለቅን፡፡ በርካ ቶች የበልጉ ወቅታዊ ቅዝቃዜ ሳይበግራቸው አምረ ውና ደምቀው በግራና ቀኝ በሚገኘው የእግረኞች መንገድ ላይ ቆመዋል፡፡ ሌሎች ‹‹ስንኖር ሰው ስንሞት ሀገር እንሆናለን›› በሚል ዶክተር አብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በተሰየሙበት ወቅት ከተናገሩት ውስጥ የተቀነጨበ የአንድነት መንፈስን የሚዘራ ንግግርና የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ መለያ በሆኑት ሦስት ቀለማት የተዘጋጁ ቲሸርቶችን እየገዙ ይለብሳሉ፡፡ ዕለቱም ዳግም ትንሳዔ ነውና በስፍራው የሚታዩት ኩነቶች ድርብ ድርብርብ በዓል አስመስለውታል፡፡
በሥፍራው ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ከቀትር በኋላ ለሚካሄደው ውይይት ማልደው የተገኙት ታዳሚዎችም በዳግም ትንሳዔ ዕለት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሲከሰት የነበረውን አለመረጋጋት ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ድባቅ በመምታት ዳግም ለሰው ልጆች ሁሉ የተባለውን ሰላም ለማምጣት ቆርጠው እንደተነሱ መላ ሁኔታቸው ይናገራል፡፡ ከግል መኖሪያ ቤታቸው ወጥተው ለጋራ መጠለያ አገራዊ ቤታቸው የተነገረውን ታላቅ ቃል የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በተገኙበት ዕውን እንዲሆን ለአብሮነትና ለሰላም ቃል ሊገቡ ሰዓቱ ደረሰ አልደረሰ ስሜት ውስጥ በጉጉት ሲጠባበቁ አንዳንዶቹን ጠጋ ብለን አሁን ያለውን ሁኔታ እንዴት ይመለከቱታል ስንል አነጋገርናቸው፡፡
ህዝቡ አብሮ የመኖር እሴቱ ተሸርሽሮና እየተለያየ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን ሰላም የተፈጠረ መሆኑን ከአምቦ ለዚሁ መድረክ በስፍራው በማለዳ አዲስ አበባ የመጣው ወጣት ኪታባ ቀጄልቻ ይናገራል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ተዘዋውረው ችግሮችን ለማርገብና ወደ አንድነት የሚወስድ ሥራ መስራታቸው መልካም መሆኑን በመግለጽም ለወጣቱ ጥያቄዎች ግን ፈጣን ምላሽ መስጠት ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ተናግሯል፡፡ በመንግሥት የተገባው ቃል ተፈፃሚ ከሆነ ህብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም የአገሪቱን የሰላምና የልማት ጉዞ ለማስቀጠል ዝግጁ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡
መንግሥት ከህዝብ ጋር የመግባባት ችግር አጋጥሞት እንደነበር ያጫወቱን ደግሞ የአዲስ አበባ ነዋሪው አቶ ኃይለማርያም አበበ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን የመልካም አስተዳደር እና የሥራ አጥነት ችግሮች በመኖራቸው የህብረተሰቡ ቅሬታ ነበር፡፡ ይህም በአገሪቱ የሰላም እጦት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡ከዚህ ባለፈም በአንዳንድ አካባቢዎች ይስተዋል የነበረው የኋላቀርነትና የዘረኝነት አስተሳሰብ የህዝቡ ስነልቦና አንድነትና ስሜት ላይ ክፍተት እንዲፈጠር አድርገው ቆይተዋል፡፡
እንደ አቶ ኃይለማርያም ገለፃ መንግሥት በአሁኑ ወቅት ችግሮችን ለመፍታት እየወሰደ ባለው የለውጥ እርምጃ የተረጋጋ ሁኔታ እየመጣ ነው፡፡ በቅርቡም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር የገቡት ቃል በህዝቡ ውስጥ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡ በመሆ ኑም በእያንዳንዱ ተግባር የጋራ መግባባት ከተፈጠረና ህብረተሰቡን ባለቤት አድርጎ ከተሰራ ለውጥ እንደሚመጣ የተስፋ ጭላንጭል ማየት ተችሏል፡፡
«የፍቅርና የአንድነት ኪዳን» በሚል መሪ ሃሳብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመንግሥት ቀጣይ የሥራ አቅጣጫ አሳውቀዋል። በመድረኩ ላይ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎት የተውጣጡ ከ25 ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን ከመነሻው እስከመጨረሻውም በአን ድነት በመዘመር ለሰላምና ለአብሮነት ያላቸውን ተነሳ ሽነት አሳይተዋል፡፡
የዕለቱ መርሐግብር የተጀመረው በሃይማኖት አባቶችና በአገር ሽማግሌዎች ምርቃት ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ የታየው የተሳታፊው ድባብም ልብን የሚነካ የአብሮነትና የአንድነት ስሜትን ያንፀባረቀ ነው፡፡ በዚህ ቦታ ላይ የተገኘ ሁሉ አገሪቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከነበረችበት የሰላም ችግር ተላቃ ወደ አንድነትና ሰላም መምጣቷን ይረዳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገና ንግግር እንዲያደርጉ ሲጋበዙ በአዳራሹ የነበረው ስሜት ደግሞ የተለየ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ጥቂት ቀናት በተለያዩ አካባቢዎች ያደረጓቸው ንግግሮች ተስፋ የሚሰጡና አነቃቂ መሆናቸው ለዚህ ምክንያት እንደነበር በርካቶችም ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ንግግራቸው እንደተለመደው ለወደፊቷ ተስፋ ያላት ኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ ንግግር አድርገዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየመሃሉ በተሳታፊ ጭብጨባ ታጅበው ባደረጉት ንግግርም በርካታ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ዳሰዋል፡፡ በንግግራቸው መጀመሪያም ከዚህ ቀደም እንዳደረጓቸው ንግግሮች ሁሉ የኢትዮጵ ያን ታሪኮች ዳስሰዋል፡፡ በተለይ የአገራችን የኋላ ታሪኮች ጥንካሬን እንጂ ድክመትን እንዳላሳዩን በመጠቆም ይህንን ጥንካሬአችንን በተግባር ለመተ ርጎም መስራት እንደሚገባንም በአፅንኦት ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን የአብሮነትና የአንድነት ስሜትም ምን ያህል የጠነከረና በመደመር ላይ የተመ ሰረተ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ለዚህም የጋራ ትግል፣ ፅትና የአብሮነት መንፈስ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከቃላት በተረፈ የገቡትን ቃል በተግባር ለመፈፀም ቁርጠኛ መሆናቸውንም በንግግራቸው ውስጥ አካተዋል፡፡ ሰሞኑን ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያደረጓቸው ውይይቶች ዓላማም የጀመርናቸውን የልማት ሥራዎች በህዝባዊ ድጋፍ አጅበን ወደ ተግባር ለመግባት ጠቃሚ በመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡
«እኛ ሚሊዮኖች ሆነን እንደ አንድ ቤተሰብ መስራት ይገባናል» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለአገሩ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የመንግሥትን ኃላፊነት በተመለከተም ሲገልፁ «መንግሥት ህብረተሰቡ የሚፈልገውን ብቻ ሳይሆን የሚያስፈል ገውን የማሟላት ኃላፊነት አለበት ብለዋል»፡፡ በተለይ እያደገ የመጣውን የህዝብ ፍላጎት ለማሟላት መንግሥታቸው የማስፈፀም አቅም ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን፣ ጉቦና የጥቅም ሽርክና ጎጂ መሆናቸውን አውቆ መስራት እንደሚገባ በአፅንኦት ጠቁመው፣ በመንግ ሥት መዋቅር ውስጥ የሚደረግ ምደባም በእውቀትና በችሎታ ብቻ እንዲሆን ይደረጋል ብለዋል፡፡
የመልካም አስተዳደር ከሆኑ ችግሮች ውስጥ አንዱ በስብሰባ የሚባክን ጊዜ መሆኑ ህብረተሰቡ በተደጋጋሚ ቅሬታ እንደሚያሰማ ይታወ ቃል፡፡ ይህንን በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጤታማ ባልሆነ ስብሰባ የሚባክነውን ጊዜ ለማስተካከል አሰራሮችን በቀልጣፋና ዘመናዊ አሰራር መተካት ይገባናል ብለዋል፡፡
የአገሪቱ ኢኮኖሚ ሊለወጥና ሊያድግ የሚች ለው በህዝቡ የጋራ ጥረት በመሆኑም ህዝቡ በመደበኛ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቶ መስራት እንዳለ በት አስገንዝበዋል፡፡ ከዚህ በፊት ያጋጠመው ችግር ጊዜያዊ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ «እንዲህ አይነት ወደኋላ የመመለስ ችግሮች በዚያው መቅረት ካለ እንጂ ካለበለዚያ ግን እንደመንደርደሪያ ተጠቅመን ባቸው ወደፊት ልንራመድ ይገባል» ብለ ዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በተለይ የባከነውን ጊዜ ለማካካስ መስ ራት አለብን ብለዋል፡፡
ቀጣዩ ምርጫም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የንግግር አንዱ ጉዳይ ነበር፡፡ በዚህም ንግግራቸው ተአማኒና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ከወዲሁ በቅንጅት ለመስ ራት ቃል ገብተዋል፡፡
በንግግራቸው ትኩረት የሰጡት ሌላው ጉዳይ ወጣቱን በተመለከተ ነው፡፡ ሥራ አጥነት ወጣቶችን ለሱስ፣ ለስደትና ላልተገቡ ድርጊቶች እንደዳረጋቸው የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ ለወጣቱ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል፡፡ ወጣቶችም ይህንን ወርቃማ ጊዜ ለሥራ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ንግግራቸው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የዳሰሱ ሲሆን፣ ሁሉም ለአገራዊ አንድነት በጋራ እንዲሰለፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዜና ሐተታ
ፍዮሪ ተወልደ

 

Published in የእለቱ ዜና

አዲስ አበባ፡- የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የድርሻውን ለመወጣት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር አስታወቀ፡፡ ማህበሩ የራሱን ህንፃ ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወጣት ሰለሞን ገብሩ እንደሚለው፤ ማህበሩ ከመንግሥትና ከሌሎች ባለሀብቶች ጋር በመሆን ወጣቱን ተጠቃሚ ለማድረግ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም ማህበሩ በሚያስተዳድራቸው ተቋማት ላይ ወጣቶች ተደራጅተው እንዲሰሩ እየተደረገ ነው፡፡ ሆኖም ውጤቱ በቂ ባለመሆኑና በዙ መስራትን ስለሚጠይቅ በቀጣይ ሥራውን የማስፋፋት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡
እንደ ወጣት ሰለሞን ገለፃ፤ እስካሁን ለወጣቱ ከመጡ የሥራ ዕድሎች ውስጥ በይበልጥ የማህበሩ አባላት ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም አሁንም ብዙ ወጣቶች ሥራ ስላላገኙ ተለይተው ወደ ሥራ የሚገቡበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ ለዚህም ማህበሩ 20 ሺ ወጣቶችን መልምሎ እንዲያቀርብ በተጠየቀው መሰረት እስካሁን አራት ሺ ወጣቶች ተመዝግበዋል፡፡ በዚህ ሂደት ግን የማህበሩ መዋቅር በአግባቡ ያለመስራት ችግር፤ እንዲሁም የወጣቱ ሥራን የማማረጥ ሁኔታዎች ተስተውለዋል፡፡
ማህበሩ አሁን ያለው ገቢ በቂ አለመሆኑን የሚገልጸው ወጣት ሰለሞን፤ በወረዳ ደረጃ ያሉ የማህበሩ አደረጃጀት አመራሮች ደመወዝ ሳይከፈላ ቸው በበጎ ፈቃደኝነት እያገለገሉ እንደሚገኙም ይገልጻል፡፡ የማህበሩ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ከአባላቱ የሚሰበሰበው ወርሃዊ መዋጮ እና በደርግ ዘመን የተለያዩ ማህበራት ንብረቶች የነበሩ ነገር ግን አሁን ማህበሩ የሚያስተዳድራቸው መዝናኛ ቦታዎች መሆናቸውን የሚናገረው ወጣት ሰለሞን ገቢው ከተሰበሰበ በኋላም በከተማና በክፍለከተማ በቋሚነት ለሚሰሩ አመራሮችና ሰራተኞች ደመወዝ እንደሚ ከፍልና ለሥራ ማስኬጃ እንደሚያውለው ጠቅሷል፡፡
በአሁኑ ወቅት ማህበሩ ገቢውን ለማሳደግ ህንፃ በመገንባት የራሱን ጽሕፈት ቤት ለማስገንባትና በዚህም ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለማግኘት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የጠቀሰው የማህበሩ ፕሬዚዳንት ይህም በቀጣይ ወረዳ ድረስ ያለውን መዋቅር ደመወዝ እየከፈሉ ለማጠናከር ያግዛል ብሏል፡፡ ለዚህም ማህበሩ የኤስ.ኤም.ኤስ ሎተሪ ሽያጭ እንዲያካሂድ ፈቃድ ማግኘቱን ጠቁሟል፡፡

መርድ ክፍሉ

 

Published in የእለቱ ዜና

አዲስ አበባ፡- በከተሞች በሚገነቡ ህንፃዎች ላይ የሚገጠሙ መስታወቶች ህብረተሰቡ ላይ ችግር እየፈጠሩ መሆኑ ተገለፀ፡፡ ችግሩን ለማቃለልም ቀድሞ የነበረውን የህንፃ አዋጅና መመሪያ ለማሻሻል እንቅስቃሴ መጀመሩ ተጠቁሟል፡፡

በኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ሲሳይ ደርቤ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳሉት፤ በአዲስ አበባና በሌሎች ክልል ከተሞች የሚገነቡ ህንፃዎች ላይ የሚገጠሙ መስታወቶች በህብረተሰቡ ጤና ላይ ችግር እያስከተሉ ናቸው፡፡ ይህንን ችግር ለመከላከል ቀደም ሲል የፀደቀና በሥራ ላይ ያለ የህንፃ አዋጅ ቁጥር 624/2001 ቢኖርም አዋጁ የቆየና ከጊዜው ጋር መራመድ ያልቻለ በመሆኑ አዋጁንም ሆነ መመሪያውን ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
በሁሉም ከተሞች ላይ የህንፃ አዋጁ አተገባበር ላይ ክፍተቶች እንዳሉ የሚናገሩት አቶ ሲሳይ፤ በተለይ በግንዛቤ ችግር፣ በአቅም ውስንነት እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች የሚፈጠሩት ክፍተቶች ትልቁን ድርሻ እንደሚይዙ ይገልፃሉ፡፡ በአዲስ አበባ ላይም በትክክል እየተተገበረ አለመሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ሆኖም ደንብና መመሪያው በዋናነት በህብረተሰቡ ዓይን ላይ የሚደርሱትን ጉዳቶች ጨምሮ የሚሰሩ ህንፃዎች የህዝብ ጤንነትና ደህንነት የማይጎዱ መሆን እንዳለባቸው የሚያስቀምጥ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
እንደ አቶ ሲሳይ ገለጻ፤ አዋጁንና መመሪያውን የማስፈፀም ኃላፊነት የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ነው፡፡ በዚህም የሚገነቡ ህንፃዎች በከተማ ውበትና በህብረተሰቡ ላይም ጉዳት የማያደርሱ መሆን እንዳለባ ቸው ቁጥጥር ሊያደርጉ ይገባል፡፡ በዚህም የሚሰሩ ህንፃዎች ከዲዛይን ጀምሮ ሲሰሩ ምንም አደጋ እንደማያደርሱ ተረጋግጦ መሆን ያለበት ቢሆንም፤ በመመሪያና በአፈፃፀም ክፍተት በህንፃዎች ላይ የተገጠሙ መስታወቶች በርካታ ሰዎች ላይ የዓይን ጉዳት እያደረሱ ነው፡፡
በመሆኑም በአዋጁ እንዲሁም በመመሪያው ላይ ከወቅቱ ጋር እንዲጣጣም ለማድረግ የማሻሻል ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡ ለዚህም የሚኒስቴሩ ሥራ አዋጆችና መመሪያዎች እንዲወጡ ክትትል የሚያደርግ ሲሆን፤ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አዋጅና መመሪያው ተግባራዊ እንዲሆን ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡
እንደ አቶ ሲሳይ ገለጻ፤ ይህን እንዲቆጣጠሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው ክፍለከተሞች ውስጥ የተቀመጡ የህንፃ ሹሞች ናቸው፡፡ የህንፃ ሹሞቹ በከተሞች ላይ የሚገነቡ ህንፃዎችን ከዲዛይን ጀምሮ ጠቅላላ አሰራሩ ላይ ቁጥጥር የማድረግ ኃላፊነት እንደተሰጣቸውም አቶ ሲሳይ ተናግረዋል፡፡

መርድ ክፍሉ

 

Published in የእለቱ ዜና

አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ከድርቅ አደጋ ጋር በተያያዘ በሚያጋጥም የግጦሽ እጥረት ምክንያት በከብቶች ላይ ለሚደርስ ጉዳት ማካካሻ የሚሆን የእንስሳት መድን ሽፋን መጀመሩ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነጻነት ለሜሳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የእንስሳት መድን ሽፋኑ በክልሉ ከድርቅ አደጋ ጋር በተያያዘ በሚፈጠር የግጦሽ ሳር እጥረት ምክንያት በእንስሳቱ ላይ ለሚደርስ ጉዳት ካሳ በመክፈል የአርብቶ አደሩን የችግር ተጋላጭነት ለመቀነስ ያለመ ነው፡፡ ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ጋር በመተባበርም ከመጋቢት 2010 ዓ.ም አንስቶ በአምስት ሺህ አባወራዎች ላይም በሙከራ ደረጃ ተጀምሯል፡፡
ፕሮጀክቱን በባለቤትነት የሚመራው የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መለሰ አወቀ በበኩላቸው፤ አብዛኛው የክልሉ ነዋሪ በእንስሳት እርባታ ሥራ ላይ የተሰማራ አርብቶ አደር በመሆኑ ድርቅ በሚከሰትበት ወቅት የግጦሽ ሳር እጥረት በከብቶቹ ላይ የሚደርሰው ጉዳት ኑሮውን አስቸጋሪ እንዳደረገበት ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም የእንስሳት መድን ሽፋኑ የሳተላይት የአየር መረጃን መሰረት በማድረግ ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ የክልሉ አካባቢዎች የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አርብቶ አደሩ ከብቶቹ ሞተውበት ችግር ውስጥ ከመግባቱ በፊት ሊደረስለት እንደሚገባ በማመን ወደዚህ ሥራ መገባቱን የጠቆሙት አቶ መለሰ፤ የሳተላይት የአየር ትንበያ መረጃን መሰረት በማድረግ ድርቅ ሊከሰትባቸው ይችላል ተብለው በተለዩ አካባቢዎች የሚኖሩ አርብቶ አደሮች ድርቁ ተከስቶ ከብቶቻቸው ከመሞታቸውና ችግር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ለመኖ መግዣ የሚሆን ገንዘብ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ በዚህም በክልሉ ተግባራዊ የተደረገው የመድህን ሽፋን ቀደም ሲል ከነበሩት የመድን ዓይነቶች ችግሩ ከተከሰተና ጉዳት ከደረሰ በኋላ ከሚከፈል ካሳ የተለየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ካለፈው የመጋቢት ወር ጀምሮ በሙከራ ደረጃ ሲተገበር የቆየው የእንስሳት መድን ሽፋን መርሐ ግብር የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ፕሮጀክቱን በባለቤትነት የሚመራው የዓለም የምግብ ፕሮግራምና የመድን ድርጅቶች፣ የፋይናንስ ተቋማትና ሌሎችም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት ከዛሬ ጀምሮ በጅግጅጋ ከተማ በይፋ ሥራ መጀመሩ ታውቋል፡፡

ይበል ካሳ

 

Published in የእለቱ ዜና

አንዲት ትንሽዬ ከተማ ውስጥ የሚኖር አንድ አይነስውር ሰው ነበር። ይህ አይነስውር ሰው ምሽት ላይ ከከተማው መውጫ ላይ ወደሚገኘው ወንዝ እየሄደ ንፁህ አየር መቀበል ያዘወትር ነበር። ታዲያ በዛ በጨለማ ሲሄድና ሲመለስ በእጁ የበራ ፋኖስ ይዞ ነበር የሚንቀሳቀሰው። ይህን የበራ ፋኖስ ይዞ ንፁህ አየር የመቀበል ጉዳይ የሰርክ ተግባሩ አድርጎታል።
ከዕለታት በአንዱ ምሽት እንደልማዱ የበራ ፋኖሱን ይዞ በመንሸራሸር ላይ ሳለ ሶስት ወጣቶች እርስ በርስ ሲያልፉ ያገኙታል። አይነስውሩ በድቅድቅ ጨለማ በፋኖስ ብርሃን እየተመራ በመጓዙ ይገረሙና አይነስውር መሆኑን በመጠራጠር ያናግሩታል። እርሱም በጥያቄያቸው ተገርሞ በርግጥም ሲወለድ ጀምሮ አይነስውር መሆኑን ይነግራቸዋል።
«አንተ አይነስውር ከሆንክ እንዴት እንደሚያይ ሰው የበራ ፋኖስ ይዘህ ትዞራለህ?» ብለው ይስቁበታል፣ ይሳለቁበታል። ሰውዬውም በወጣቶቹ መሳቅና መሳለቅ ሳይበሳጭ በእርጋታ እንዲህ በማለት መለሰላቸው።
«ልክ ናችሁ፤ በርግጥም እኔ አይነስውር በመሆኔ አይኔ አያይም፤ ነገር ግን የፋኖሱ ብርሃን ይጠቅመኛል፤ ምክንያቱም በፋኖሱ ብርሃን እኔ በቀጥታ ባልጠቀምበትም በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቅሜ እጠቀምበታለሁ። ምክንያቱም ሰዎች በጨለማው ምክንያት ሳያዩኝ ሊገፈትሩኝ ይችላሉ። ከገፈተሩኝ በኋላ ከምናደድባቸውና ከማዝንባቸው ፋኖሱን ይዤ ባበራላቸው ሁለታችንም እንጠቀማለን» ብሏቸው ሄደ። ወጣቶቹም በሰውዬው ቅን አስተሳሰብ ተደነቁ። በአይነስውሩ ማፌዛቸው አሳፈራቸው። በርግጥም ከነርሱ የተሻለ ቅን ልብ ስላለው ከራሱ አልፎ ለሌሎች እየኖረ መሆኑ አስደነቃቸው። ከማየት ማስtዋል እንደሚበልጥ ተረዱ። ከዛን እለት ጀምሮ ህይወታቸውን ለሌሎች በማሰብና በቅንነት ለማሳለፍ ወሰኑ።
በርግጥም የምናየው በህሊናችን ሲሆን ማስተዋላችን የበዛ ይሆናል። ለሰዎች የምናደርገው በጎ ነገር በራሱ ተመልሶ በእጥፍ ይከፍለናል። ቅን ልቦች ሁልጊዜም የሚጠቅሙት ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡን እንደሆነ እንረዳለን።
አንዳንድ ጊዜ ማስተዋል ሲሳነን ነገሮችን የምናያቸው እራሳችን ለመረዳት በፈለግነው ልክ ይሆናል። አንዳንድ እውነታዎች ተዛብተው የሚተረጎሙት ለነገሮቹ በሰጠነው የፍላጎት ግመታ ሊሆን እንደሚችል ልብ ልንል ይገባል። እውነታው እኛ እንደፈለግነው ወይም ለምንፈልገው ጉዳይ ጋር ሳይገጣጠም ሲቀር ልንበሳጭ እንችላለን። ምክንያቱም እኛ የተረዳንበትና ነገሩ የተገለፀበት መንገድ የተለያያ ሊሆን ይችላልና። በተለይ ደግሞ ወጣቶች ስንሆን ነገሮችን በሰከነ መንፈስ የማየት እድላችን ሊጠብ ይችላል። ለዚህም ነው የአይነስውሩን እውነት ወጣቶቹ እራሳቸው በፈለጉትና በመሰላቸው መንገድ በመረዳታቸው የተሳሳቱት። መሳሳት በራሱ ውድቀት አይደለም፤ ከስህትት ተምሮ ወደተሻለ አስተሳሳብ መምጣት ይቻላልና። ከወጣቶቹ ታሪክ የተረዳነውም ይህንኑ ነው።
በወጣትነት ዕድሜ በርካታ ምርጫዎች ከፊታቸው ይደቀናሉ። አንዳንዶቹም በሕይታቸው ላይ ዘላቂ ተጽዕኖ ሊኖራቸው ይችላል። በአሁኑ ጊዜ የምናደርጋቸው አንዳንድ ውሳኔዎች የወደፊት ሕይወታችንን ሊያበላሹት ይችላሉ። በመሆኑም ካለፉ በኋላ ይቆጩናል። በአንፃሩ ደግሞ ጥንቃቄና ጥበብ የታከለባቸው ምርጫዎች አስደሳችና የተሳካ የሕይወት መስመር ያመላክቱናል ወይም ያደርሱናል። የዚህን ትክክለኛነት ለማየት በሕይወታችን የምናደርጋቸውን ምርጫዎች አመዛዝኖ በሚነግርን ህሊናዊ አይናችን ልናዳምጠው ይገባል።
የሀገራችን ወጣቶች የተሻለች ኢትዮጵያን ለማየት ብዙ የህይወት መስዋእትነት ከፍለዋል። ይህ መስዋእትነታቸው የታሪክ መዝገብ ከትቦት ይገኛል። አሁንም ብዙ ታሪክ የሰሩና ለመስራት የተዘጋጁ ወጣቶች አሉን። ወደፊት ታሪክ ለመስራት የሚያስብ ወጣት ደግሞ አኩሪ ታሪኮቹን ጠብቆ ለትውልድ በማስተላለፍ ረገድ የራሱን ገንቢ ሚና መጫወት ይገባዋል፡፡ እንደ ባለተራ ትውልድ የጀግኖች አባቶቹን አደራ ተቀብሎ የማስቀጠል ታሪካዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል።
ወጣቶች የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታውን ከኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ ጋር ለማስተሳሰር የሚያስችል አንድነት ሊኖራቸው ይገባል። ይህን አንድነት ለመፍጠር ደግሞ በሀገራዊ አስተሳሳቦች ላይ የጋራ ግንዛቤ ይዘው እንዲንቀሳቀሱ እድሉ ሊመቻችላቸው ይገባል።
ዛሬ ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ ወጣቶች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ውይይት አንደሚያደርጉ ይጠበቃል። ይህ ከሚፈጠሩት መልካም አድሎች መካከል ተቀዳሚው ነው። ከዚህ ውይይት የወጣቶች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ ለሀገር እድገት በሚኖራቸው አስተዋፅኦና በመሰል ጉዳዮች መግባባት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። በመመካከር የተሻለች ኢትዮጵያን መፍጠር እንችላለን። የዚህ ሁሉ ማጠንጠኛው ደግሞ አስተውሎት የተሞላበት አስተሳሰብን ማጎልበት ነው። ከቅርብ ጊዜ ታሪካችን የተረዳነው አስተውሎት በጎደለው ጉዟችን ብዙ ስህተቶችን ፈፅመናል። በቀላሉ ልንመልሳቸው የማንችላቸውን የህይወትና የንብረት ጥፋት አድርሰናል። ይህ ስህተት መሆኑን ካመን ከስህተት መማር ብልህነት በመሆኑ ዛሬ በአዲስ አስተሳሰብ ለኢትዮጵያችን ብልፅግና መስራት ይኖርብናል። አስተውሎ የሚራምድ ብዙ መንገድ ሊጓዝ ይችላልና።

Published in የእለቱ ዜና

የጤፍ ምርትን የማቀነባበር የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት መብት (ፓተንት) በአውሮፓው የኔዘርላንድ ኩባንያ ከአሥር ዓመት በፊት ተይዟል። ኢትዮጵያ የባለቤትነት መብቱ ያለአግባብ ተወስዶብኛል እያለች ስትጠይቅ ብትቆይም እስካሁን ጉዳዩ እልባት አላገኘም።

የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማርዮ እንደሚሉት፤ በጀርመን እና ሌሎች አምስት አገራት ውስጥ ጤፍ በዱቄት መልክ አዘጋጅቶ ወይም በዱቄቱ ኬክ ሰርቶ ለመሸጥ ተቀባይነት ያለው የጤፍ ብቸኛ የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤት የሆነው የኔዘርላንዱ ኩባንያ ነው።
‹‹ጤፍ ግሉቲን ከሚባል አሚኖ አሲድ ነፃ ነው›› የሚሉት ዶክተር መለሰ፣ ይህ የተፈጥሮ ይዘት ከጤና አንፃር ተፈላጊነቱ በዓለም ላይ መጨመሩን፣ ጤፍ በቀጣይ ዓመታት የሚኖረውን ተፈላጊነት በማሰብ ኢትዮጵያ በበላይነት ገበያውን ለመቆጣጠር ያላትን ዕድል ለመጠቀም የመብት ባለቤትነቷን መረከብ እንደሚኖርባት ያብራራሉ። ይህ ከሆነ በህጋዊ መንገድ ጤፍን ለአውሮፓ ገበያ ማቅረብ ይቻላል። ጤፍን በውድ ዋጋ ለዓለም ገበያ የማቅረብ ዕድል እንዲፈጠር፣ አርሶአደሮችም የበለጠ ለማምረት እንዲነሳሱ ማድረግ እንደሚያስችል ያብራራሉ፡፡ የባለቤትነት መብት ማግኘቱ ለአገርም ዕውቅና ያሰጣል ይላሉ፡፡
ድርጊቱ ከኢኮኖሚ ጉዳትም በላይ የማንነት ማጭበርበርን የሚያሳይ ክስተት የታከለበት ነው የሚሉት ዶክተር መለሰ፣ የባለቤትነቱን መብት ወደ ኢትዮጵያ ማስመለስ መቼም ቢሆን ችላ ሊባል እንደማይገባ ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ጊዜያዊ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤርሚያስ የማነብርሃን እንደሚገልጹት፣ በአሁኑ ወቅት የጤፍ ምርት በአምስት የአውሮፓ አገራት የሚታወቀው የኢትዮጵያ በሚል ሳይሆን በአንድ የኔዘርላንድ ኩባንያ በሚዘጋጅ የምግብ አይነት ነው። ይህ ስሙን የሚቀያይር ኩባንያ፣ በአውሮፓ አዕምሯዊ ንብረት (ፓተንት) ቢሮ በኩል በተወሰኑት የአውሮፓ አገራት የጤፍ ማቀነባበር መብትን አግኝቷል።
በቅድሚያ ኩባንያው በተጭበረበረ መንገድ ያገኘውን የባለቤትነት መብት ማሰረዝና ቀጥሎም ጤፍ የኢትዮጵያ መሆኑን ማስመዝገብ እንደሚገባ የሚገልጹት አቶ ኤርምያስ፣ ለዚህም ድርድርን፣ ህዝባዊ ዘመቻን እና የህግ አግባብን መጠቀም እንደሚገባ ያመለክታሉ።
‹‹የጤፍ ጀነቲክ ሃብት የተጠበቀበት ሁኔታ ደካማ ነው›› የሚሉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሳይንስ፣ መገናኛ እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው መለሰ ናቸው። ጉዳዩ መነሳት ከጀመረ ከአሥር ዓመታት ወዲህም ቢሆን ኢትዮጵያ ውጤታማ ተግባር አለማከናወኗን ይጠቁማሉ፡፡የውጭ ሀገሩ ኩባንያ በየአገራቱ የተሰጠው ፈቃድ በአንዳንዶቹ በኩል በሁለት ዓመታት ውስጥ ስለሚጠናቀቅ ማሳደስ እንደሚጠበቅ ይገልጻሉ።ይህ የጊዜ ገደብ ደግሞ ለመጠናቀቅ የሚቀሩት የተወሰኑ ወራት መሆናቸውን በመጥቀስም፣ ኩባንያው ፈቃዱን ከማሳደሱ በፊት ኢትዮጵያ የቤት ሥራዋን ማጠናቀቅ እንደሚገባት ያመላክታሉ።
‹‹የድርጅቱ የጤፍ ማቀነባበር የባለቤትነት መብት እንዲሰረዝ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ጥረት ቢደረግም ወጤቱ አዝጋሚ ነው›› የሚሉት ዶክተር መለሰ፣ ወደ ህግ አግባብ የመግባት አስፈላጊነትን ይጠቁማሉ፡፡ ኩባንያው ከአንዴም ሦስት ጊዜ ስሙን እየቀያየረ እና መብቴን ለሌላ ድርጅት ሸጫለሁ እያለ ማወናበዱ የመብት ጥያቄውን ውስብስብ እንዳደረገው ያመለክታሉ፡፡ አሁን በአገር አቀፍ ደረጃ መብቱን ለማስመለስ የሚደረገውን ጥረት እንዲከታተል የተቋቋመው ኮሚቴ ጉዳዩን በትኩረት ሊይዘው እንደሚገባም ያስገነዝባሉ።
እንደ ዶክተር መለሰ ማብራሪያ፤ በጤፍ የባለቤትነት መብት ላይ ኢትዮጵያ ያነሳቸውን ጥያቄ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ለማቅረብ ጥናት እየተደረገ ይገኛል። ለፍርድ ሂደቱ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ማሰባሰብ ይገባል። በተለይ በጤፍ እና በጤፍ ምርት ሂደቶች ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሁፎች እና ጥልቅ መረጃዎችን ማደራጀት ያስፈልጋል። ይህም በፍርድ ቤት አሸንፎ ህገወጥ መብቱን በማሰረዝ ኢትዮጵያን ባለመብት ለማድረግ ወሳኝ ነው።
አቶ ኤርሚያስም በዚህ የዶክተር መለሰ ሀሳብ ይስማማሉ። እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ጉዳዩ የህግ መፍትሄ ያስፈልገዋል። ኢትዮጵያም በድርድር፣ በህዝባዊ ዘመቻ እና በህግ መንገዶች ተጠቅማ መብቱን ለማግኘት ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። የድርድሩ ውጤት ብዙም አጥጋቢ ባይሆንም በዘመቻ መልክ በሰፊው ጤፍ የኢትዮጵያ መሆኑን ዓለም እንዲያውቀው ማድረግ ይገባታል። ያለፈውን እየወቀሱ ከመቀመጥ ጉዳዩ በህግ አግባብ እንዲፈታ ማድረግ ሁነኛው አማራጭ መሆን አለበት።
ጉዳዩን በህግ ፊት አቅርቦ በፍትህ መንገድ ፈቃዱን ማሰረዝ እንደሚገባ የሚናገሩት አቶ ኤርምያስ፣ ለኢትዮጵያ ጠበቃ ቀጥሮ ተከራክሮ በመርታት የኩባንያውን መብት ማሰረዝ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ።
አቶ ጌታቸው እንደሚገልጹት፤ የዓለም አቀፉ የአዕምሯዊ ንብረት ተቋም በኢትዮጵያ የጤፍ መብት ላይ በሚነሳው ጥያቄ ተመስርቶ ባቀረበው ሃሳብ መሰረት የጤፍ ምርት ባለቤትነትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከመጠየቅ አስቀድሞ በአገር ውስጥ ማስመዝገብ ይገባል። እስከ አሁን ጤፍ በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት አልተመዘገበም። የኩባንያውን ፈቃድ ለማሰረዝ ጥረት ከማድረግ አስቀድሞ በአገር ውስጥ ማስመዝገብ ያስፈልጋል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የዓለም አቀፍ ባለመብትነት እውቅና ማግኘት በብቸኝነት ምርቱን በተፈለገው መንገድ ለመሸጥ እና ለመጠቀም ፍቃድ እንደ ማግኘት ይቆጠራል። በኢትዮጵያ እና ሄልዝ ኤንድ ፐርፎርማንስ ፉድ ኢንተርናሽናል በሚባል የኔዘርላንድ ኩባንያ መካከል በተደረገ ስምምነት መሰረት ኩባንያው በኢትዮጵያ የጤፍ ዝርያዎች ላይ 12 ዓይነት የምርምር ሥራ እንዲያከናውን ፍቃድ ተሰጥቶት ነበር። ኩባንያው ከአራት ዓመታት በኋላ 'ኪሳራ ደርሶብኛል' በሚል ሥራውን ቢያቆምም፣ ከአውሮፓ የአዕምሯዊ ንብረት ጤፍን በዱቄት፣ በፓስታ፣ በብስኩት እና በሌሎች መልኩ አቀነባብሮ የማዘጋጀት እና የመነገድ መብት አግኝቷል።
በኔዘርላንድ፤ በብሪታኒያ፣ ጣሊያን፣ ቤልጅየም፣ ጀርመን መብቱን አግኝቶ እየተጠቀመበት ይገኛል። ኢትዮጵያ ይህን ህገወጥ መብት ለማሰረዝም በአገር አቀፍ ደረጃ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚመራ ኮሚቴ ያዋቀረች ሲሆን፤ በኮሚቴው ውስጥም የውጭ ጉዳይ፣ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ፅህፈት ቤት፣ የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት በአባልነት ከተካተቱት መካከል ይገኙበታል።
ዶክተር መለሰ የክስ ሂደቱን በተጠናቀረ መረጃ በተደገፈ ሥርዓት አከናውኖ መርታት ካልተቻለ ከጤፍ ምርት ጋር ተያይዞ የሚደርሰው ኢኮኖሚያዊ እና የማንነት ኪሳራ አገሪቷን ይጎዳታል ሲሉ ስጋታቸውን ይጠቁማሉ። በተለይ ጤፍ አቀነባብረው ለመላክ በርካታ ሃብት ሥራ ላይ ያዋሉ ዜጎችን ተስፋ እንደሚያጨልም በማመልከት መጠንቀቅ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡
አቶ ኤርሚያስ ጤፍን አቀነባብሮ የመጠቀም እና የመሸጥ መብትን ከአውሮፓው ኩባንያ ማስመለስ ካልተቻለ ጤፍን በእንጀራ መልክ እና በዱቄት መልክ ወደአውሮፓ የሚልኩ ኢትዮጵያውያን ተቀባይነት እንደማያገኙ በመጠቆም፣ ይህም በአገሪቷ ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራዎች እንዲደርሱ ያደርጋል ይላሉ።
እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ፤ ኩባንያው ባለቤትነት መብቱን በየአገራቱ ከማሳደሱ በፊት ኢትዮጵያ በአገሯ ጤፍን በመመዝገብ መረጃዎችን ይዛ በመገኘት መከራከር ትችላለች። ለዚህ ደግሞ የአገር ውስጥ ምዝገባው መጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ወደ አውሮፓም ሆነ ዓለም አቀፉ የአዕምሯዊ ንብረት በመሄድ የመብት ጥያቄ ለማቅረብ መሞከር ትርፉ ኪሳራ እንደሚሆን በመጠቆምም ቅድሚያ በሀገር ውስጥ ምዝገባው መካሄድ እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡  

 

ዜና ትንታኔ
ጌትነት ተስፋማርያም

 

 

 

 

Published in የእለቱ ዜና

በክፍሉ በበራፍ ሁለት ጥበቃዎች በቀኝና በግራ ተቀምጠዋል። ወለሉ ላይ ደግሞ ህጻናቱን የሚጠብቁ ሰዎች ካርቶን አንጥፈው ስማቸው እስኪጠራ ጋደም ብለው ይጠባበቃሉ። በአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የጨቅላ ህፃናት ህክምና ክፍል ውስጥ ትርምስምስ ያለ እንቅስቃሴ ይስተዋላል። ወደክፍሉ ሲገባ የታመቀው አየር እንኳን ለህጻናቱ ይቅርና አዋቂውን ይረብሻል። በተለይ ደግሞ የተለያዩ አልኮል ነክ የህክምና መስጫ ግብዓቶች ሽታ ሲጨመርበት አስም ለያዘውና በቀላሉ መተንፈስ ለማይችል ሰው አስቸጋሪ ነው። ክፍሉ ውስጥ ያሉት ህጻናት ይህን መተፋፈግ እንዴት እንደተቋቋሙት ለመመልከት መግባት ነበረብኝና ወደ ውስጥ ገባሁ። 

በክፍሉ በስተግራ በ«ካንጋሮ ስታይል» የሙቀት ህክምና የሚሰጥበት ክፍል አለ። በስተቀኝ ደግሞ የመተንፈስ ችግር ያለባቸው፣ ሙቀት የሚያስፈል ጋቸውና ያለጊዜያቸው የሚወለዱ ህጻናት የሚያርፉ በት ክፍል ይገኛል። የሙቀት ክፍሉ የሚሰጠውን አገልግሎት ለመመልከት ወደ ውስጥ ገባሁ። በአንድ አልጋ ላይ ሦስት ህፃናት ተኝተዋል። ባስ ሲልም በአንድ አልጋ ላይ አራት ህጻናት እንደሚተኙ ያገኘኋቸው ነርስ ነግረውኛል።
በጠባቧ ክፍል ውስጥ ያሉት የሙቀት መስጫ መሳሪያዎች ደግሞ ይበልጥ ክፍሉን አጨናንቀውታል። አማራጭ ባለመኖሩ በክፍሉ ከ40 እስከ 65 የሚደርሱ ህጻናትን እንደሚቆዩ በአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የጨቅላ ህፃናት አይሲዩ ዲፓርትመንት ኃላፊ ሲስተር ትዕግስት ደሪባ አረጋግጠውልኛል።
ሲስተር ትዕግስት እንደሚናገሩት፤ በሆስፒታሉ የቦታና መሳሪያ እጥረት እንዲሁም የአልጋ ውስንነት በመኖሩ ጨቅላ ህፃናትን በተገቢው መንገድ ማስተናገድ አልተቻለም። በተለይም በሙቀት መስጫ መሳሪያ እጥረት የተነሳ በአንድ አልጋ ላይ የተለያየ ህመም ያለባቸው ህጻናት ይተኛሉ። የመተንፈስ ችግር ያለባቸውንና ሙቀት የሚያስፈልጋቸው ህጻናትም በአንድ አልጋ ላይ በማስተኛት አንድ አይነት የሙቀት መጠን ይሰጣቸዋል። ይህ ደግሞ የጨቅላ ህጻናቱን የሞት ቁጥር እንዲጨምር መንስኤ ሆኗል።
«በጤና ህግ መሰረት በተለያዩ በሽታዎች የተያዙ ህጻናትን እንኳን በአንድ አልጋ በአንድ ክፍል ውስጥ ማስተናገድ ያስጠይቃል» የሚሉት ሲስተር ትዕግስት፤ ከችግሩ ግዝፈት የተነሳ በአንድ አልጋ ላይ አንድ የማሞቂያ መሳሪያ ተጠቅሞ ሦስት ህጻናት እንዲተኙ ተደርጓል። በ24 ሰዓት ውስጥ በሆስፒታሉ ያለጊዜያቸው የሚወለዱ ህጻናት ቁጥር እስከ 20 ይደርሳል። ከተለያዩ የህክምና ተቋማት ሙቀት ፍለጋ ወደሆስፒታሉ የሚመጡ ህፃናት ደግሞ በየቀኑ በአማካይ እስከ 70 እንደሚደርስ ይገልጻሉ። ስለዚህም ህጻናቱን ለማትረፍ ሲባል በተጨናነቀ ቦታ ማከሙ ግድ እንደሆነባቸው ያስረዳሉ።
‹‹በክፍሉ ያሉት አልጋዎች 32 ብቻ ናቸው። ህጻናቱን ለደቂቃ ህክምናውን ካላገኙ እንደሚሞቱ ይታወቃልና በአንድ ጊዜ ከ40እስከ 65 ልጆች በክፍሉ እንዲቆዩ ይደረጋል። ለአንዱ የሚያስፈልገው የሙቀት መጠንና ለሌላው የሚያስፈልገው የሙቀት መጠን መለያየቱ ቢታወቅም አማራጭ ባለመኖሩ በአንድነት እንዲጠቀሙም ይደረጋል›› ይላሉ ሲስተር ትዕግስት። አሰራሩ ህክምና ያገኙትንም ሆነ የማያገኙትን ህጻናት ለከፋ ጉዳት እየዳረጋቸው መሆኑ ግልጽ መሆኑን ያስረዳሉ። በተጨማሪም የባለሙያ አለመሟላት አስፈላጊውን አገልግሎት ለመስጠት እንዳላስቻለ የሚናገሩት ሲስተር ትዕግስት፤ በቂ ነርሶች መሟላት እንዳለባቸው ያሳስባሉ። የቅጥር ሁኔታው በደረጃ ሲቀመጥ ለሁለት ጨቅላ ህጻናት አንድ ነርስ ቢያስፈልግም በክፍሉ ያሉት ነርሶች ግን 6 ብቻ ናቸው። በአማካይ ለ65 ህጻናት እያገለገሉ ይገኛሉ። በመሆኑም ኮሌጁ በቂ የሰው ኃይል፤ ግብዓትና አስፈላጊው የህክምና ስታንዳርድ ለመሟላት አስቸኳይ ምላሽ ይሻል ይላሉ።
የሆስፒታሉ ፕሮቮስት ዶክተር ስለሺ ጋሩማ በበኩላቸው፤ በተጣበበ ቦታ ላይ ህክምናው እየተሰጠ መሆኑን አምነው ችግሩን ለማቃለል ከጤና ቢሮና ከአጋር አካላት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ያስረዳሉ። ነገር ግን በተቋሙ የመሳሪያ እጥረት አለ በሚለው አይስማሙም። በቂ የህክምና መሳሪያ ቢኖርም ቦታ ባለመኖሩ ተመላሽ በመሆኑ አገልግሎቱን በበቂ ሁኔታ መስጠት አለመቻሉን ያስረዳሉ። ነገር ግን ወደሌላ ህንፃ ለማዛወር በመታሰቡ በቂ የሙቀት መስጫ መሳሪያ እንዲኖር የሚያግዝ እንደሚሆን ይገልጻሉ። አዲስ ህንጻ እየተገነባ በመሆኑ እና ከሌሎቹ የህክምና ክፍሎች የተለየ ትኩረት በመሰጠቱ በሳምንታት ውስጥ ለህጻናቱ የተሻለ ክፍል እንደሚዘጋጅ ይናገራሉ።
የነርሶችን ጉዳይ በተመለከተም በውጭ አገራት ያለውን ደረጃ ማለትም ለአንድ ጨቅላ ህጻን ሦስት ነርስ መጠቀም ላይ ለመድረስ ትኩረት ሰጥተው በመስራት ላይ መሆናቸውን የሚናገሩት ዶክተር ስለሺ፤ በየጊዜው የተገልጋዩ ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ ችግሩ አዲሱ ህንጻ ውስጥ ቢገባ በቀላሉ እንደማይፈታ ይናገራሉ። ስለዚህ ቋሚ መፍትሄ ለማበጀት በየጊዜው የቦታም ሆነ የግብዓት እንዲሁም የነርሶችን ቁጥር ለማሳደግ ተጨማሪ ጥረት ይጠይቃል። መንግሥትም ተጨማሪ ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል።
ያለጊዜያቸው የተወለዱ ህጻናት በብዛት እንዲሞቱና የተጠቃሚዎች ቁጥር እንዲበራከት ያደረገው ዋነኛ ምክንያት የሙቀት ህክምናን የሚሰጡ ተቋማት በአካባቢው ያለመኖራቸው መሆኑን የሚያስረዱት ዶክተር ስለሺ፤ አሁን ላይ አገልግሎቱ በጤና ጣቢያ ደረጃ እንዲሰጥ ለማድረግ የህክምና መሳሪያ ከአጋር አካላት በመረከብ ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።
የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ዋቆ እንደሚሉት፤ ተገቢውን ሙቀት አለማግኘት ለጨቅላ ህጻናት ሞት ምክንያት በመሆን ሰፊውን ድርሻ ይይዛል። ስለዚህም ችግሩን መቅረፍ የሚቻለው በቂ መሳሪያዎች ሲኖሩና ቦታዎች ምቹ ሲሆኑ ነው። በመሆኑም በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የህክምና የመሳሪያ ችግር በተቻለ መጠን እንዲፈታ ዩኒሴፍ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁሟል።
በአገሪቱ በአማካይ በቀን29 ህጻናት የሚሞቱ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከልም ብዙውን ቁጥር የሚይዙት ካለጊዜያቸው የሚወለዱ ህጻናት መሆናቸውን ዩኒሴፍ ያወጣው መረጃ ያመላክታል። ለሞታቸው መንስኤ የሆነውም የህክምና መሳሪያ እጥረትና ለህጻናቱ ትኩረት አለመስጠት መሆኑንም ያስቀምጣል። 

 

ዜና ሐተታ
ጽጌረዳ ጫንያለው

 

 

 

Published in የእለቱ ዜና

አዲስ አበባ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶክተር) በቀጣይ ሳምንት ከባለሃብቶች እና ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ውይይት ለማድረግ ማቀዳቸውን የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ። 

በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ «የፍቅር እና የአንድነት ኪዳን» በሚል መሪ ሃሳብ ከ25ሺ ዜጎች ጋር ውይይት ያደርጋሉ።
የኢፌዴሪ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶክተር) ትናንት በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶክተር) ቃለመሃላ ከፈጸሙ ጀምሮ ከተለያዩ ክልሎች እና የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አካሂደዋል። ውይይቶቹ ተጠናክረው የሚቀጥሉ በመሆኑ በቀጣይ ሳምንት ከአገሪቷ የንግድ ማህበረሰብ ከተውጣጡ ዜጎች እና ባለሃብቶች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ላይ ያተኮረ ውይይት ያካሂዳሉ።
እንደ ዶክተር ነገሪ ገለጻ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከንግዱ ማህበረሰብ እና ከባለሃብቶች ጋር በሚያካሂዱት መድረክ የአገሪቷን የልማት እቅዶች በተቀናጀ መልኩ በማከናወን ወደተሻለ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ሰፊ ውይይት ይካሄድበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በተጨማሪ ዶክተር ነገሪ እንደገለጹት፣ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ የፍቅር እና የአንድነት ኪዳን በሚል መሪ ሃሳብ በሚዘጋጀው የወጣቶች መድረክ የፌዴራልና የክልል ኃላፊዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮችና ምሁራን፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ተወካዮች ተሳታፊ ናቸው። የመድረኩ አላማ የለውጥ መሰረት የሆነውን ህዝቡን ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ እንዲሰራ የሚያስችል እና ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል ያማከለ ነው።

ጌትነት ተስፋማርያም

 

Published in የእለቱ ዜና
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002832140
TodayToday984
YesterdayYesterday778
This_WeekThis_Week9860
This_MonthThis_Month32320
All_DaysAll_Days2832140

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።