Items filtered by date: Friday, 13 April 2018

የኢትዮጵያ የሉዓላዊነት ታሪክ ዘመናትን ያስቆጠረ፣ በከፍታ ላይ የቆመ፣ ከሩቅ ከፍ ብሎ የሚታይና ሙሉ ክብርን የተጐናጸፈ ነው፡፡ ሀገራችን ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ የቆየችው ጠላት ተኝቶላትና የሚተነኩሳት አጥታ ሳይሆን ጥቃትን የማይቀበል ደም ያላቸው የሳተና ልጆች እናት በመሆኗ ነው፡፡ ሉዓላዊነት ለኢትዮጵያውያን የክብርና የማንነት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን መተኪያ የሌላት ህይወትን በፈቃደኝነት የሚገብሩላት አድማስ የማይገድበው አስተሳሰብ ነው፡፡
የታሪክ መዛግብት ወደኋላ መለስ ብለው ቢፈተሹ ሀገራችን የሌላን አገር መሬት ለመቀራመትና ሉዓላዊነትን ለመጋፋት አንድ ጊዜም እንኳ ሙከራ እንዳላደረገች ያስረዳል፡፡ ታሪካችን በአብዛኛው የጦርነት አሻራ ያረፈበት ቢሆንም የተከስተው ግን አንድም ሉዓላዊነታችንን ላለማስደፈር በሌላም በኩል ጭቆናን አሽቀንጥሮ ለመጣልና የሁሉም ዜጐች ቤት የሆነች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ መሆኑ ከማንም ሊሰወር አይችልም፡፡
የምዕተ ዓመታት ታሪካችን እንደሚያሳየውና ወዳጅም ጠላትም ጠንቅቆ እንደሚረዳው የሌላን የማይፈልጉ፣ ክብራቸውን ለድርድር የማያቀርቡና ባርነትን የሚሸከም ጫንቃ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ድንበራቸውን ተሻግሮ ሊወራቸው የመጣን ጠላት በአንድ ልብ ታግለውና በአንድ ጉድጓድ ተቀብረው የኢትዮጵያውያን ልብም ሆነ መሬት ወራሪን እንደማይቀበል ደጋግመው አስመስክረዋል፡፡
አድዋ፣መተማ፣ ካራማራም ሆነ ባድመ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት መጋፋት እሳት መጨበጥ መሆኑን ጠላት የተማረባቸው ምርጥ ታሪካዊ አውዶች ናቸው፡፡ «በበጐ ከሆነ ለቁም ነገር ጉዳይ ጐረቤት ወዳድ ነን እንግዳ ተቀባይ፣ ግን ሀገራችንን ክፉ የሚያስባትን ቆራጥ ነን ልጆቿ አንወድም ጥቃትን» የሚለው የዘፈን ስንኝ ኢትዮጵያውያን ለወዳጆቻቸው ፍቅር፣ ሉዓላዊነታቸውን ለሚጋፋ ኃይል ደግሞ ቆንጥር መሆናቸውን በሚገባ የሚያስረዳ ነው፡፡
የድንበር መገፋት ብቻ ሳይሆን የማንቀበለውን አስተሳሰብ በላያችን ላይ ለመጫን የሚደረግ ሙከራ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ሉዓላዊነትን የመጋፋትና ፍጹም ተቀባይነት የሌው ነውረኛ ተግባር ነው፡፡ ድህነታችንን አምነን ከዚህ ለመውጣት በምናደርገው ጥረት በአንዲት ጠጠር እንኳ የሚደግፈንን ኃይል አመስግነን የምንቀበለው ክብራችንን ሲጠብቅና ሉዓላዊነታችንን ሲያከብር ብቻ እንደሆነም ተደጋግሞ የታየ እውነታ ነው፡፡ ይሁንና ይህ ሀቅ ተሰውሮባቸው ይሁን በእብሪት ተነሳስተው ይህንን እውነታ ለመቀበል የሚቸገሩ አካላት ዛሬም እንዳሉ እየተመለከትን ነው፡፡
ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በአሜሪካ ህግ መወሰኛ ም/ቤት የተረቀቀውና የፀደቀው HR 128 የተባለው ህግ ነው፡፡ የኢትዮጵያውያንን ባህሪ፣ ማንነትና ታሪክ የዘነጋው ይሄ ህግ ለኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያውያን የበለጠ እንቆረቆራለን የሚል መልዕክት ሊስተላልፍ የሞከረ የዘመኑ ታላቅ ፌዝ ነው፡፡ ይሄን ህግ ያረቀቁም ሆነ ያፀደቁ አካላት ቆም ብለው እንዲያስቡት የሚያስፈልገው ጉዳይ ለዜጐቻችን ከኛ ከኢትዮጵያውያን የበለጠ ተቆርቋሪ እንደሌለና ሀገራችን በውስጥ ጉዳይዋ ማንም ገብቶ እንዲፈተፍት የማይፈቅድ መንግሥትና ህዝቦች ያሏት ሀገር መሆኗን ነው፡፡ ከአንጀት ካለቀሱ ዕንባ አይገድም እንደሚባለው እነዚህ አካላት እውነት ለሀገራችንና ለዜጐቻችን የሚቆረቆሩ ከሆነ ህዝብና መንግሥት ድህነትን ለማስወገድ በሚያደርጉት ጥረት ላይ አንዲትም ግራም ብትሆን ድጋፋቸውን ይለግሱና ምስጋናችንን ይቀበሉ፡፡
ከዚህ ውጪ ግን በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት ሽፋን የኢትዮጵያውያንን እጅ ለመጠምዘዝ መሞከር ከንቱ መሆኑን ተረዱ እንላለን፡፡ ይህ አልዋጥ ብሏችሁ የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች አከባበር ለኢትዮጵያውያን ለማስተማር የምትዳዱ ከሆነም ሀገራችን የዴሞክራሲ ሀሁ የሆነውን የገዳ ሥርዓት ለዓለም ያበረከተች ታላቅ ሀገር መሆኗን ደግመን ልናስታውሳችሁ እንወዳለን፡፡
አሁን በቅርቡ እንኳን ሀገራችንን ከገባችበት ትልቅ የፖለቲካ ቀውስ ለማውጣት ኢትዮጵያውያን የተጓዙበትን መንገድና የተካሄደው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ያለምንም የውጭ ኃይል ጣልቃ ገብነት ለራሳቸው ችግር ራሳቸው መድኃኒት የሚቀምሙና የሚፈወሱ ታላቅ ህዝብና ሀገር መሆናቸውን ያመላከተ ነው፡፡
ስለሆነም ዛሬም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመጋፋትና ከእኛ በላይ እናውቅላችኋለን በሚል የተሳሳተ እሳቤ በከንቱ የምትደክሙ አካላት ለሀገራችንም ሆነ ለህዝባችን ከእኛ ከኢትዮጵያውያን የበለጠ የሚቆረቆርም ሆነ የሚሠራ ኃይል እንደሌለ ተገንዝባችሁ ከፍሬ አልባ ተግባራችሁ ተቆጠቡ እንላለን፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ክብሯንና ሉአላዊነቷን ለዘላለም የማያስደፍሩ የኩሩ ህዝብ ሀገር ናትና፡፡

Published in የእለቱ ዜና

አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ በሊበን ጩቃላ ወረዳ ሊበን ጋዱላ ቀበሌ መጋቢት 29ቀን 2010ዓ.ም ሌሊት የደረሰው የጎርፍ አደጋ በ25 ሄክታር ማሣ ላይ የለማና ከ550ሺ ዶላር በላይ ገቢ የሚያስገኝ ለወጪ ንግድ የደረሰ የተለያየ ዝርያ ያለው የፋሶሊያ ምርት በጎርፍ አደጋ ሙሉ ለሙሉ መውደሙን የኢትዮ ፍሎራ ድርጅት ባለቤት ገለጹ፡፡

የድርጅቱ ባለቤት አቶ ፀጋዬ አበበ አደጋው የተከሰተው እርሻው በሚገኝበት ቦታ በዘነበ ዝናብ ሳይሆን፣ ከአምቦ፣ በቾና ሆለታ ከፍታማ ቦታዎች ወይም ጩቃላ ተራራ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የተከሰተ ጎርፍ የእርሻ ማሳውን ሰብሮ በመግባቱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አቶ ፀጋዬ ድርጅቱ ለጎርፍ መከላከያ ከሰራው አራት ሜትር ከፍታ በላይ ሰብሮ ወደማሳው የገባው ጎርፍ እየለማ ካለው 70 ሄክታር ማሣ ውስጥ 25ሄክታሩን ሙሉ ለሙሉ ያወደመው መሆኑን ገልፀው፤ ከማሳው ላይ በየሳምንቱ እስከ መቶ ሺ ኪሎግራም ትኩስ ምርት ወደውጭ ለመላክ በዝግጅት ላይ እንደነበር፤ ለብልሽት የተዳረገው ምርትም ከ550ሺ ዶላር በላይ እንደሚገመትና በአሁኑ ጊዜ ጎርፉ ቢቆምም ይዞት የመጣው ደለል በማሳው ላይ መተኛቱን አመልክተዋል፡፡
በአካባቢው የጎርፍ አደጋ ሲከሰት የመጀመሪያ እንዳልሆነና የአሁኑን ለየት የሚያደርገው በማይጠበቅ በት ወቅት መሆኑን የገለፁት አቶ ፀጋዬ፤ በ2009 ዓ.ም. ጳጉሜ ወር ላይ የእርሳቸውንና ሉላ ፍሩት የተባለውን ድርጅት ጨምሮ በአንድ መቶ ሄክታር ላይ የለማውን የወጪ ንግድ አትክልት ሙሉ ለሙሉ ማውደሙን ተናግረዋል፡፡
ቦታውን ለአትክልት ምርት ከመንግሥት በኢንቨስ ትመንት ሲወስዱ የጎርፍ መከላከያ እንደሚሰራላቸው ቃል እንደተገባላቸውና የመከላከያውን ሥራ ለመስራት ጅምር እንቅስቃሴ ቢኖርም እርሻቸውን ከአደጋ መታደግ እንዳልተቻለ፣ የአዋሽ ወንዝ በደለል በመሞላቱ ጎርፍ የመከላከል አቅም እንደሌለውና ድርጅታቸው ጎርፉን ለመከላከል የራሱን ጥረት ቢያደርግም በድርጅቱ አቅም መፍትሄ ማምጣት እንደማይታሰብ አክለው ገልጸዋል፡፡
የጎርፍ አደጋው በተከሰተበት ቦታ ተገኝተው ችግሩን ያዩት የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸርና ግብርና ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አዱኛ ደበላ እንደገለፁት፣ የጎርፍ አደጋው ጉዳት ያስከተለው ክረምቱ ከመድረሱ በፊት ከወዲሁ መፍትሄ ለመስጠት ከኦሮሚያ መስኖ ልማት ኤጀንሲና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር ቀጠሮ ይዘው ባለቡት ወቅት ነው፡፡
ዶክተር አዱኛ ደበላ አደጋው በዚህ ወቅት የጠበቁት እንዳልሆነና በአዋሽ ተፋሰስ ላይ ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ መግባባት ላይ መደረሱን፣ በዕቅድ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
የአዋሽ ተፋሰስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ግዛው የጎርፍ አደጋውን አሳሳቢነት ሲገልፁ፡- አምና ከፍተኛ በሚባል ደረጃ የጎርፍ አደጋው በአትክልት ልማት ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ ችግሩን በጊዜያዊነት ለመከላከል ውሃው ወደ ውስጥ እንዲሰርግና ባለበት እንዲቆይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ውሃ ስጋት መሆን የለበትም ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ውሃ በሀብትነት ጥቅም ላይ የሚውልበት ዝርዝር ጥናት የያዘ የተቀናጀ የጎርፍ መከላከል ጥናት በአማካሪ ድርጅቶች በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ከቆቃ በላይ የአዋሽ ወንዝን ተከትለው የሚገኙ ወረዳዎችን ባማከለ የሚካሄደው ጥናት ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያስገኝ፣ አሁን የደረሰውን አደጋ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የአጭር ጊዜ መፍትሄ እንደሚወሰዱም ገልጸዋል፡፡
የችግሩ አሳሳቢነት እየታወቀ አፋጣኝ መፍትሄ ያልተሰጠበትን ምክንያት አቶ ጌታቸው ሲያብራሩ ተፋሰሱ ሰፊ እንደሆነና ባለው የበጀት አቅም ሁሉንም ማዳረስ እንደማይቻል፣ ቅድሚያ በሚሰጣቸው አካባቢዎች ላይ ትኩረት ተሰጠቶ በመሰራት ላይ በመሆኑ መዘግየቶች መከሰታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዱላ ሻንቆ የጎርፍ አደጋን ቅፅበታዊ ዝናብ የጎርፍ አደጋ ያስከትላል፡፡ለአጭር ሰዓት የዘነበ ዝናብ ፍጥነቱም አጭር ይሆናል፡፡ ችግሩ የደረሰበት አካባቢም ከዚህ ጋር በተያያዘ የተፈጠረ ነው፡፡ የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች ያልተቋረጠ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸውና ኤጀንሲው በየጊዜው የሚሰጠውን መረጃም መከታተል እንደሚጠበ ቅባቸው አስገንዝበ ዋል፡፡

ለምለም መንግሥቱ

Published in የእለቱ ዜና

አዲስ አበባ፡- በሀገሪቱ ከአምስት እስከ 17 ዓመት የዕድሜ ክልል በሚገኙ ዘጠኝ ሚሊዮን ልጆች ከአቅም በላይ ሥራ እንዲሠሩ በመገደዳቸው ምክንያት ለጉልበት ብዝበዛ መዳረጋቸውን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ ይፋ አደረገ።

በሀገሪቱ ከአምስት እስከ 17 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ልጆች ቁጥር 37 ሚሊዮን እንደሚገመት የገለጸው መረጃው፤ 19 ሚሊዮን የሚሆኑት ልጆች በተለያየ ሥራ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙና ከቤት ውጪ ገቢ በማስገኘት ሥራ ላይ የሚሳተፉት 24 ነጥብ 2 በመቶ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡
ጥናቱ ትናንት ይፋ በተደረገበት ወቅት የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ዳይሬክተር አቶ ተሾመ አድኖ፤ ዓለም አቀፉ የልጆች የሥራ ስምሪት ስታንዳርድ ከአምስት ዓመት እስከ 11 ያሉ ሕፃናት ሥራ እንዲሠሩ አይፈቅድም። ሆኖም በሀገሪቱ በዚህ የዕድሜ እርከን ውስጥ ያሉ ልጆች ሰፊ ሽፋን ይይዛሉ።
ዕድሜው እየጨመረ ሲሄድ የሥራ ጫናው ቢቀንስም አገሪቱ ብዙ መሥራት ያለባት ተግባር አለ የሚሉት አቶ ተሾመ፤ ልጆች ከአንድ ሰዓት በላይ መሥራት እንደሌለባቸው፣ ሥራ የሚሠሩ ከሆነም ምቹ ሁኔታ ሊፈጠርላቸው እንደሚገባ፣ ሥራው በራሱ አደገኛ መሆን እንደሌለበትና ከባድ መሳሪያ መጠቀም እንደሌለባቸው ጥናቱም እንደ መፍትሔ እንደሚያስቀምጥ አስረድተዋል።
እንደ አቶ ተሾመ ገለጻ፤ በክልል ደረጃ አደገኛ ሥራ ይሠራባቸዋል ተብለው የተለዩት አፋር፣ ሱማሌ፣ ኦሮሚያና ሌሎች ክልሎች በየደረጃው ይቀመጣሉ። ስለሆነም በዚህ ደረጃ የልጆች የሥራ ስምሪት 95 በመቶ የሚደርሰው በገጠር አካባቢ በእርሻ ሥራ ላይ የሚሰማሩትን ይይዛል። በቅጥር ደግሞ 2ነጥብ 1 በመቶ ይሸፍናል። ይህ የሚያመለክተው በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚኖረው የጉልበት ብዝበዛ በተለይ በቤት ውስጥ የሚደረገው ጫና ከፍ ያለ መሆኑን ነው። በዚህም በሀገሪቱ ጉልበታቸው ብዝበዛ ከሚደርስባቸው ዘጠኝ ሚሊዮን ውስጥ 52 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው ተረጋግጧል።

ጽጌረዳ ጫንያለው

 

Published in የእለቱ ዜና

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ላላት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት መጠናከር ትኩረት ሰጥታ እንደምትሰራ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ባለፈው ዓመት ከ855ሚሊዮን 422ሺ ዶላር በላይ ገቢ ያስገኘ የወጪ ምርት ለጎረቤት አገራት መሸጡን፣ የውጭ ባለሃብቶች ባለፉት ዓመታት በ473 የኢንቨስትመንት ሥራዎች መስክ መሰማራታቸውን፣ 13ሺ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያንም የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልጿል፡፡ 

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም ትናንት በጽህፈት ቤታቸው ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት በቋንቋ፣ በባህልና ድንበር መተሳሰራቸው ብቻ ሳይሆን ሰፊ የገበያ መዳረሻ ናቸው፡፡ይህ በመሆኑም ለረጅም ጊዜ በፖለቲካ መስክ አተኩሮ የቆየው የጎረቤት አገራት ግንኙነት በኢኮኖሚ መስክ የጋራ ጥቅም ላይ ተመስርቶ የበለጠ እንዲተሳሰር ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል፡፡
የአገሪቷ የገቢና የወጪ ንግድ የሚስተናገደው በጎረቤት አገሮች ወደብ መሆኑን ለአብነት የጅቡቲና ሱዳን ወደቦችን ጥቅም ላይ መዋል የተናገሩት ቃል አቀባዩ፤ሌሎች የወደብ አማራጮችንም ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ቃል አቀባዩ ለአገሪቱ ሰላምና ዕድገት የጎረቤት አገራት ቁልፍ ሚና እንዳላቸው፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ግንኙነት ይበልጥ እንደምታጠናክር፤ ከአካባቢው አገራት ጋር የኢኮኖሚ ውህደት ለማምጣት የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን የማጣጣም እንዲሁም ህጋዊ የድንበር ንግድ የማበረታታት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ መለስ እንዳሉት፤ ወቅታዊ የኢኮኖሚ ትስስሩ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና ቱሪዝም መስክ የላቀ እንዲሆን የመሰረተ ልማት አበረታች ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም በመንገድ፣ በባቡርና በወደብ አጠቃቀም የተጠናከረ ግንኙነት መፍጠር ተችሏል፡፡ የመሰረተ ልማት ትስስሩ አበረታች ቢሆንም የሰላምና ደህንነቱ ሁኔታ በሚፈለገው ደረጃ አለመሆኑ ለኢኮኖሚ ግንኙነት መጠናከር እንቅፋት ስለሚሆን መንግሥት ከጎረቤት አገራት ጋር በጥምረት ይሰራል፡፡

አዲሱ ገረመው

 

Published in የእለቱ ዜና

. በበጀት ዓመቱ የወባ ስርጭት በ17 በመቶ ቀንሷል

 

አዲስ አበባ፡- በሀገሪቱ በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመቀነስና የዘርፉ ባለሙያዎች ከትምህርት ቤት ይዘውት የሚወጡትን እውቀትና ክህሎት በማጎልበት ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ገለጸ፡፡ 

54ኛው የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ጉባዔ እና ዓለም አቀፍ የጤና አውደ ርዕይ ትናንት በሚሌኒየም አዳራሽ በተከፈተበት ወቅት የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ገመችስ ማሞ እንደተናገሩት፤ በሀገሪቱ በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመቀነስና የዘርፉ ባለሙያዎች ከትምህርት ቤት ይዘውት የሚወጡትን እውቀትና ክህሎት ከወቅቱ ቴክኖሎጂ ጋር በማዘመን ዕውቀታቸውን እንዲያጎለብቱት በማድረግ ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ ነው፡፡በዘርፉ በየጊዜው አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እየተገኙ በመሆኑ ባለሙያዎች ብቃታቸውን ከወቅቱ ጋር እንዲያሳድጉ በማድረግ ውጤታማ ሥራዎችን ሰርቷል፡፡
በሀገሪቱ ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የህክምና ትምህርት ተቋማት ቁጥር ከአስር እጥፍ በላይ አድጓል፡፡ በመንግሥት ብቻ ተይዞ የነበረው አገልግሎትም ወደ ግሉ ዘርፍ ተስፋፍቷል፡፡ ትምህርት ቤቶች የሚቀበሏቸውና የሚያስመር ቋቸው ተማሪዎች ቁጥር ጨምሯል ያሉት ዶክተር ገመችስ፤ ለህብረተሰቡ ጥራት ያለውና በሥነ-ምግባር የተሞላ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት የበለጠ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ገመችስ ለህክምና አገልግሎት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እጥረት በተለይም የህይወት አድን መድኃኒቶች በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ከገበያው እየጠፉና በተቃራኒው የሰውን ህይወት የሚጎዱ አልኮል መጠጦችና አደንዛዥ ዕፆች መስፋፋት በጤናው ዘርፍ ላይ የተጋረጡ ተግዳሮቶች በመሆናቸው ችግሩን ለመቀነስ የማህበሩ አባላት እንዲሁም መንግሥት በትጋት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃን በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ ወባ በወረርሽን መልክ እንዳይከሰትና ባለፉት አሥርት ዓመታት በተሰሩ ሥራዎች እድሉን ከ70 እስከ 80 በመቶ መቀነስ የተቻለ ሲሆን፤ በዚህ ዓመትም የወባ ስርጭት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ17 በመቶ መቀነስ መቻሉንና ይህም በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የተሰሩ ሥራዎች ውጤት መሆኑን ገልፀዋል፡፡በዚህም በመበረታታት በ239 ወረዳዎች የወባ ማጥፊያ ዘመቻ እስከመታወጅ ደርሷል፡፡ይህም በ2030 ወባን ለማጥፋትና ወባ የህብረተሰብ የጤና ችግር ወደማይሆንበት ደረጃ ለመድረስ ምቹ ሁኔታ መኖሩን አመላካች ነው ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል በወባ ምክንያት የብዙ ዜጎች ህይወት መጥፋቱን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ የወባ በሽታ ያለባቸውን ሰዎች ፈልጎ ለማግኘት የተዘረጋው አሰራር አበረታች ውጤት ማምጣቱንና ጉበት ውስጥ ያለው የፕላዝሞዲየም ህዋስን ፈልጎ በማከም ወባን ለማጥፋት ለሚደረገው ርብርብ ሀኪሞችና የሙያ ማህበራት አባላት ኃላፊነታቸ ውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
‹‹ጥራት ለህክምና›› በሚል መሪ ሃሳብ ለተከታታይ ሦስት ቀናት የሚካሄደው አውደ ርዕይ በህክምና ትምህርት ጥራት፣ በጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ችግር፣ በዘርፉ ያሉ ማነቆዎች፣ የህክምና ግብዓቶች እጥረትና በሀገር ውስጥና በውጭ ባሉ የዘርፉ ተሞክሮዎች ላይ የሚመክር ሲሆን፤ በአውደ ርዕይው 80 የተለያዩ መድኃኒትና የህክምና ግብዓት አምራቾች፣ አስመጪዎችና አከፋፋዮች ይሳተፋሉ፡፡

ዑመር እንድሪስ

 

Published in የእለቱ ዜና

አዲስ አበባ፡- በፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ የመድኃኒት ስርጭት አገልግሎት ክፍተት እንዳይኖር በቴክኖሎጂ በታገዘ የመረጃ ልውውጥ ዘዴ እየሰራ መሆኑን የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ ፡፡

የኤጀንሲው ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን ሞገስ የመድኃኒት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ከጤና ተቋማት ጋር ተናብቦ መስራትን አስመልክ ተው በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለፁት፣ ሐኪሞች፣ የፋርማሲና የተለያዩ ባለሙያዎች የተካተቱበት 127 አባላትን የያዘ ቡድን «ቫይበር ግሩፕ» እንዲሁም «በኢሜይል» ድረገፅ አማካኝነት ቅርንጫፉ ከሚያደርገው የመረጃ ልውውጥ በተጨማሪ በጋራ መድረክ ላይ በውይይት ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ ይገኛል፡፡ሰፊ አገልግሎት ከሚሰጡ ትላልቅ ሆስፒታሎች ጋር የበለጠ ለማጠናከርም በበጀት ዓመቱ ትኩረት አድርጓል፡፡
እንደ አቶ ሙሉቀን ማብራሪያ ቅርንጫፉ ከዋናው መስሪያ ቤት ጋር በየሁለት ወሩ በሚካሄድ መድረክ ላይ ስለአቅርቦቱ ይነጋገራል፡፡ እንደአስፈላ ጊነቱም በስልክ ያሳውቃል፡፡ የጤና ተቋማት የመድኃኒት ፍላጎትም መረጃ ሰብስቦ ያቀርባል፡፡ በዚሁ መሠረትም የ2011ዓ.ም. የመድኃኒት አቅርቦት ፍላጎትን አስቀድሞ ጠይቋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ካለፉት ጊዜያት የተሻለ ሥራ መሠራቱን የጠቆሙት አቶ ሙሉቀን በበጀት ዓመቱ በመደበኛ ግዥ408ሚሊዮን፣በእርዳታ387ሚሊዮን መድኃኒት በቅርንጫፉ ተሰራጭቷል፡፡
ቅርንጫፉ ለደንበኞች የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻልና ከዋናው መስሪያቤት ጋርም የተቀላጠፈ ግንኙነት እንዲኖረው ከሠራተኞች ጋር ግምገማ በማድረግ ክፍተቶቹ እንዲታረሙ፣ጠንካራ ጎኖች እንዲጎለብቱ መግባባት ላይ መደረሱንም አቶ ሙሉቀን አመልክተዋል፡፡
አቶ ሙሉቀን አያይዘውም የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ በኤጀንሲው ሥር የመድኃኒት ስርጭት ከሚያከናውኑ 20 ቅርንጫፎች መካከል አንዱ መሆኑን፣ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተያይዞ ግዢ ለመፈፀም ችግር መኖሩን ገልፀዋል፡፡
በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የፋርማሲ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ብዙአየሁ ወልደህፃን በበኩላቸው ቅርንጫፉ በተዘረጋው የመረጃ ልውውጥ ዘዴ ያለውን የመድኃኒት ክምችት በማሳወቅ ለሚሰጡት የህክምና አገልግሎት እያገዛቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የመረጃ ልውውጡ መጠናከሩ አንዱ ቅርንጫፍ የሌለው ከሌላ ቅርንጫፍ ለመጠቀም የሚያስችል አሰራር እንዲፈጠር ማገዙን የተናገሩት አቶ ብዙአየሁ፤ በሆስፒታሉ ሊታዘዙ የሚገባቸው መድኃኒቶች ፣ለህክምናና ለቤተሙከራ የሚያገለግሉ ግብአቶችን ጭምር በየ15ቀኑ በማቅረብ ያለውንና የሌለውን አስቀድመው የሚያውቁበት አሰራር መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡
በአንዳንድ የመድኃኒት አቅርቦቶች ላይ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ እጥረት እንደሚያጋጥም የጠቆሙት አቶ ብዙአየሁ በአሁኑ ጊዜ ለደም ግፊት፣ ለልብ፣ ለእንቅርት፣ ለቀዶ ጥገና የሚውል ጓንት፣ለስኳርና ለደም ማቅጠን የሚውሉ መድኃኒቶች እጥረት መኖሩን አመልክተዋል፡፡ አንዳንዶቹ በግዥ ሂደት ላይ እንደሆኑ መረጃው እንዳላቸውም ገልፀዋል፡፡

ለምለም መንግሥቱ

 

Published in የእለቱ ዜና

ለምግብነት የሚውሉ የእንስሳት ተዋጽኦ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ሌሎች ሰብሎች አመራረት፣ ቅንብር፣ ስርጭትና ለተጠቃሚ የሚደርስበትን ሂደት ጤናማና ደህንነቱ የተጠበቀ ማድረግ ተገቢ ቢሆንም በሀገር ደረጃ ይህን ሊያስገድድና ሊያረጋግጥ የሚችል የምግብ ፖሊሲ፣ የአፈጻጸም መመሪያና ደንብ አለመኖር ችግሮችን እያስከተለ መሆኑን የዘርፉ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ 

የምግብ ፖሊሲ አለመኖር ሀገሪቱ ማግኘት ያለባትን የውጭ ምንዛሬ ከማስቀረቱ ባሻገር አምራቾች ከምርቶቻቸው አኳያ ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም እንዳያገኙ አድርጓል የሚሉም አሉ፡፡ በሀገር ደረጃ የምግብ ደህንነት ፖሊሲ አለመኖር ምን ችግሮችን አስከትሏል?
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር፣ የሦስተኛ ዲግሪ ዕጩና የስነ-ምግብ ተመራማሪ አድማሱ ፈንታ እንደሚሉት፤ የምግብ ፖሊሲ በሀገር ደረጃ አለመኖር ለምግብነት መዋል የሚገባቸውና የማይገባቸው ምግቦች እንዳይለዩ ከማድረጉ ባሻገር ምርቶች ካላቸው ንጥረ ምግብና ከሚሰጡት ጥቅም አኳያ ዋጋ እንዳያወጡ አድርጓል፡፡ ይህም በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ሸማቹ ምርቱን በዓይኑ በማየት ብቻ እንዲገዛ እያደረገ ሲሆን፤ አምራቾች ለሚያቀርቡት ምግብ ፍትሐዊ ዋጋ እንዳያወጡ ከማድረጉ ባሻገር ተጠቃሚዎች ካለምንም መስፈርት እንዲሸምቱ ያስገድዳል፡፡
በሀገር ደረጃ የትኛውም ዓይነትና በየትኛውም የጥራት ደረጃ ላይ ያለ ምርት ከነጉድለቱ ገበያ ላይ እየቀረበ መሆኑ በተጠቃሚ ጤና ላይ ከሚያደርሰው ችግር ባሻገር ሀገሪቱ እየሠራችበት ያለውን የምግብ ዋስትና የሚጎዳ ነው፡፡ የምግብ ዋስትና ፕሮግራሙ ጥራትና ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ ማቅረብ እንደሚገባ ያስቀምጣል የሚሉት መምህር አድማሱ፤ ከኢኮኖሚያዊ ጥቅም አንጻር በወጪ ንግዱ ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ የበረታ ነው፡፡ ለአብነት በበርበሬ ላይ አልፎ አልፎ የሚከሰት ‹‹አፍላቶክሲን›› ምርቱ በዓለም ገበያ ተቀባይነት ሲያሳጣና አምራቾችን ለኪሳራ ሲዳርግ ይስተዋላል፡፡ ይህም የምግብ ደህንነት ፖሊሲ አለመኖር ዋናው ችግር አርሶ አደሩ የምግብን ደህንነት በሚያበላሹና በሚጎዱ ነገሮች ላይ በቂ ግንዛቤ እንዳያገኝ ያደርጋል ይላሉ፡፡
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምግብ ሳይንስ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር፣ መምህርና የስነ-ምግብ ተመራማሪ ዶክተር ይሁኔ አየለ፤ በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ የህዝብ ብዛት እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በምግብ ላይ ቅየጣዎች ወይም ባዕድ ነገሮች እንዲቀላቀሉ እየተደረገ ነው፡፡ እንዲሁም ለጤና ጎጂ የሆኑ መጠጦች ካለ ማንም ከልካይ ሁሉም እንዲጠቀማቸው እየተዋወቁ ነው፡፡ በተለይ በሽልማት መልክ የሚተላለፉ ማስታወቂያዎች በርካቶች ‹‹ዕድሌን ልሞክር›› በማለት ስለሚጠቀሟቸው ያለባቸውን በሽታ የሚያባባስ ኬሚካል እየወሰዱ ነው፡፡ ይህ የፖሊሲ ማዕቀፍ አለመኖር ችግር ነው ይላሉ፡፡
በተጨማሪም ከውጭ የሚገቡም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምግቦች ላይ እንደ መድሃኒት በማስተዋወቅ ለመሸጥ የሚደረግ ዘመቻ አለ፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ምግብ በመድሃኒት ስም ሲቸበቸብ ይታያል፡፡ ሰው ወደ ትክክለኛ ጤና ጣቢያ በመሄድ ጤንነቱን መከታተልና የባለሙያ ምክር መከተል ሲገባው ለመሸጥ ሲባል መድሃኒት ናቸው፤ ለተለያዩ በሽታዎች ፈውስ ይሆናሉ፤ በማለት የተሳሳተ መንገድ እንዲከተል ሲደረግ ይስተዋላል የሚሉት ዶክተር ይሁኔ፤ ለአብነት ከዚህ ቀደም የውጭ ድርጅቶች ምግብን በመድሃኒት ስም ሲሸጡ ነበር፡፡ በሀገሪቱ ሞሪንጋ፣ ጥቁር አዝሙድ ወዘተ... ለሦስት መቶ በሽታዎች መድሃኒት ነው እየተባሉ ሽያጭ ላይ የሚውሉትም ትክክል እንዳልሆኑ ይገልጻሉ፡፡
እንደ ዶክተር ይሁኔ ገለጻ፤ ምግብ ያድናል ተብሎ የማስተዋወቅ ዘመቻ ሊደረግበት አይገባም፡፡ ምግብ ሰዎች በበሽታ እንዳይጠቁና ጤንነታቸውን እንዲጠብቁ እንደሚያደርግ ግልጽ ሆኖ ሳለ ለዚህ በሽታ ፈውስ ይሆናል እየተባለ ሊሸጥ አይገባም፡፡ እነዚህንና የመሳሰሉትን ችግሮች እልባት ሊሰጥ የሚችል ፖሊሲ ማውጣት ካልተቻለ ችግሩ እየተወሳሰበና በተለያየ መልኩ ደህንነታቸው ያልተጠበቁ ምግቦች የሚቀርቡበት አማራጭ አየሰፋ ይሄዳል፡፡
በኢትዮጵያ ሆላንድ ንግድ ትብብር ለግብርና እድገት ፕሮግራም የቅመማ ቅመም፣ ሃመልማላማና ማዕዛማ ዘይቶች ተመራማሪና አማካሪ አቶ አዲሱ አለማየሁ ሲያብራሩ፤ የምግብ ፖሊሲ አለመኖር ከምግብ አመራረት ጀምሮ ለተጠቃሚ እስከሚቀርብ ድረስ ባለው ሂደት ችግሮችን እያስከተለ ነው፡፡ በቅመማ ቅመም ዘርፍ በርበሬ በጥንቃቄ ጉድለት ምክንያት ለአፍላቶክሲን ሲጋለጥ ይስተዋላል፡፡ አርሶ አደሩን እንዲሁም ነጋዴውን የሚገድበው የምግብ ደህንነት ፖሊሲ፣ ህግና መመሪያ ባለመኖሩ የሚሸጠው ምርት ሚዛን እንዲያነሳ ውሃ የሚያርከፈክፍበትና ለፈንገስ እንዲጋለጥ የሚያደርግበት ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ ይህ በሰዎች ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል፡፡ በርበሬም ሆነ ሌሎች በጥንቃቄ ጉድለት በአፍላቶክሲ የተመረዙ ምግቦች ለሕፃናት መቀንጨርና ለጉበት ካንሰር ምክንያቶች ናቸው፡፡ ይህም የማህበረሰቡ ጤና በአግባቡ እንዳይጠበቅ እያደረገ ነው፡፡
የምግብ ፖሊሲ አለመኖር ምርቶች ጥራታቸው እንዲጠበቅ ባለማድረጉ በማህበራዊ ህይወት ቀውስ ከማስከተሉ ባሻገር ወደ ውጭ በሚላኩ ምርቶች ላይ የተለያዩ ሀገራት ገደቦችን እንዲጥሉና ምርቱ ጥራቱ ተፈትሾ የሚያልፍበት ውጣ ውረድ(ቢሮክራሲ) አሰልቺ ሆኗል፡፡ ይህም የሀገር ውስጥ ላኪዎች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው እንዳይሸጡና አጠቃላይ ወደ ውጭ የሚላከው ምርት በተወሰነ መጠን እንዲቀንስ አድርጓል ያሉት ተመራማሪው፤ አርሶ አደሩ የሚያመርተውን ምርት በአግባቡ እንዳይሸጥ እያደረገ ከመሆኑ ባሻገር ተወዳዳሪነት በሀገር ደረጃም እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ አርሶ አደሮች ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለማምረት ከፍተኛ ወጪ አውጥተውና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው ቢያመርቱም፤ ጥራቱን የጠበቀው ካልጠበቀው ጋር በተመሳሳይ ዋጋ የሚሸጥበት ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ ይህም ተጠቃሚነታቸውን ዝቅ አድርጎታል ብለዋል፡፡
‹‹በሀገሪቱ በምግብ ራስን መቻል የሚለው ሃሳብ ቅድሚያ የሚሰጠው ቢሆንም የምግብ ጤናማነት ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ምግብ የሚወሰደው ጤንነትን ለመጠበቅ እንጂ ርሃብን ለማስታገስ ብቻ አይደለም፡፡ የተወሰደው ምግብ ጤንነትን የሚጎዳ ከሆነ ምግብ አለመውሰድ ሊያስከትለው ከሚችለው ችግር የተለየ አይደለም፡፡ ይህም የፖሊሰው ክፍተት ያመጣው ችግር ነው፡፡
«በሀገሪቱ የምግብ ፖሊሲ አለመኖር የአውሮፓ ህብረትና ሌሎች ሀገራት ከኢትዮጵያ በሚገቡ የቅመማ ቅመም ምርቶች ላይ አዲስ መመሪያና ደንብ እንዲያወጡ አድርጓል፡፡ ይህም በዘርፉ ያሉ ባለሀብቶች መመሪያውን አሟልተው ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ፍትሕዊ ያልሆነ የንግድ ውድድር ላይ እንዲገቡ፣ በሌሎች ሀገር አምራቾች በቀላሉ እንዲበለጡና ተጎጂ እንዲሆኑም አድርጓል፡፡›› በማለት ተመራማሪው ያብራራሉ፡፡
በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስነ-ምግብ ተመራማሪ ወይዘሮ አረጋሽ ሳሙኤል፤ ምግቦች ቢታሸጉ ከምን እንደተሠሩ፣ የያዙት ንጥረ-ነገር፣ የተመረቱበትና የሚበላሹበት ጊዜ በትክክል ይቀመጣል፡፡ በሀገሪቱ ሁኔታ ይህን የሚያስገድድ ነገር ስለሌለ አገልግሎት ሰጭዎችም ሆኑ በምግብ ንግድ ዘርፍ ያሉ ነጋዴዎች ምንነታቸው ያልታወቁ ምርቶችን ያቀርባሉ፡፡ በርካታ ጊዜ ሰዎች በአንድ አጋጣሚ በተመገቡት ምግብ ከፍተኛ የጤና መታወክ ሲደርስባቸውና ለሞት ሲዳረጉ ይስተዋላል፡፡ ይህ የሚሆነው በምግብ ደህንነት ዙሪያ ወጥ የሆነ ፖሊሲ፣ መመሪያና ደንብ ባለመኖሩ መሆኑን ያብራራሉ፡፡
ዓለም አቀፍ የምግብ ፖሊሲ ደህንነት ደረጃ (ስታንዳርድ)፤ ሁሉም ምግቦች ከአመራረታቸው ጀምሮ በገበያ ላይ እስኪቀርቡ ድረስ የሄዱበት የአመራረት ሂደት፣ የያዙት ንጥረ-ነገር፣ የተመረቱበትና የሚበላሽበት ጊዜ፣ የምርቱ የጥራት ደረጃ በትክክል እንዲቀመጡ ያዝዛል፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ ራሱን የቻለ ፖሊሲ፣ ህግና መመሪያ ያልተወጣለት በመሆኑ ምግብ በዘፈቀደ ለተጠቃሚዎች የሚቀርብበት ሁኔታ ተስፋፍቶ እንደሚገኝ ባለሙያዋ ያስረዳሉ፡፡
እንደ አቶ አዲሱ ገለጻ፤ ቅመማ ቅመምም ሆኑ ሌሎች ምግቦች የሰው ልጅ የሚመገቧቸው በመሆናቸው ጤናማነታቸውና ደህንነታቸው ሊረጋገጥ፤ ምንም ዓይነት አሉታዊ ተጽዕኖ አለማድረሳቸውም መታመን ይኖርበታል፡፡ ምግቦች በአጭር ጊዜም ሆነ በረጂም ጊዜ የጤና እንከን ማስከተልም አይገባቸውም፡፡ ለአብነት በቅመማ ቅመም ዘርፍ የምግብ ደህንነት ፖሊሲ የሚያስፈልገው ዋናው ምክንያት ከሚመረተው ምርት ውስጥ 85 በመቶ ቅመማ ቅመም ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል በመሆኑ ደህንነቱ ሊረጋገጥ ስለሚገባ ነው፡፡ እንዲሁም 15 በመቶው ወደ ውጭ ሀገር የሚላክ ቢሆንም ሀገራት ለዜጎቻቸው ጤንነት ሲሉ ወደ ሀገራቸው ስለሚገቡ ምርቶች ጥራትን የተመለከተ የራሳቸው መስፈርት ህግና ደንቦች ያላቸው በመሆኑ ችግሩ መፍትሔ ካልተሰጠው በወጪ ንግዱ ተወዳዳሪነት ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ እየበረታ ይሄዳል፡፡
እንደ ዶክተር ይሁኔ ገለጻ፤ ለሀገር ውስጥ ገበያ መቅረብ ያለባቸው የምርቶች የጥራት ሁኔታ አለመታወቅና ለወጪ ንግዱ ብቻ ትኩረት መሰጠቱ የጥራት ጉድለት ያለባቸው ምርቶች ሀገር ውስጥ ገበያ ላይ እንዲቀርቡ እያደረገ ነው፡፡ በመሆኑም ሀገር ውስጥ የምግብ ደህንነትን የሚያረጋግጥ ፖሊሲ ማውጣትና መተግበር ካልቻለ በወጪ ንግዱ ላይ ከሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዕኖ ባሻገር ለዜጎች ተስማሚና ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ ለማቅረብ ተግዳሮቱ የበረታ ይሆናል፡፡

ዜና ትንታኔ
ዑመር እንድሪስ

 

 

Published in የእለቱ ዜና

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002832139
TodayToday983
YesterdayYesterday778
This_WeekThis_Week9859
This_MonthThis_Month32319
All_DaysAll_Days2832139

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።