Items filtered by date: Wednesday, 06 December 2017

የአሜሪካ ኮንግረስ ኤች አር 128 ለማፅደቅ ያሳለፈው ውሳኔ የአሜሪካ መንግሥት አቋም አለመሆኑና ኢትዮጵያ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ የማያሳይ መሆኑን የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ የአሜሪካ ኮንግረስ ኤች አር 128 ለማፅደቅ ያሳለፈው ውሳኔ የአሜሪካን አቋም የሚያንፀባርቅ አይደለም፡፡ ከመግለጫነት ባለፈ ምንም ዓይነት ህጋዊ ትርጉምና አንዳች ተጽዕኖ የለውም፤ የሁለቱም አገራት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

«የአሜሪካ መንግሥት የበርካታ ተቋማት ድምር ውጤት፤ እነዚህ ተቋማት ደግሞ በራሳቸው ነፃም ተደጋጋፊም በመሆናቸው የውሳኔ ሃሳቡ የተወሰኑ የኮንግረሱ አባላት
አቋምና አስተሳሰብ እንጂ የአሜሪካ መንግሥት አይደለም» የሚሉት አቶ መለስ፤ ይህም ህጋዊ ተፈፃሚነት የሌለው በመሆኑም በአገራቱ ግንኙነት ላይ ምንም ዓይነት አሉታዊ ተፅዕኖ እንደማይፈጥር አስረድተዋል፡፡

እንደ ቃል አቀባዩ ማብራሪያ፤ መግለጫው በመሬት ላይ ያሉና የተለወጡ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያላስገባ እና አፍራሽ ነው፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ዴሞክራሲው እንዲጠናከርና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እስረኞችን የመፍታት፣ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የማካሄድ፣ ከፓርቲዎች ጋር ምክክር የማድረግ ሥራ እየተሰራ ባለበት ወቅት ኮንግረሱ ሰነዱን ለማፅደቅ ያሳለፈው ውሳኔ ወቅታዊ ያልሆነ እና ያልተገባ ነው፡፡

«የኮንግረሱ አባላት የፈለጉትን ሃሳብ የመስጠት መብት ቢኖራቸውም ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ነፃ አገርና ህዝብ ያላት እንደመሆንዋ የሚመጡ ነገሮች እንደፈለጉ ሊጭኑብን እንደማይችሉ ሊታወቅ ይገባል» የሚሉት ቃል አቀባዩ፤ መንግሥት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚፈታውም ኮንግረሱን ለማስደስት ሳይሆን የህዝብ ጥያቄ መመለስ ስለሚገባው መሆኑን ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ትኩረት እንደምትሰጥና በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ፀጥታን በማስፈን ረገድ በጋራ መስራቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል አመልክተው፤ የአሜሪካ ኮንግረስም ይህንን በጎ ግንኙነት ከግምት በማስገባት አካሄዱን ማስተካከል እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡

በመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መሃመድ ሰይድ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት አስቀድሞም ቢሆን በአገሪቱ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ባለበት ወቅት የኮንግረሱ አባላት ይህንን ውሳኔ ማስተላለፋቸው ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ « በህገ መንግሥቱ ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው የሰብዓዊ መብት ማክበርና ማስከበር ዴሞክራሲን መገንባት የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ህዝቡ ባነሳው ጥያቄ መሰረት መንግሥት ችግሮችን ለይቶ ተግባራዊ እርምጃ ወስዷል፤ ይህ በሆነበት ሁኔታ ውሳኔው በኛ በኩል ተቀባይነት አይኖረውም» ብለዋል፡፡

የውሳኔ ሃሳቡ አንዳንድ ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ ከሚፈልጉ አባላት የመነጨ መሆኑን አቶ መሃመድ ገልፀው ፤ በሁለቱ አገራት መካከል በጣም የቆየና ጥሩ የሚባል በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነታቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ በተለይም በፀረ ሽብር እንቅስቃሴ በኩል በጋራ የጀመሩት ዘመቻ ቀጣይነት እንዲኖረው የሁለትም መንግሥታት ፍላጎት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደዚህ ዓይነት የአገርን ሉዓላዊነትና ጥቅም የሚነካ ጉዳይን በሚመለከት በእውነታ ላይ የተመሰረተ ዘገባ ማቅረብ እንደሚገባቸው አቶ መሃመድ አሳስበው፤ በተለይም ከጋዜጠኝነት ሥነምግባር ውጭ የሆኑ አሉባልታዎችና አፍራሽ አስተሳሰቦችን በጥንቃቄ በመፈተሽ ለህዝብ መረጃ ማስተላለፍ እንደሚ ገባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የአሜሪካ ኮንግረስ ከትናንት በስቲያ ኤች አር 128 የተባለ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት እንዲከበርና ሁሉን አቀፍ አስተዳደር እንዲኖር ለመደገፍ ያለመ ነው ያለውን የውሳኔ ሃሳብ አቅርቦ በአብላጫ ድምጽ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ በአገሪቱ ውስጥ በተጨባጭ መሬት ላይ ያለውን ለውጥ በማገናዘብና በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ግምት ውስጥ በማስገባት ይህን የተዛባ ውሳኔ አስመልክቶ ተቃውሟቸውን ያሰሙ የአሜሪካ የኮንግረስ፣ የሴኔት እና የአስፈፃሚው አካል አባላትን አመስግኗል፡፡

Published in የእለቱ ዜና

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829522
TodayToday1152
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7242
This_MonthThis_Month29702
All_DaysAll_Days2829522

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።