የጥቁር ገበያው ጥቁር አሻራ Featured

18 Apr 2018

ጥቁር_ገበያው አቅሙን በማፈርጠም በአገሪቱ ኢኮኖሚና በዜጎች ህይወት ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ነው፡፡ ጥቁር ገበያው መደበኛውን የፋይናንስ ሥርዓት በማዳከም ህገ ወጥ የገንዘብ ገበያ እንዲስፋፋ እያደረገ መሆኑን ምሁራን ይናገራሉ፡፡

በትናንትናው ዕለት ንግድ ባንኮች አንድ የአሜሪካ ዶላር በ27 ነጥብ 23 ብር፣ ዩሮን በ33 ነጥብ 47 ብር ፣ የእንግሊዝ ፓውንድን በ36.58 ብር ሲገዙ፤ እነዚህ ገንዘቦች በጥቁር ገበያው አንድ ዶላር በ34 ብር፣ ዩሮ በ41 ነጥብ 60 ብር፣ ፓውንድ 47 ነጥብ 80 ብር መገዛታቸው ታውቋል፡፡
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የግብር እና ጉምሩክ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ለሚሳ ባይሳ፤ እየተባባሰ የመጣው ጥቁር ገበያ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ውድቀት እንደሚያስከትል ይገልፃሉ። ጥቁር ገበያው ብዙ ችግር ባለበት የግብር እና የጉምሩክ አሰራር ላይ የበለጠ ጫና በማሳደር ከፍተኛ ተግዳሮት ሆኗል ይላሉ። ችግሩ ከውጭ በሚገቡ መድኃኒቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል፤ ዜጎች ከአገር ውጪ ሄደው እንዳይታከሙ በማድረግ በህይወት ላይ አደጋን ደቅኗል ብለዋል፡፡
የነቀምት ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አድማሱ ቴሶ፤ጥቁር ገበያው ኮንትሮባንድ እንዲስፋፋ፣ የአገር ውስጥ ቁጠባ እንዲዳከም፣ የአገር ውስጥ ልማት እንዲጓተት፣ ህገወጥነት እንዲስፋፋ እና የገንዘብ ተቋማትን በማዳከም የአገሪቱን ኢኮኖሚ እየገዘገዘ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ዶክተር አድማሱ እንደሚሉት፤ በአገሪቱ ጥቁር ገበያው በከፍተኛ ደረጃ እንዲንር የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ የብር የመግዛት አቅም መቀነሱ አንዱ ምክንያት ነው፡፡ በምጣኔ ሀብት ሳይንስ ዜጎች ለውጭ ሸቀጥና ገንዘብ ያላቸውን ፍላጎት ቀንሰው ለአገር ውስጥ ምርትና ገንዘብ ትኩረት እንዲሰጡ የብር የመግዛት አቅም እንዲዳከም ይደረጋል፡፡ ሆኖም ግን የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ባላገናዘበ መልኩ የብር የመግዛት አቅም እንዲዳከም መደረጉ ጥቁር ገበያው እንዲጠናከርና በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና እንዲያሳድር አድርጎታል።
የምጣኔ ሀብትና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ፤ የጥቁር ገበያ መጠናከር ለኢኮኖሚው መውደቅ ዋና ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ። የብር የመግዛት አቅምን በአንድ ጊዜ በ15 በመቶ ማውረድ አሉታዊ የኢኮኖሚያዊ ንዝረቱ በእያንዳንዱ የዜጋ ኪስ እንዲሰማ አድርጓል፡፡
እሳቸው እንደሚሉት ለፋብሪካዎች ግብዓትና መለዋወጫ፣ ለአዳዲሶቹ ደግሞ መሳሪያዎችን ለመግዛት የውጭ ምንዛሪ ያስፈልጋል፡፡ ፋብሪካዎቹ ይህንን ከመንግሥት ስለማያገኙ ወደ ጥቁር ገበያ ይሄዳሉ። በዚህም የተነሳ ምርታቸው ውድ ይሆናል። ምርት ሲወደድ ደግሞ የዜጎች ኑሮ በከፍተኛ ጫና ውስጥ ይወድቃል።
የብር የመግዛት አቅም ሲወርድና ኑሮ ሲወደድ ዜጎች በመንግሥት ላይ እምነት በማጣት ገንዘባቸውን በባንክ ማስቀመጡን እንደሚተው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ይገልፃሉ፡፡ በምትኩም ህንፃ የመገንባት፣ ወርቅና የውጭ አገር ገንዘቦችን የመግዛት አማራጮችን ይወስዳሉ፡፡ይህም በባንኮች የገንዘብ እጥረት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ የአገሪቱ ገንዘብ ስለማይንቀሳቀስ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ድቀትን ያስከትላል። ህገ ወጥነትን በማስፋፋት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ያቃውሳል፡፡
ከአገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑት በአገልግሎት ዘርፍ መሰማራታቸውን ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ጠቁመው፣ የዘርፉ ተዋናዮች በቀጥታና በተዘዋዋሪ የውጭ ምንዛሪ ጥገኛ ናቸው ብለዋል። በመደበኛው ሥርዓት የውጭ ምንዛሪ ካለገኙ የጥቁር ገበያ ተዋናይ በመሆን ገንዘቡ ወደ ባንክ እንዳይገባ በማድረግ ኢ-መደበኛ አካሄድ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ አስረድተዋል፡፡ ጥቁር ገበያው እያደገ ሲሄድ መደበኛው የኢኮኖሚ ሥርዓት እየፈረሰ እንደሚሄድ አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ የማይመረቱ መድኃኒትን የመሳሰሉ ሸቀጦችን ከውጭ ለማስገባት እንደምትገደድ ጠቁመው ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የአገር ውስጥ ምርትና ባህርይ የሚፈለገውን ምንዛሪ የሚያገኝ አለመሆኑን ዶክተር ቆስጠንጢኖስ አስገንዝበዋል፡፡ የተለያዩ ምርቶችን በብዛት ማቅረብ አለመቻሉ ከብር የመግዛት አቅም ጋር ተዳምሮ በፊት ተሽጦ ይገኝ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ማሳጣቱን ይናገራሉ፡፡ የውጭ ምንዛሪና ፍላጎቱ ባለመጣጣሙ ህገ ወጦች ብቻ ሳይሆኑ ህጋዊ ነጋዴዎችም ወደ ጥቁር ገበያው እንዲያመሩ አድርጓል፡፡
ፖለቲካዊ ችግሮችም ለጥቁር ገበያው መስፋፋት ምክንያት መሆናቸውን ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ያመላክታሉ። በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ከመንግሥት ጋር ኩርፊያ ውስጥ በመግባታቸው በባንኮች ይልኩ የነበረውን ዶላር ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ ማድረጋቸውን ይጠቁማሉ።
የመንግሥት የፊስካልና የፋይናንስ ፖሊሲ የሚመራበት መንገድ ትክክል አለመሆኑንም በምክንያትነት ያነሳሉ። መንግሥት የሚያገኘው የውጭ ምንዛሪና ለመስራት የሚያቅደው አለመጣጣሙ፤ ዜጎች በውጭ ምንዛሪ የሚፈልጓቸውን መሰረታዊ ነገሮች ሳያሟሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን መያዝ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ባንኮች ጥቁር ገበያውን ለማሽመድመድ በጥናት ላይ የተመሰረተ ስልት ነድፈው ተቀናጅተው አለመስራታቸው ለጥቁር ገበያ መጠናከር ዕድል ፈጥሮለታል።
ዶክተር ለሚሳ፤ በበኩላቸው መንግሥት የጥቁር ገበያውንና የባንክን የምንዛሪ መጠን ማቀራረብ አለመቻሉ፣ በህገ ወጦች ላይ አስተማሪ እርምጃ አለመውሰዱ፣ ዶላር በሚያሸሹ ባለስልጣናት ላይ አጣርቶ እርምጃ አለመውሰዱ ለችግሩ ምክንያት መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ የዓለም አቀፍ ለጋሾች ድጋፍ መቀነስ፣ የምትገኘውን ዶላር በኃላፊነት አለመጠቀም ለጥቁር ገበያው መስፋፋት መንስዔ መሆኑን ያብራራሉ።
ኢህአዴግ አገሪቱን ከመቆጣጠሩ በፊት አንድ የአሜሪካን ዶላር በሁለት ነጥብ 07 ብር፤ እንዲሁም እ.አ.አ በ1992 አንድ ዶላር በ አምስት ብር ይመነዘር እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። ከመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ጀምሮ እስካሁን ድረስ የብርን የመግዛት አቅም በተለያዩ ዓመታት በሳንቲም ደረጃ እየቀነሰ እንዲመጣ መደረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በ1993 ዓ.ም አንድ የአሜሪካ ዶላር በአምስት የኢትዮጵያ ብር ይመነዘር ነበር፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት የውጭ ንግዱን ለማጠናከርና ለማበረታታት የብር የመግዛት አቅም በ15 በመቶ እንዲቀንስ ሲደረግ፤ ከሰባት ዓመት በፊት የብር የመግዛት አቅም በ20 በመቶ እንዲቀንስ መደረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በእነዚህ ዓመታት ታዲያ ጥቁር ገበያው በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋና እየተጠናከረ መምጣቱ ነው የሚገለፀው፡፡
ለችግሩ አፋጣኝ እርምጃ ካልተሰጠ ጥቁር ገበያው ህገ ወጥ የገንዘብ ገበያን በማስፋፋት የፋይናንስ ተቋማትን ያዳክማል፡፡ ተጨማሪ የብር የመግዛት አቅም የመቀነስ እርምጃንም ሊያስከትል ይችላል፡፡ ኢንዱስትሪዎች እንዲዘጉ፣ ባለሀብቶች ተስፋ እንዲቆርጡ፣ የመንግሥት ትላልቅ ፕሮጀክቶች እንዲጓተቱና እንዲቆሙ ያደርጋል፡፡ መደበኛውን ሥርዓት በማዳከም የኢኮኖሚውን ውድቀት በማፋጠን የአገሪቱን ዕድገት ያዳክማል፡፡

ዜና ትንታኔ
አጎናፍር ገዛኸኝ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829490
TodayToday1120
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7210
This_MonthThis_Month29670
All_DaysAll_Days2829490

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።