መንግሥትና ባለሀብቱ - በአዲስ ምዕራፍ Featured

18 Apr 2018

የሸራተን አዲስ ሆቴል ግቢ ከወትሮው በተለየ ደምቋል፡፡ በርካታ ሰዎችም ከመኪና እየወረዱ ወደ ሆቴሉ እየገቡ ነው፡፡ የሆቴሉ ሠራተኞች ለእንግዶቻቸው ደማቅ አቀባበል ማድረጉን ተያይዘውታል፡፡ ተጋባዡ እንግዳ የጥሪ ካርዱን እያሳየ ወደ ውስጥ ሲዘልቅ እኛ ደግሞ የሚመለከተው አካል ጋር ሄደን ስማችንን አስፈልገን በማግኘት ወደ አዳራሹ ገባን። በአዳራሹ ከመላ አገሪቱ የተውጣጡ ባለሀብቶችና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በአዳራሹ ታድመዋል፡፡ 

ከባለሀብቶች ጋር ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ የያዙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ አዳራሹ ሲገቡ እንግዶቹ ሞቅ ባለ ጭብጨባ ተቀበሏቸው። የአገር ውስጥ ባለሀብቱንና የንግዱን ማህበረሰብ በመወከል ኢንጂነር መላኩ ይዘዘው ንግግር አደረጉ፡፡


የአገሪቱ የንግድ ስርዓት ከፍተኛ አደጋ እንደተጋረጠበት በመጠቆም ንግግራቸውን የጀመሩት ኢንጂነር መላኩ ከችግሮቹ መካከል ደግሞ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከፍተኛውን ቦታ እንደሚይዝ አስምረውበታል፡፡
የወጪ ንግዱን በማሳደግ ፍላጎትን ለመሙላት ቢሰራም የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትና ግኝቱ አለመመጣጠኑን ኢንጂነር ይዘዘው አስረድተዋል፡፡ ፍላጎቱ 15 ቢሊዮን ዶላር ቢደርስም ግኝቱ ከ 6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር አለመብለጡን ነው የጠቆሙት፡፡


እንደ ኢንጂነሩ ገለጻ የሚገኘውም የውጭ ምንዛሪ ቢሆን ፍትሐዊ አጠቃቀም ባለመኖሩ አሁን ላይ ለመድኃኒት መግዢያ እንኳን እየጠፋ ነው፡፡ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ከፍተኛ የሰራተኛ ቁጥር ያላቸው ፋብሪካዎችም የመዘጋት አደጋ ተደቅኖባቸዋል፡፡ ከፍተኛ እጥረት እንዳለበት የሚገለጸው የውጭ ምንዛሪ በጥቁር ገበያ በስፋት ይስተዋላል፤ ከአገርም እየወጣ ይገኛል።


አንዳንድ የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተጠያቂነትን ተላብሰው እያገለገሉ ነው ብሎ ለመናገር እንደሚከብድ ኢንጂነር መላኩ ገልፀዋል፡፡ በተለይም በመሬት አቅርቦት፣ በኃይል፣ በቴሌኮም፣ በገቢዎችና ጉምሩክ፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ እንዲሁም በፍትህ ዘርፍ ኢ-ፍትሀዊ አሰራር በመስፈኑ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እያሽመደመደው ይገኛል ብለዋል፡፡


ሌሎች የመድረኩ ተሳታፊዎችም ሊፈቱ የሚገቡ ያሏቸውን ጥያቄዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል፡፡ የእንጦጦ እደ ጥበብ ተቋም ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቤተልሄም ብርሃነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለሀብቱ በአገሩ ጉዳይ እንደሚያገባው በማመን የውይይት መድረኩ እንዲዘጋጅ ማድረጋቸውን አድንቀዋል፡፡ ድርጅታቸው የኤች አይ ቪ ኤድስ/ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ በእንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን በፀበል ቦታ ያሉ ችግረኛ ሴቶችን በመሰብሰብ የተለያዩ የዕደ ጥበብ ሥራዎችን በማሰራት ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አሁን የተፈጠረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራቸውን እየተፈታተነው እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
‹‹መንግሥት የወጪ ንግዱን ደግፌያለሁ ቢልም ሥራው በተግባር የሚታይ አይደለም፤ በዚህ የተነሳ ደግሞ የእርሳቸውን ድርጅት ጨምሮ በርካቶች ከሥራ እየወጡ ነው›› በማለት ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲበጅ አሳስበዋል፡፡ ድርጅታቸው ለአገርና ለወገን የሚጠቅም ሥራ እየሰራ ቢሆንም ለማስፋፊያ የሚሆን መሬት ጠይቀው አራት ዓመት ሙሉ ያለምንም መልስ እየተመላለሱ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡


ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከተሳታፊዎቹ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመፍታት ባለሀብቱ የበኩሉን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ ‹‹እናንተ ካልረዳችሁን ችግሩ ምናልባትም ለሚቀጥሉት 15 እና 20 ዓመታት ሊቀጥል ይችላል። ይህ የኢትዮጵያ ብቻ ችግር አይደለም፡፡ እንደ እኛ ያደጉ አገራት ያለፉበት ነው። ያለውን የውጭ ምንዛሪ በአግባቡ መጠቀም ይገባል›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መደገፍ ያለባቸውን ለይቶ መደገፍ ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ለቅንጦት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ መቀነስ ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡


ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ በርካታ ዳያስፖራዎች በተለያዩ አገራት ቢኖሩም የውጭ ምንዛሪን ወደ አገር ውስጥ በመላክ በኩል ከፍተኛ ክፍተት አለ። የውጭ ምንዛሪን አለመላክ መንግሥትን መጉዳት አለመሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ አለመላክ ዝቅተኛ ዶላር የማመንጨት አቅም ያላቸው ነጋዴዎችና ከእነርሱ የሚጠቀሙ የህብረተሰብ ክፍሎችን መጉዳት ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ላይ በደንብ ማሰብና መረዳዳት ይገባል፡፡
ጥቁር ገበያው ያለው አቅም ምናልባትም መንግሥት ካለው አቅም ላይተናነስ እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡ ይህ ህገ ወጥ አካሄድ ገበያውን ይዞ እንዳይቀጥል መንግሥት ተገቢውን ጥረትና እርምጃ እንደሚወስድ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹እናንተም ኃላፊነታችሁን መወጣት አለባችሁ›› በማለት ባለሀብቶች ችግሩን በመከላከል ሂደት ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡


በባለሀብቱና በመንግሥት በኩል የሚስተዋለው ብክነት ሌላው የውጭ ምንዛሪ ክምችቱን እየተሻማ ያለ ችግር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡ ‹‹በመንግሥት በኩል በርካታ ሰብሰባዎች ከተደረጉ በኋላ ማሳረጊያው ወደ ውጭ አገር መሄድ ነው፡፡ ውጭ አገር መሄድ በራስ ከሆነ ችግር ላይኖረው ይችላል፤ በመንግሥት ሲሆን ግን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን ይወስዳል›› ያሉ ሲሆን ይህን ለማስተካከል መግባባት ላይ መደረሱን አስገንዝበዋል፡፡ ባለሀብቱ ከተለያዩ የመገልገያና የቅንጦት እቃዎች በመቀነስ የውጭ ምንዛሪ ክምችቱን በተወሰነ ደረጃ ማገዝ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡


በመንግሥት አገልግሎት ሰጪ መስሪያ ቤቶች ላይ ከፍተኛ የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተት መኖሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ ገልፀዋል፡፡ ይህንን የሥራ ባህል መቀየር ካልተቻለ ከባድ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ ክፍተቱ በፍትህ ዘርፍም እንደሚስተዋል ጠቁመዋል፡፡ በአዲሱ የሪፎርም ሥራም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ችግሮቹን ለማስተካከልና ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ቃል ገብተዋል፡፡ በእነዚህ ሂደቶች ውስጥ ባለሀብቱ በንቃት ሊሳተፍ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ዜና ሐተታ
እፀገነት አክሊሉ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829491
TodayToday1121
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7211
This_MonthThis_Month29671
All_DaysAll_Days2829491

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።