የውጭ ምንዛሪ እጥረት የብረታ ብረት ፋብሪካዎችን ህልውና ተፈታትኗል Featured

18 Apr 2018

አዲስ አበባ፡- የውጭ ምንዛሪ እጥረት በጥሬ ዕቃ አቅርቦት ላይ ችግር በመፍጠሩ የብረታ ብረት ፋብሪካዎችን ህልውና እየተፈታተነ መሆኑን የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ማህበር አስታወቀ፡፡

የማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ ኢንዱስትሪዎቹ ባለፈው አንድ ዓመት ለጥሬ ዕቃ ግዥ የሚሆን በቂ የውጭ ምንዛሪ ባለማግኘታቸው ከማምረት አቅማቸው ከ10 እስከ 15 በመቶ እያመረቱ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅትም አብዛኛዎቹ ማምረት ያቆሙ ሲሆን ፤ እያመረቱ የሚገኙትም ቢሆን የገቡትን ውል ለመፈጸም እንጂ በቀጥታ ለገበያው ለማቅረብ አይደለም፡፡
በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ለአንድ ዓመት ያህል አብዛኛዎቹ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅማቸው መባከኑን የጠቆሙት አቶ ሰለሞን ችግሩን ለመፍታት ለረጅም ጊዜ የሚሆን ጥሬ ዕቃ ለመግዛት የሚያስችል የውጭ ምንዛሪ ይገኛል ተብሎ ቢጠበቅም የተገኘው ትንሽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለተወሰኑት ፋብሪካዎች እንደ ማምረት አቅማቸው እስከ አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የውጭ ምንዛሪ መሰጠቱን ከኢንዱስትሪዎች ባገኙት መረጃ ለማወቅ መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡
እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ የተሰጠው የውጭ ምንዛሪ ግፋ ቢል 15 ቀን አምርተው ከማቆም የሚታደጋቸው አይደለም፡፡እንደገና የውጭ ምንዛሪ የማግኘት እድሉ ሲኖር ጥሬ ዕቃ ከውጭ ለማስመጣት የግዥ ሂደቱ ሦስትና አራት ወር የሚፈጅ በመሆኑ ፋብሪካዎቹ ማምረት ለማቆም ይገደዳሉ፡፡
ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ የብረት ዋጋ እየናረ መሄዱን የተናገሩት አቶ ሰለሞን በቤቶችና መሰል ግንባታዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ጥሬ ዕቃ የሌላቸው የብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎች ሠራተኞቻቸውን ላለመበተን በጥገና ሥራ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ጉዳዩን ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በማሳወቅም ‹‹ችግሩ ይታያል፤ መፍትሄ የሚገኝበት መንገድ ለማፈላለግ ጥረት ይደረጋል›› የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡
የብረት ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፊጤ በቀለ መንግሥት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች የውጭ ምንዛሪ በቅድሚያ እንዲያገኙ አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የተወሰነም ቢሆን ዶላር ሲሰጥ ቢቆይም ይህ ግን በቂ አለመሆኑን ነው የገለፁት፡፡ ችግሩን ለመፍታትም ለዘርፉ ቅድሚያ በመስጠት በቂ ባይሆንም የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡ በዘላቂነት ደግሞ በውጪ ንግድ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ደግሞ ዘላቂ መፍትሄ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
ማህበሩ 74 የአርማታ ብረት፣ ቱቦላሬ፣ የቤት ክዳን ቆርቆሮ፣ ሽቦዎችና ሌሎች የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ምርቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን በአባልነት አቅፏል፡፡በአገር አቀፍ ደረጃ ከብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ከዛሬ 20 ዓመት በፊት የፋብሪካዎች የማምረት አቅም 20ሺ እና 30 ሺ ቶን ብረት ሲሆን አሁን በዓመት 10 ሚሊዮን ቶን ብረት የማምረት አቅም ላይ ተደርሷል፡፡ 

ጌትነት ምህረቴ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829492
TodayToday1122
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7212
This_MonthThis_Month29672
All_DaysAll_Days2829492

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።