ቋሚ ኮሚቴው ‹‹ባለስልጣኑ የሃይል ብክነትን አልቀነሰም›› አለ Featured

18 Apr 2018

የኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለስልጣን ከሚመረተው ሃይል እየባከነ ያለውን 26 በመቶ ሃይል በተጨባጭ መቀነስ አለመቻሉን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ወቀሰ። 

ቋሚ ኮሚቴው ከትናንት በስቲያ የባለስልጣኑን የዘጠኝ ወር እቅድ አፈጻጸም ሲገመግም ባለስልጣኑ 26 በመቶ እየባከነ ያለውን ሃይል በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ ወደ 15 በመቶ ለማውረድ እቅድ ቢይዝም በአሁኑ ወቅት ከሚባክነው ሃይል ምን ያህሉን እንደቀነሰ ለምክር ቤቱ መግለፅ አልቻለም፡፡
የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አስቴር አማረ፤ ባለስልጣኑ የተሰጠውን ሃላፊት በአግባቡ አለመወጣቱን ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ዓመት የሃይል ብክነቱ እንዲቀንስ ውይይት ቢደረግም በዘንድሮው ዓመት ባለስልጣኑ በሰራቸው ስራዎች ምን ያህል የሃይል ብከነት እንደቀነሰ አለመታወቁን አስረድተዋል፡፡ ባለስልጣኑ በኢንዱስትሪዎች፣ በተቋማት በግለሰቦች መኖሪያ ቤት በሚያደርገው ምርመራ የብክነት መንስዔዎችን ቢያገኝም በተለያየ መልኩ ማስተካከያ አለማድረጉን ተናግረዋል፡፡ ምክር ቤቱ የሚሰጣቸውን ግብረ መልሶች ወስዶ ተግባራዊ በማድረግ በኩልም ችግር እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ ጀምበርነሽ ክንፈ፤ በበኩላቸው አገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያወጣች የምታመነጨውን ኃይል ከብክነት ለመታደግ ተቋሙ ከማስተማር እስከ መቅጣት የሚደርስ ስልጣን ቢሰጠውም በአግባቡ እየተወጣ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የኤሌክትሪክ ሃይል የውጭ ምንዛሬ ማግኛ፣ የዲፕሎማሲያችንም አካል ነው›› በማለት ባለስልጣኑ ተጨባጭ የሃይል ብክነት ቅነሳ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ሞገስ፤ ሃይልን ለመቆጠብ የኤሌክትሪክ ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎች አስገዳጅ ደረጃ እንዲወጣላቸው፣ የተጠቃሚዎች ግንዛቤ እንዲያድግ፣ በፋብሪካዎችና በመኖሪያ ቤቶች የሃይል ብክነት መንስዔዎችን በመለየት የሃይል ቅነሳ ለማድረግ መስራታቸውን ገልጸዋል።
‹‹ባደረግናቸው የተለያዩ ጥናቶች ብክነቱ መቀነሱን አመላክተናል›› ያሉት አቶ ጌታሁን በአገር አቀፍ ደረጃ ይባክን ከነበረው 26 በመቶ የሃይል አቅርቦት ምን ያህሉ እንደቀነሰ ግን ለማወቅ አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡ የሃይል ብክነት በምን ያህል እንደቀነሰ የማወቅ ሃላፊነትም የባለስልጣኑ አለመሆኑን ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት አራት ሺ አምስት መቶ ሜጋ ዋት ታመነጫለች፡፡ ግንባታው እየተፋጠነ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስድስት ሺ 450 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም አለው፡፡ ግንባታው ሲጠናቀቅም የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል ከ10ሺ ሜጋ ዋት በላይ ያደርሰዋል፡፡

አጎናፍር ገዛኸኝ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829530
TodayToday1160
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7250
This_MonthThis_Month29710
All_DaysAll_Days2829530

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።