በቁጭት - የሀሳብ ፍጭት Featured

18 Apr 2018

ለህዝብና ለአገር የሚጠቅሙ ተግባራትን ለማከናወን የሩጫው ዙር የሚከርበት ወቅት ላይ ነን፡፡ እርስ በርስ በመደጋገፍና በመመካከር ሁሉን ዓቀፍ ለውጥ ለማምጣት የጋራ ጉዞው የሚጠናከርበት ወሳኝ ጊዜ፡፡
አንዱ ሌላኛውን የሚከስበት፣የሚወቅስበት፣የሚተችበት፣ከሩቅ ሆኖ የሚመለከትበት…ጊዜ አብቅቷል፡፡ ‹‹እኔ ብቻ ነኝ የሀገርና የህዝብ ተቆርቋሪ፣እኔ ያልኩህን አድምጥ፣እኔ ነኝ ትክክል›› ማለት ትክክልም፣ ተገቢም አይደለም፡፡ ትክክለኛ መስመርን ተከትሎ ትክክለኛ ሃሳብ ማራመድ ነው ትክክለኛነት፡፡ በዚህ ጎዳና የሚራመድ ብዙ ተከታይ ይኖረዋል፤ተቀባይነት ያገኛል፤የአሸናፊነትን ተክሊል ይቀዳጃል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሰሞኑን ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ባደረጉት ውይይትም ይሄው እውነታ ነው የተንፀባረቀው፡፡ ለህዝብና ለአገሩ የሚጨነቅ ሁሉ የበኩሉን ሚና ሊጫወት ይገባል፡፡ ጠቃሚ የሚለውን ሃሳብ በመሰንዘር ልማቱን መደገፍና ወደ ፊት ማስኬድ ይጠበቅበታል፡፡ አገር የምትለማውና የህዝብ ተጠቃሚነት የሚረጋገጠው የጋራ ጉዞው ሲጠናከር ነው፡፡
ልሂቃንና ፖለቲከኞች አማራጭ ሃሳቦችን ይዘው በመቅረብ የአንድነት ጉዞው በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲገነባ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ አሁን ጊዜው ጠንካራ ሃሳብ አሸንፎ የሚወጣበት ነውና፡፡ በተለይም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቃሚ አማራጭ ሃሳቦችን ይዘው በመቅረብ መንግሥትን ሊሞግቱ ይገባል፡፡ ተራርቀው የቃላት ጦርነት መግጠም ሳይሆን፣ በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው በሃሳብ ፍጭት የተሻለ ሃሳብ እንዲወለድ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡
የመደማመጥ፣ የመወያየትና በሃሳብ የመሞገት አካሄድ ርቀውን መቆየታቸውን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ባለመሆኑ ጥይት በመለዋወጥ ሞትን የመሸመት ታሪክ ለማስተናገድ መገደዳችንን አስረድተዋል፡፡ ይህን በአፈ ሙዝ የመነጋገር ጥቁር አሻራ በሠላማዊ የውይይት መድረክ በሃሳብ የበላይነት ማሸነፍ እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡
በተለያዩ ሃሳቦች መካከል የሚደረግ ውይይትና ክርክር የተሻለው ጠንካራ ሃሳብ አሸንፎ እንዲወጣ ዕድል ይሰጣል፡፡ አሸናፊው ሃሳብ ደግሞ ለህዝብና ለአገር ጠቃሚ የሆኑ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ያስችላል፡፡ ስለሆነም የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ በኩል በንቃት መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የችግሮች መፍቻና መሻገሪያ መፍትሔዎችን ለማበጀት ተፎካካሪ ፓርቲዎች በንቃት ሊሳተፉ ይገባል፡፡
መንግሥት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ቆርጦ መነሳቱ በተደጋጋሚ ተመልክቷል፡፡ በዚህ በኩልም ታዲያ የታሰበውን ለማሳካት የፖለቲካ ፓርቲዎች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ገዥው ፓርቲ በበኩሉ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው ዝግጁ መሆኑን በግንባሩ ሊቀ መንበር በኩል አስታውቋል፡፡
የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱን በማጠናከሩ ሂደት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በንቃት መሳተፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ያለ ፓርቲዎች ንቁ ተሳትፎ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ውጤታማና ስኬታማ አይሆንምና፡፡ ዴሞክራሲን መገንባት የሁሉንም ተሳትፎና የጋራ ጥረት የሚጠይቅ ከባድ ሥራ ነው፡፡ ስለሆነም ትርጉም ያለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲጎለብት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጠናክረውና ተቀናጅተው መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡
ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመንግሥት ለቀረበው የ‹‹አብረን እንስራ›› ጥሪና የጋራ ጉዞ ተግባራዊ ምላሽ መስጠት አለባቸው፡፡ ፓርቲዎቹ ከህዝብ የወጡና ለህዝብ የቆሙ እንደመሆናቸው ለህዝቡ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ክፍተቶችን በማሳየት፣መፍትሔዎችን በመጠቆምና አማራጭ ሃሳቦችን በማቅረብ ከአዲሱ የመንግሥት አመራር ጋር ለመስራት የገለፁትን ፍላጎት በተግባር ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለተሻለ ለውጥ መንቀሳቀስና መትጋት አለባቸው፡፡ ህዝቡ ከቃል ያለፈ ተጨባጭ እርምጃ ይፈልጋልና፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች ለህዝባቸውና ለአገራቸው ይጠቅማሉ በሚሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡ የተለያዩ አማራጭ ሃሳቦችን በማቅረብ የሃሳብ አሸናፊነት ተቀባይነት የሚያገኝበትን አካሄድ ማጎልበትና ማስረፅ አለባቸው፡፡ በሃሳቦች መካከል የሚደረጉ ክርክሮች ጎልተው የሚደመጡበት፣ ጠንካራ ሃሳብ አሸናፊ ሆኖ የሚወጣበትን ጠቃሚ ባህል ለማዳበር መትጋትም ግዴታቸው ነው፡፡
ያለሥራ የባከኑት ቀናትና ዓመታት ቢሰራባቸው ኖሮ ሊመዘገብ የሚገባውን ውጤት ከግምት ውስጥ ያስገባ የቁጭት ስሜትን መታጠቅ አለባቸው፡፡ የቁጭቱ ረመጥ ተቆስቁሶ የጋለ ሃሳብ እንዲወለድ መትጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከተግባር ሃሳብ ይቀድማልና በሃሳቦች ፍጭት ጠንካራና ለውጥ አራማጅ ሃሳብ ነጥሮ እንዲወጣ የሁሉም ተሳትፎና ትብብር ግድ ይላል፡፡

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829553
TodayToday1183
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7273
This_MonthThis_Month29733
All_DaysAll_Days2829553

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።