‹‹ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ቅደም ተከተል አስይዞ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለአፈፃፀምም ማቅረብ የምሁራኑ ድርሻ ነው›› - ዶክተር ዓለም መብርሃቱ የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት Featured

17 Apr 2018
ዶክተር ዓለም መብርሃቱ የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ  ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዓለም መብርሃቱ የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ፎቶ፡- በሐዱሽ አብርሃ

ኢትዮጵያ ካሏት መልካም በረከቶች በመነሳት ልዩነቶችን እንደ ውበትና የዕድገት መሰረት በመውሰድ ቀድሞ ወደ ነበረችበት የስልጣኔ ማማ ለመውጣት እንደሚያስችላት በፖሊሲዎቻችንና ስትራቴጂዎቻችን በስፋት ተዳሷል፡፡ ነገር ግን ይህንን ማድረግ ካልተቻለና የህዝብ አገልጋዩ ኪራይ ሰብሳቢነት ከተጠናወተው ይህን ለማሳካት አዳጋች እንደሚሆንም በግልፅ ተቀምጧል፡፡ በወቅቱ የተቀመጡት መሰረታዊ ሀሳቦች ከጊዜ ወደጊዜ እየተሸረሸሩ በመምጣታ ቸው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሰላምና አለመረጋጋቶች መከሰታቸውን መንግስት ራሱን በጥልቀት በፈተሸበት ወቅት አረጋግጧል፡፡


ለችግሮቹ መፍትሄ ናቸው የተባሉትንም ችግሮች በመፍታት ህዝብን ለመካስ እንደሚሰራ ቃል ገብቷል፡፡ በዚህም በተለይ ህዝቡን የልማቱ ተሳታፊና ባለቤት ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከሰሞኑም የትግራይ ክልል ዋና ከተማ በሆነችው መቐለ ከተማ የምሁራን መድረክ ተካሂዷል፡፡ እኛም በዚህ ዙሪያ በዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንትና የትግራይ ቲንክ ታንክ ምክረ ሀሳብ ሰጪ ቡድን አስተባባሪ ከሆኑት ዶክተር ዓለም መብርሃቱ ጋር ያደረግነውን ቃለምልልስ ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡


አዲስ ዘመን፡- መቐለ ላይ የተደረገው የምሁራን ውይይት መድረክ ዋና ዓላማ ምን ነበር?
ዶክተር ዓለም፡- በተለያዩ ወቅቶች በተፈጠሩ ህዝባዊ መድረኮች ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠት አኳያ ችግሮች እንዳሉ ሲነሱ ቆይቷል፡፡ ለችግሮቹ ባለቤትና መፍትሄ ለማስቀመጥ በተለይ በምሁራን በኩል ሊሰጥ የሚገባውን ድጋፍ፣ ምክረ ሀሳብና ጥናትና ምርምር መሰረት ያደረጉ የመፍትሄ ሀሳቦች መጠቀም ይቻል ዘንድ የክልሉ መንግስት ድጋፍ የሚፈልግባቸውን 15 የሚደርሱ ጉዳዮች ለይቷል፡፡ በዚህም ከቲንክ ታንኩ ጋር በመሆን ምሁራን ሀሳብ እንዲያቀርቡ በመጠየቅና የህዝቡን ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችሉ ሀሳቦች ተወያይቶ በተወሰነ ደረጃ መልክ ለማስያዝ ዓላማ አድርጎ የተካሄደ የውይይት መድረክ ነው፡፡


አዲስ ዘመን፡- መንግስት ከምሁራኑ ጋር ለውይይት ያቀረባቸው 15 መሰረታዊ ጉዳዮች ምን ነበሩ?
ዶክተር ዓለም፡- ለውይይት የቀረቡት ዋና ዋና ጉዳዮች በርካታ ሀሳቦችን በውስጣቸው ያቀፉ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ድህነትን በተሻለ ፍጥነት እንዴት መቀነስ ይቻላል? እያጋጠሙ ያሉ እንቅፋቶች ምንድን ናቸው? እነዚህን እንቅፋቶችን መፍትሄ እንዲያገኙ ለማስቻል መወሰድ ያለባቸው መፍትሄዎችስ? በሚሉት ዙሪያ ያጠነጠነ ነው፡፡ እንደ አገር በሚፈለገው ደረጃ ድህነትን መቀነስ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች አሉ፡፡ በክልሉ ያለው የድህነት መጠን 27 በመቶ ነው፡፡ ይህም በአገር ደረጃ ካለው 23 ነጥብ 5 በመቶ ጋር ሲነፃጸር ከፍ ያለ ነው፡፡


ችግሩን በፍጥነት መቀነስ ይቻልባቸዋል በተባሉ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ እያጋጠሙ የሚገኙ ተግዳሮቶችና መልካም ዕድሎች እንዲሁም የግብርና ትራንስፎርሜሽን ላይ በርካታ ጉዳዮች ተዳሰዋል፡፡ በተያያዘ ህጋዊ ያልሆኑ ቤቶች ስራ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን እያስነሳ መሆኑም ውይይት ከተደረገባቸው ጉዳዮች ውስጥ ይገኝበታል፡፡ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ፣ የነዋሪው የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና መሰል ጥያቄዎች ከተሞች ላይ ከሚነሱ በርካታ ችግሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የውሃ አቅርቦት ችግርም ቢሆን የህብረተሰቡ አንገብጋቢ ጥያቄ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተነስቷል፡፡


ከቱሪዝም ጋር በተያያዘ በክርስትናው የአክሱም በእስልምናው የነጃሺ እንዲሁም ሌሎች ከሀይማኖታዊ ጉዳዮች ውጪ የሆኑ ከሶስት ሺህ ዓመታት በፊት የነበሩ የአርኪዎሎጂ መስህቦች መገኛና የስልጣኔ መነሻም በመሆን ትታወቃለች፡፡ በተመሳሳይ የማዕድን ስራ ጋር ተያይዞ ክልሉ በርካታ ማዕድን መገኛ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ህብረተሰቡንና አገሪቱን በሚጠቅም መልኩ ለመስራት የተጀመሩ መልካም ተግባራት ቢኖሩም በወርቅ እምነበረድና መሰል ማዕድናት የውጪ ምንዛሬን በማግኘት ማህበረሰቡን በሚጠቅም መልኩ መስራት ላይ ቀሪ ስራዎች አሉ፡፡ በዚህም ምሁራን ሊያበረክቱት የሚችሉትን አስተዋፅዖ ተፈትሾበታል፡፡


በአገር ደረጃ በርካታ ጥያቄዎች የሚነሳው ወጣቶች ላይ በመሆኑ በክልሉ ወጣቶችን በአግባቡ የመደገፍ፣ የማገዝና የማብቃት ጉዳዮች ታይተዋል፡፡ በዚህም ሁሉን ነገር መንግስት እንዲያቀርብ መፈለግ ሳይሆን እነርሱ የሚገባቸው ርቀት እንዲጓዙ ማስቻልና ግንባታ ስራው ላይ ማተኮር እንደሚገባ ታምኗል፡፡ በተመሳሳይ በአገር ደረጃ የትምህርት ተደራሽነትና ፍትሀዊነት ላይ የተሰሩ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ቢኖሩም በጥራት ላይ ግን በችግር የሚነሱ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸው ታይቷል፡፡ ክፍተቶችን በመሸፈን ተማሪዎች በዕውቀታቸውና በስነምግባርም የታነፁ እንዲሆኑ ቤተሰብ ካለው ድርሻ ውጪ መንግስትም ጥራትን ለማረጋገጥ መስራት እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል፡፡ ከትምህርት ጎን ለጎን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራው ቁልፍ ዘርፍ በሆነው ጤና ላይ የሚታዩ ችግሮችን ሊያቃልል በሚችል መልኩ መሰራት እንዳለበት የተደረገው ውይይትም ሌላው አጀንዳ ነበር፡፡


የትግራይ ህዝብ የተለየ ተጠቃሚነት እንዲሁም የህወሓት የበላይነት በፖለቲካ አመራሩ ውስጥ እንዳለ በርካታ የመገናኛ ብዙሃን በተለይ ከህግ ማዕቀፍ ውስጥ ያልሆኑት በተደጋጋሚ ሲያነሱ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታዎች ናቸው፡፡ ይህም በአሁኑ ወቅት ካለው የአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር ተያይዞ አጀንዳ ሊሆን ችሏል፡፡ በዚህም ትክክለኛ የክልሉን ተጨባጭ ምስል በሚያሳይ መልኩ ሳይሆን የክልሉን ህዝብ፣ መከላከያ ሰራዊትና የፀጥታ ስርዓቱን ዒላማ በማድረግ የተሳሳተ ምልከታ እንዲኖር የሚደረግ ዘመቻ ነበር፡፡


በመድረኩ እንደ ቀልድ ሲነገሩና የክልሉም ህዝብ ስቆ ያሳልፋቸው የነበሩ የተዛቡ አመለካከቶች ‹‹ውሸት ሲደጋገም ዕውነት ይሆናል›› እንደሚባለው ችግር መፍጠራቸው ታምኗል፡፡ በተለይም ወጣቱ ሀይል ያለውን ዕውነታ እንዲያውቅ ከማድረግ ይልቅ በውሸት እንዲሸበብና ይህን ተቀብሎ እንዲኖር አድርጎታል፡፡ ይህን ለማስተካከል ስራዎች መሰራት እንዳለባቸውም ትምህርት የተወሰደበት መድረክ ነው፡፡
የተለያዩ አካላት የስራ ነፃነትና ተደጋጋፊነት ላይ በተለይ ህግ አውጪ፣ ህግ ተርጓሚና ህግ አስፈፃሚ አካላት ታችኛው መዋቅር ድረስ ቢገኙም ህብረተሰቡ ግን ችግሮችን ከማንሳት አልቦዘነም፡፡ ለዚህም ተቋማዊ አቅምን በሚገነባ መልኩ አለመዋቀራቸው እንደ ምክንያት ሊነሳ ይችላል፡፡ አንዱ ሌላውን በሚቆጣጠርበትና ለችግሮች መፍትሄ እየተቀመጠ መሄድ ላይ ችግር ይስተዋላል ፡፡ በዚህም ህብረተሰቡ በ1983 ዓ/ም ጅማሮ ላይ የተሻለ ፍትህ ያገኝ እንደነበርም በማንሳት በአሁኑ ወቅት እያገኘ ስላለው አገልግሎት ጥያቄዎችን እንዲያነሳ እያደረገው ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ህግ አስፈፃሚ አካላት በስፋት ቢኖሩም የህብረተሰቡን እርካታ ማረጋገጥ ያልተቻለው ለምንድን ነው? በሚል በሰፊው ውይይት ተደርጎ አቅጣጫም ተቀምጧል፡፡


አዲስ ዘመን፡- ውይይቱን በዚህ ወቅት ላይ እንዲካሄድ ያደረገው ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?
ዶክተር ዓለም፡- መንግስት የተለያዩ ለውጦችን እያደረገ ይገኛል፡፡ የህዝብ መድረኮች እየተፈጠሩና በጥልቅ ተሃድሶ የተለዩ ችግሮችም እየተፈተሹ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው ልምድ በሚፈጠሩ መድረኮች የሚነሱ ሃሳቦች ላይ የተወሰነ ርቀት ለመጓዝ ጥረት ይደረጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን እየተነሱ ያሉት ችግሮች በርካታ በመሆናቸው እስካሁን በተመጣበት መልኩ የሚፈለገው ደረጃ መድረስ አዳጋች ይሆናል፡፡ ለህዝብ ጥያቄ ፈጣንና አግባብ ያለው መልስ መስጠትም ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም የምሁራኑን አቅም ቀድሞ ከነበረው በላቀ ደረጃ መጠቀም ተገቢ ነው የሚል መነሻን በመያዝ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡


ውይይት በተደረገባቸው 15 አንኳር ነጥቦች ላይ የክልሉ አስተዳደር የምሁራኑን ድጋፍ ምን መሆን እንዳለበትም ያመላከተ መድረክ በመሆኑ ይህንን መሰረት ያደረጉ ስራዎችም ይሰራሉ፡፡ ማህበረሰቡ የሚጠይቃቸው ጥያቄዎችና ድርጅቱ በጥልቀት ወደ ውስጡ አይቶ የለያቸው ጉዳዮች አፋጣኝ ሳይንሳዊና ዘላቂነት ያለው የተሻለ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል የሚል ዕምነት መያዙም ለመድረኩ መካሄድ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡


አዲስ ዘመን፡- ከወቅቱ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር የሚያያይዘው ጉዳይ ይኖር ይሆን?
ዶክተር ዓለም፡- በትምህርት ጥራት፣ በጤና፣ በወጣቶችና መሰል ዘርፎች ላይ የሚነሱ የህዝብ ሀሳቦች በአገር ደረጃ እየተነሱ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በመቐለው መድረክ የተነሱ ጥያቄዎችም በሌሎችም አካባቢዎች የሚነሱ አገራዊ ጥያቄዎች በመሆናቸው የጋራ ችግር ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ ለጥያቄዎቹም ተገቢ መልስ መስጠት ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም የተነሱት ጉዳዮች በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች ሊሰራባቸው የሚገቡና ትኩረትን የሚሹ ናቸው፡፡ ትግራይ ውስጥ ያሉ ችግሮችና የሚሰጡ መፍትሄዎችም በተመሳሳይ መልኩ ጥናትን መሰረት በማድረግ በሌሎችም አካባቢዎች ቢሰራ አንዱ ከአንዱ በመማማር ፈጣን ለውጥን ማምጣት ይቻላል፡፡


አዲስ ዘመን፡- በመድረኩ ላይ የተነሱ ዋና ዋና አከራካሪ ሀሳቦች ምን ምን ናቸው? የተደረሰበትስ መቋጫ ምን ነበር?
ዶክተር ዓለም፡- የተለዩት ችግሮች በአንድ መድረክና በውስን ሰው የተነሱ ሳይሆን በስፋት ድርጅቱም የገመገማቸውና በተለያዩ ህዝባዊ መድረኮች ሲነሱና ሲመከርባቸው የነበሩ በመሆኑ አከራካሪ አልነበሩም፡፡ ችግሮች በአንድ ጀምበር ይጠፋሉ ማለት ባይቻልም ደረጃ በደረጃ ማቃለልና በድህነት ወለል ውስጥ ያሉ ማህበረሰቦችን ወደ ተሻለ ሁኔታ ውስጥ ማሸጋገር ወሳኝ በመሆኑ ቆራጥ ስራ ለማከናወን ታቅዷል፡:


አገሪቱን መካከለኛና ከፍተኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ የጋራ መስማማት ላይ የተደረሰበት ቢሆንም የትኛው ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል? መቼ? በምን መልኩና እንዴት? የሚለው ግን በቀጣይ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች ጥናት ላይ ተመስርቶ ችግሮችን እንደየ ፈርጃቸው ይለያሉ፡፡ ይህም ተግባር ላይ ሲውል የተሻለ ውጤት እንደሚያመጣ ተስፋ የተሰነቀበት መድረክ ነው፡፡ በክልል ደረጃም ይህንን ኃላፊነት ወስዶ ሊያስተባብር የሚችል የምርምር ተቋም ወይም ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሊቋቋም እንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡


አዲስ ዘመን፡- በውይይቱ የክልሉ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም ይቋቋም የሚል ሀሳብ መቅረቡ ይታወቃል፡፡ የተቋሙ መመስረት ለክልሉ ብሎም ለአገር ያለው ፋይዳ ምንድን ነው?
ዶክተር ዓለም፡- እንዲቋቋም በሀሳብ የተጠነሰሰው ተቋም ስራዎቹን ወደ ትግበራ እንዲለወጡ ያስተባብራል፡፡ ወደ ተግባር ሲገባ በተለያየ ምክንያት ሳይተገበሩ የሚቀሩ ስራዎች እንዳይኖሩም የተፈፀሙትንና ያልተፈፀሙትን እየተከታተለ በጥናት እየለየ ፈፃሚውን አካል ይጠይቃል፡፡ በዚህም ሀሳቦቹ ወደ ትግበራ እንዲገቡና ያልተፈፀሙትን እንዲፈፀሙ የተፈፀሙትንም ውጤታቸውን እየመዘነ ይሄዳል፡፡


ተቋሙ ጥናትና ምርምሮችን እያደረገ የሚሄድ በመሆኑ በአገር ደረጃ ከተለያዩ የፖሊሲ ጥናት ተቋማት ጋር የሚያገናኘውን ልምድም አቀናጅቶ በርካታ ስራዎችን እንደሚሰራ ይጠበቃል፡፡ በውስጡም ለተነሱት ችግሮችና መፍትሄ ማምጣት የሚችሉ ምሁራንን ያቀፈ ይሆናል፡፡ ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል እንዲጀመር ይታቀድ እንጂ በክልሉ የሚሰሩ ስራዎች በአገር ደረጃ ለሚከናወኑት ተግባራት እንደ ግብዓት ሆነው ያገለግላሉ፡፡


አዲስ ዘመን፡- እርስዎ እንደ አንድ የቲንክ ታንክ ቡድን አባልና አስተባባሪ የተለዩት ችግሮች በዚህ መሰል መድረኮች ይፈታል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ዓለም፡- ለለውጥ ትልቁ እርምጃ የሆነው ችግርን አውቆና ተረድቶ መፍትሄ ለማምጣት መስራት ነው፡፡ በዚህም መንግስት ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው ችግሮች መፍትሄ ማግኘት እንደሚገባቸው ያምናል፡፡ ለዚህም በበርካታ ጊዜያት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ቢያከናውንም ትክክለኛውን ለውጥ ለማምጣት ድጋፍ ያስፈልገዋል፡፡ በሌላ በኩል መንግስትም በተለያየ መንገድ ለአገሪቱ ጠቃሚ የሆኑ ዕውቀቶች ባለቤት የሆኑ ሁሉ አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት መዘንጋት የለበትም፡፡


አገሪቱ ምንም እንኳን ከጊዜ ወደጊዜ ከድህነት ለመውጣት በሰራችው ስራ ለውጦች ማምጣት ብትችልም ያልተሻገረቻቸው ችግሮች በመኖራቸው ሳይንሳዊ የሆነውን መንገድ መምረጥ ለነገ ተብሎ የሚቀር ሊሆን አይገባም፡፡ ይህን መሰል ተቋማትም በዓለም ደረጃ ከዕድገት ማማ ደርሰዋል የሚባሉትም ሆኑ በማደግ ላይ ያሉ አገራት ተጠቅመውበት እመርታዊ ለውጥን ያስመዘገቡበት ነው፡፡ በመሆኑም መንግስት ሀሳቡን ቶሎ ተግባራዊ በማድረግ የህብረተሰቡን ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ምሁሩም ዕድል አግኝቶ ትምህርትና ምርምር ቀስሟልና ህብረተሰቡ ባገኛቸው መድረኮች የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ቅደም ተከተል አስይዞ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለአፈፃፀምም ማቅረብ ደግሞ የምሁራኑ ድርሻ ይሆናል፡፡


አዲስ ዘመን፡- ብዙ ጊዜ አዳዲስ ሀሳቦች ይፈልቃሉ አንዳንዶቹ በሃሳብ ሲቀሩ የተወሰኑት ደግሞ መሬት ወርደው ተግባራዊም ይደረጋሉ፡፡ ነገር ግን ውጤት አልባ ሆነው መቅረታቸው በአገሪቱ እንደ ትልቅ ችግር ይነሳልና የመቐለው መድረክ ከዚህ ምን ያክል የተላቀቀ ነው?
ዶክተር ዓለም፡- በሚፈጠሩ በርካታ መድረኮች ሀሳቦች ይነሳሉ፤ ግን ወደ ተግባር ሲገቡ አይታይም፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው የቲንክ ታንክ ቡድን 2008 ዓ.ም መባቻው አንስቶ እንቅስቃሴዎች ቢኖሩትም በተዘጋጀው አንድ መድረክ ከቀረቡት ችግር ፈቺ ሀሳቦች ውጪ በሚፈለገው ሁኔታ ወደ ተግባር አልገባም፡፡ በማህበረሰብ መድረኮችም ችግሮችንም የመለየት ክፍተት ባይኖርም ለሚነሱት ችግሮች ተከታትሎ ምላሽ መስጠት ላይ ውስንነቶች እንዳሉ ይነሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ አንድን ተግባር ለመፈፀም ከሁለት ዓመት በላይ መጠበቅ የሚቻልበት ሁኔታ የለም፡፡


በስብሰባዎች ኮሚቴ ይቋቋማል፣ የተለያዩ አዋጆች ይወጣሉ፤ ነገር ግን ማስፈፀሚያ መመሪያዎች ሳይኖራቸውና ሳይተገበሩ ለበርካታ ወቅቶች ሲቆዩ ማየት የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የተጀመረው እንቅስቃሴ ግን ወደ ትግበራ ሊገባበት እንደሚገባ በመነጋገር ለችግሮቹ የመፍቻ ጊዜ ገደብ ተቀምጦላቸው እንዲፈቱ መደረግ እንዳለበት መድረኩ ላይ የጋራ መግባባት ተደርሶበታል፡፡ ተፈፃሚነቱን የሚከታተል ተቋም አስፈላጊ መሆኑም መድረኩ አምኖበታል፡፡ ትግበራ ላይ ሲገባ በስሜትና በስብሰባ ስለተባለ ብቻ ሳይሆን በተጠኑና በተረጋገጡ ጉዳዮች ላይ መድረኮች እየተፈጠሩም ይሆናል፡፡ ከህብረተሰቡ ጥያቄ ጎን ለጎንም መገናኛ ብዙሃን አጀንዳቸው አድርገው ለተፈፃሚነቱ ሞጋች ሊሆኑ ይገባል፡፡


አዲስ ዘመን፡- በመቐለው መድረክ ላይ የተነሱና እንደ አገር መልካም ውጤትን የሚያመጡ ሀሳቦችን ወደ ተግባር የሚያሸጋግር አካል አለ ብለው ያምናሉ? ተግባራዊ እንዲሆንስ በምን መልኩ ይከናወናል?
ዶክተር ዓለም፡- ወደ ተግባር ለማሸጋገር አቅዶ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የክልሉ መንግስት ነው፡፡ እንደ ጽህፈት ቤት ሆኖ ማስተባበሪያ በህግ የሚቋቋምለት ሲሆን በዚህ ውስጥ የተለያዩ ልምድ ያላቸው አካላት ስለሚኖሩ ለተግባራዊነቱ ይሰራሉ፡፡ በዚህም ፈፃሚ፣ አስፈፃሚ እንዲሁም ክትትል የሚያደርግላቸው አካል በግልፅ ተቀምጦላቸዋል፡፡ በቀጣይ የሚያጋጥሙ ችግሮችም በሂደት እየለዩ እየገመገሙና መፍትሄ እያስቀመጡም ይጓዛሉ፡፡


አዲስ ዘመን፡- በውይይቱ ላይ በበቂ ሁኔታ መሳተፍ የነበረባቸው ሰዎች አልተጋበዙም የሚሉ ቅሬታዎች ይነሳሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ሀሳብ አለዎት?
ዶክተር ዓለም፡- በበቂ ሁኔታ ሁሉም አካላት ተሳታፊ ሆነዋል የሚል ግምገማ የለም፡፡ ነገር ግን በአዲስ አበባ የሚገኙ በትምህርትና በምርምር ተቋማት በመስራት የካበተ ልምድ ባለቤት የሆኑ ምሁራን እንዲገኙ ተደርጓል፡፡ ስራው ይጀመር በሚል በበጎ ፈቃድ የተጀመረ መልካም ተግባር ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ክፍያም የሌለው ለህዝብ ጥቅም የሚሰራ ስራ በመሆኑ አስተዋፅዖ ማበርከት የሚፈልጉና ፍላጎት ያላቸው አካላት ቢሳተፉ በሩ ምን ጊዜም ክፍት ነው፡፡


አዲስ ዘመን፡- የውይይቱ ቀጣይነትና አስፈላጊነት ላይ የማይስማሙ ሰዎች አሉ፡፡ የዚህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው አካላትን በምን መልኩ ስለ መድረኩ አስፈላጊነት ማሳመን ይቻላል? የቤት ስራውስ የማን ነው?
ዶክተር ዓለም፡- የማይስማሙ ሰዎች መኖራቸው የዴሞክራሲ አንዱ መገለጫ በመሆኑ ግርምትን የሚጭርና እንደ ችግር የሚታይ አይደለም፡፡ ስለዚህ አያስኬድም ወይም ውጤታማም አይሆንም የሚሉ አካላት ካሉ ሀሳባቸው ይከበራል፡፡ ስራዎች ቢሰሩም ህብረተሰቡ በሚፈልገውና በሚጠይቀው ልክ ማሟላት እንደማይቻል ይታወቃል፡፡ በመሆኑም የማይስማሙ አካላት ሌሎች አማራጮችን ይዘው ከቀረቡ ለማዳመጥና ወስዶ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁነቱ እንዳለ በማወቅ ሀሳባቸውን ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡


አዲስ ዘመን፡- እናንተ እንደ አንድ የምሁራን ስብስብ ከዚህ መድረክ ምን የቤት ስራ ይዛችሁ ወጣችሁ?
ዶክተር ዓለም፡- መንግስት ምሁራኑን በህዝብ ሀብት የተማሩ በመሆናቸው የእገዛ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ይህም ትልቅ የህዝብና የመንግስት ጥያቄና ኃላፊነት ነው፡፡ ምሁሩም ይህንን ተቀብሎ የመስራት የዜግነትና ህዝባዊ ኃላፊነት አለበት፡፡ በመድረኩ የተመከረባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በመስራት አገሪቱ የኢኮኖሚ ሽግግር እንድታደርግ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ ይሰራል፡፡ ለዚህም የሚረዱ አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች በአሁኑ ወቅት እየተከናወኑ ሲሆን ጊዜው ባይወሰንም ተቋሙ በቅርብ ስራ እንደሚጀመርም ይታመናል፡፡


አዲስ ዘመን፡- ቀረ የሚሉትና የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?
ዶክተር ዓለም፡- የወጣቶች ግንባታ ላይ ብዙ ክፍተቶች በመኖራቸው በትምህርቱ ዘርፍ አንዳንዶች ወረቀቱን እንጂ ዕውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት ያለመያዝ ችግሮች ይታያሉ፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለመምህራን የሚሰጠው ክብር እያነሰ መሆኑ ትምህርት ቤት መዋያ እንጂ ዕውቀት የሚቀሰምበትና ተማሪዎችም በስነምግባር የሚታነፁበት መሆኑ እየተዘነጋም ነው፡፡ ይህም አደገኛ በመሆኑ ትምህርት ጥራቱንም የቁልቁል የሚወስድ ሊታረም የሚገባ አመለካከትና ተግባር ነው፡፡


በችግሮቹ ሳቢያ ወጣቱ ከማንበብ ይልቅ በማህበራዊ ድረገፆች የተለቀቁትን መረጃ ብቻ በማየት ሳያመዛዝን በስሜት መነዳት በሰፊው ይታይበታል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመክበር መሻትም ሌላው ችግር ነው፡፡ በዚሁ ላይ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ማንሳት ተገቢ ቢሆንም ቅድሚያ ግን የተሻለ ሆኖ መገኘት ይገባል፡፡ ይህም ወላጅንና የአገርን ባህልና ወግ ከማክበር ይጀምራል፡፡ አገር ተረካቢ በመሆናቸውም በተሰማሩበት መስክ ውጤታማ ለመሆን መትጋት ይገባቸዋል፡፡ ይህን ማድረግ ሲቻልም ለለውጥ የተጀመረውን ጉዞ በመደገፍ ከታለመው ግብ መድረስ ይቻላልና ሁሉም ለአገሩ ዕድገት ጠንክሮ መስራት ይጠበቅበታል፡፡


አዲስ ዘመን፡- እናመሰግናለን!
ዶክተር ዓለም፡- እኔም አመሰግናለሁ!

ፍዮሪ ተወልደ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829548
TodayToday1178
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7268
This_MonthThis_Month29728
All_DaysAll_Days2829548

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።