የተፈቀደ ግን ያልተፈቀደ ጉዞ Featured

17 Apr 2018

በርካታ ወጣት ሴቶች አሮጌው ፖስታ ቤት ግቢ ውስጥና በአካባቢው ይታያሉ፡፡ ወጣቶቹ ወደ አረብ ሀገሮች ለመሄድ ፓስፖርት የሚያወጡ መሆናቸውን ጉዳዩን በየዕለቱ የሚከታተሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይገልጻሉ፡፡ ያነጋገርናቸው ወጣቶችም ያረጋገጡልን ይህንኑ ነው፡፡ አዲስ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አዋጅ ተግባራዊ መደረግ ጀምሮ ይሆን ስል ራሴን ጠየቅሁ፡፡ 

በሕገ ወጥ መንገድ ሲደረግ የቆየውን የውጭ ሀገር ጉዞ እና ሲያስከትል የኖረውን ዘርፈ ብዙ ችግር እንደሚፈታ ታምኖበት የወጣውን አዲሱ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አዋጅ ለማዘጋጀት ሲባል በተለይም ወደ አረብ አገራት የሚደረግ የሥራ ስምሪት ጉዞ ታግዶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ አዋጁ ጽድቆ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተውለት እንዲሁም ከተቀባይ አገራት ጋር ስምምነቶች መፈረማቸውንም ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዚህም ዜጎች ወደ አራት ያህል በሚሆኑ አገራት በሕጋዊ መንገድ ተጉዘው መስራት ይችላሉ፡፡
ፓስፖርት ለማውጣት በኢትዮጵያ ፖስታ ቤት አግኝተን ያነጋገርኳቸው ወጣቶች እንደሚሉት፣ ዜጎች በአዲሱ አዋጅ መሠረት በሕጋዊ መንገድ ወደ አረብ ሀገሮች መሄድ ትችላላችሁ ቢባሉም በተጨባጭ ግን ሕጉ ሥራ ላይ እየዋለ አይደለም። በዚህ የተነሳም አሁንም ሕገ ወጡን መንገድ ለመከተል እየተገደዱ ይገኛሉ፡፡
ወጣት ካሚላ መሀመድ ፓስፖርት አውጥታ ለች፡፡ ፓስፖርት ያወጣችውም በሕጋዊ መንገድ ወደ አረብ ሀገሮች መሄድ ይቻላል ሲባል ሰምታ ነው፡፡ ወጣቷ ሳዑዲ አረቢያ በሕጋዊ መንገድ ሄዳ ለመስራት ብትወስንም፣ ሕጋዊውን መንገድ እንዴት ማግኘት እንደምትችል አላወቀችም።
«ቀደም ሲልም ወደ አረብ አገር ለመሄድ ተነስቼ ነበር፤ መንግሥት ጉዞውን በማገዱና እኔም በሕገ ወጥ መንገድ መሄዱን ስለፈራሁ ተውኩት» የምት ለው ወጣቷ፣ አሁን ጉዞው ተፈቅዷል መባሉን ሰምታ ለች፡፡
«በአገር ውስጥ ሰርቶ መለወጥ መልካም ነው» የምትለው ወጣት ካሚላ፣ ወደ ውጭ አገር መሄዱ የተሻለ ገቢ ያስገኛል ብላ በመገመት ውሳኔ ላይ መድረሷን ትናገራለች፡፡ «መንግሥት ጉዞው በሕጋዊ መንገድ እንዲፈጸም፣ የሚኬድባ ቸው አገራትን የአኗኗር ዘይቤ የተከተሉ ሥልጠ ናዎችን እንድናገኝ ማድረጉና የትምህርት ማስረጃም መጠየቁ ጥሩ ነው» ትላለች።
እንደ ካሚላ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመሄድ የወሰነችው አለምነሽ ሙሄ ተመሳሳይ አስተያየት ትሰጣለች፡፡ በአገር ውስጥ መስራት ጥሩ መሆኑን ጠቅሳ፣ የተሻለ ለማግኘት በሚል ወደ ውጭ መሄድን መርጣለች። አዲስ የሥራ ስምሪት ጉዞ መፈቀዱን ብትሰማም፣ ሥልጠና ከማግኘትና ፓስፖርት ከመያዝ የዘለለ እርምጃ መውሰድ እንደልተቻለች ጠቁማለች፡፡
ወጣት አለምነሽ ሕጋዊ መንገድ መመቻቸ ቱን በአድናቆት አይታዋለች፡፡ «መንግሥት ባወጣው አዋጅ ብሎም ከተቀባይ አገሮች ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት የፈለግነው ሀገር ሄደን ለመስራት ተስፋ ጥለን ነበር» የምትለው አለምነሽ፣ ሕጋዊ የተባለው ይህ መንገድ አሁንም ዝግ እንደሆነ አድርጋ ነው የተመለከተችው፡፡
ይህ አሠራር በተባለው መሠረት በፍጥነት ሥራ ላይ የማይውል ከሆነ ግን ሕገወጥ ስደቱን ያባብሰዋል የሚል ስጋት አድሮባታል፡፡ «እኔም ሆንኩ ሌሎች በሕገወጥ መንገድ ከአገር መወጣታችን አይቀርም» ስትል ጠቁማለች፡፡ ይህም በዜጎች ላይም ሆነ በአገር ላይ የሚያደ ርሰው ጉዳት በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነም ነው ያስገነዘበችው።
ወጣት ሊሻን ሙሀመድ በበኩሏ ወደ አረብ አገር ሄዳ ለመስራት በማሰብ ፓስፖርት አውጥታ ለች፤ አስፈላጊውን ሥልጠናም ወስዳለች፤ የሙያ ብቃት ምዘና (ሲኦሲ) ተፈትና አልፋለች፡፡
ወጣቷ በሕጋዊ መንገድ ለመሄድ የሚፈቀ ድበትን ቀን ብትጠባበቅም፣ «ተፈቅዷል ከአራት አገራት ጋር ስምምነት ፈጽመናል» ከሚባለው ውጪ በተግባር የሚታይ እርምጃ አለመወሰዱን ትጠቁማለች፡፡ በዚህ የተነሳም ለምታውቀው ደላላ ፓስፖርቷን ሰጥታ ለመሄድ አስባለች። ይህም ሕገ ወጥ ደላሎችን በመከላከል ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳርፍም በመጠቆም፣ ዜጎችንም ለችግር የሚዳርግ ነው ትላለች።
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ባሳዝን ደርቤ እንደሚሉት፤ እስከ አሁን 44 ኤጀንሲዎች አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተው ፍቃድ ወስደዋል፤ ወደ ተለያዩ የአረብ አገራት መሄድ የሚፈልጉ ዜጎች የሚሄዱበትን አገር የአኗናር እንዲሁም የሚሰሩትን ሥራ የተመለከተ ሥልጠና እንዲያገኙ 40 የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በአገር አቀፍ ደረጃ ተመርጠው ወደሥራ ገብተዋል። ዜጎችም ሥልጠናውንና የምዘና ፈተናውን ወስደዋል።
«መንግሥትም ከተቀባይ አገሮች በተለይም ከኳታር፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ኩየትና ጆርዳን ጋር ስምምነት ፈርሟል» የሚሉት አቶ ባሳዝን፣ እነዚህና ሌሎች ተመሳሳይ ሥራዎች ጉዞውን አስተማማኝ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝግጀቶች ተብለው ሊወሰዱ እንደሚችሉ ያብራራሉ።
እንደ አቶ ባሳዝን ገለጻ፤መንግሥት ሂደቱን ሕጋዊ ለማድረግ ረጅም ጊዜ ወስዶ ሰርቷል ፤ ይህም በሕግ በኩል ያለውን ክፍተት ለመሙላት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ይህ ሁሉ በሥራ ላይ ለሚከሰቱ ችግሮች ዋስትና ይሆናል ወይ የሚለውን መለየት የሚቻለው በሂደት ነው።
እነዚህ ዝግጅቶች ይከናወኑ እንጂ፣ ዜጎች ወደሚፈልጓቸው አገራት መቼ ይሄዳሉ የሚለው ጉዳይ አሁንም በሥራ ላይ ያለና ቁርጥ ያለ ቀን ያልተቀመጠለት መሆኑን አቶ ባሳዝን ተናግረዋል።

ዜና ሀተታ
እፀገነት አክሊሉ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829549
TodayToday1179
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7269
This_MonthThis_Month29729
All_DaysAll_Days2829549

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።