ከመረጃ በስተጀርባ Featured

17 Apr 2018

 

ዜጎች በአገራቸው ማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ መረጃ የማግኘት መብት እንዳላቸው በመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 በግልጽ ተቀምጧል፤መረጃዎችን በጥራትና በፍጥነት ለህዝቡ ተደራሽ በማድረግ በኩል የመገናኛ ብዙሃን ቁልፍ ሚና እንዳላቸውም ይታወ ቃል፡፡ ተቋማቱ ይህን ሚናቸውን በአግባቡ እንዲጫ ወቱ ማንኛውም የመንግሥት አካል መረጃ የመሰብ ሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት መብታቸውን ማክበር እንዳለበትም በአዋጁ ላይ ሰፍሯል፡፡
ይሁንና የመገናኛ ብዙሃኑ ወቅታዊ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ለማቅረብ የሚደረገው ጥረት በተባባሪ አካላት ፍቃደኝነት መጓደል ምክንያት ችግር እየገጠመው ነው ሲሉ ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ፡፡
ጋዜጠኛ አዲስ ህይወት ተስፋዬ መረጃ በፍጥ ነት አግኝቶ በትኩስነቱ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት በርካታ ችግሮች እንዳሉ ትገልፃለች፡፡ከእነዚህ ችግሮች መካከል ትክክለኛውን ምንጭ በተፈለገው ጊዜና ሰዓት ማግኘት አለመቻል አንዱ መሆኑን ትጠቅሳለች።የመረጃ ምንጮች ለሥራ ወደ ክልል ወጥተናል፣ አልተዘጋጀንም የሚሉና ሌሎችም ምክንያቶችን በመደርደር ፣ቀጠሮ በማብዛት ትክክለኛውን የመረጃ ምንጭ ለማግኘት እንቅፋት ከሆኑ ምክንያቶች ውስጥ እንደሚጠቀሱ ትገልጻለች፡፡
‹‹አንድ ሰው ሙያው ላይ እስካለ ድረስ ሁሌም መረጃ ለመስጠት ዝግጁ ነው ተብሎ ይታሰባል›› የምትለው አዲስ ህይወት፤ የመረጃ ባለሙያዎቹ ይህን ከማድረግ ይልቅ ጊዜ ይሰጠን ፤ ዝግጅት ያስፈልገናል ሲሉ እንደሚደመጡ ትጠቁማለች፡፡ ይህም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያው እቅዱን እንዳያሳካ እንደሚያደርገው ትጠቁማለች፡፡
እንደ አዲስ ህይወት ገለጻ፤ በመረጃ ሰጪ አካላት በኩል የሚቀርቡት ሁሉም ምክንያቶች አሳማኝ አይደሉም ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡አልፎ አልፎ ከአቅም በላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች ቢኖሩም የመገናኛ ብዙሃን ሁሌም ትኩስ መረጃዎችን ለህዝቡ ማድረስ ስላለባቸው መረጃው የሚመለከተው አካል ባይኖር እንኳ ተወካይ ማስቀመጥ የግድ መሆኑን ትናገራለች፡፡
አንዳንድ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች እነርሱ በፈለጉት መንገድ ይሰራሉ፡፡ ለምሳሌ ጉዳዩን መተንተን የሚችልና ለቦታው የተመደበ ባለሙያ እያለ ራሳችን ካልሰጠን የሚሉበት ጊዜ ብዙ ነው በመሆኑም ሁሉም በየደረጃው ኃላፊነቱን መወጣቱ መረጃን በትክክል በሚፈለገው መልኩ ለህዝብ ለማቅረብ ያግዛል ትላለች፡፡
እንደ አዲስ ህይወት ማብራሪያ፤መረጃን ከመንግሥትም ሆነ ከግል ተቋማት በፍጥነት እንዳይገኝ ከሚያደርጉት መካከል መረጃውን በትክክል አቀናብሮ ያለመያዝ ፣ወቅታዊ አለማድረግና የመገናኛ ብዙሃንን መፍራት የሚሉት ይገኙበታል። እዚህ ላይ ግን ባለሙያውም ትኩስ መረጃን ከሌሎች ቀድሞ ለማግኘት ሲል የሚፈጥረው ጉትጎታ ማሰልቸትን እንደሚያስከ ትልም ተናግራለች፡፡
‹‹የመረጃ ነፃነት አዋጁ መከበር ይኖርበታል፤ መገናኛ ብዙሃንም ‹በተደጋጋሚ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም › በማለት አየር ላይ የማዋልና በጋዜጣ ላይ የመፃፍ ልምድ ሊያዳብሩ ይገባል ትላለች ፡፡
ጋዜጠኛ ሲሳይ ሳህሉ በበኩሉ እንደሚገል ፀው፤ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት አዋጁ ሁሉም ተቋማት ለመረጃ በራቸውን ክፍት ማድረግ እንዳለባቸው ቢደነግግም፣መረጃ ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በሰዓቱ ለማግኘት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ሲቸገሩ ይታያል፡፡
ይህ የሚያሳየው መረጃ ለመስጠት ፍላጎት አለመኖሩን ነው የሚለው ሲሳይ፣ከዚህ አንጻር ብዙ ያልተሰሩ እንዳሉ ይጠቁማል፡፡ መረጃ ቶሎ ካለማግኘት ጋር በተያያዘም ህብረተሰቡ የሚፈልጋቸው ወሳኝ መረጃዎች እያመለጡት ነው ይላል፡፡
እንደ ጋዜጠኛ ሲሳይ ገለፃ፤መረጃ ክፍል ላይ በኃላፊነት የተቀመጡ ሰዎች ይህንን አለመስራታቸው አንድም የአቅም ውስንነት እንዳለባቸው ይጠቁማል፡፡ ነገሮችን ወደ ፖለቲካዊ አንድምታ የመቀየር ሁኔታዎችም ይስተዋላሉ፡፡ ሥራዎች አጥጋቢ ባልሆኑበት ጊዜ ይህን ለህብረተሰቡ ለማውጣት ፍርሃት ያድርባቸዋል፤ ይህ ሁሉ መረጃ ቶሎ የማግኘቱን ዕድል ያጠበዋል ሲል ያብራራል፡፡
ጋዜጠኛ ሲሳይ እንደሚገልፀው፤መረጃን በትኩሱና በወቅቱ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ መሰራት ይኖርበታል፡፡ መንግሥት ህብረተሰቡ መረጃ በፍጥነት የሚያገኝበትን መንገድ ለማመቻቸት በተለያዩ ተቋማቱ ላይ ተፅዕኖ ማሳደር ይጠበቅበታል፡፡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችም መረጃን ከመለመን ይልቅ መረጃ የማግኘት መብታቸውን ተጠቅመው አበክረው መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንን አድርገው መልስ ሲያጡ ሂደቱን በመጠበቅ ወደሚመለከተው ክፍል ገፍቶ መሄድ ያስፈልጋል፡፡
በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽንና የህዝብ ተሳትፎ አገልግሎት ኃላፊ ወይዘሮ አማረች በቀለ ፤መረጃ ለማግኘት ችግር እንዳለ ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በተደጋጋሚ እንደሚደመጥ ይገልጻሉ፡፡ችግሩ የተፈጠረው ባለሙያዎቹ ከህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች መረጃን ከመጠየቅ ይልቅ በተቋሙ ውስጥ ያሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ማነጋገር ስለሚፈልጉ ነው የሚሉት ወይዘሮ አማረች፣ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው ስለሚሰራበት ተቋም በቂ መረጃ ስለሚኖረው ጋዜጠኞቹም በዚሁ ልክ እምነት ጥለው ሊጠቀሙበት ይገባል ይላሉ ፡፡
እንደ ወይዘሮ አማረች ገለፃ ፤አንዳንዴ የአሰራር ችግሮች ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ትክክለኛውን መረጃ አጣርቶ ለመስጠት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በዚህ ሂደት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያው የሚፈልገውን መረጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማግኘት ይቸገራል፡፡ በመርህ ደረጃ የህዝብ ግንኙነት ክፍሉ ተደራጅቶ ማንኛውም አካል ቢመጣ መረጃ የመስጠት ግዴታ ቢኖርበትም የአደረጃጀት ክፍተትና በባለሙያውም በኩል መረጃን አጥርቶ የመያዝና የማቀበል ችግሮች አሉ፡፡ መረጃ በእጃቸው ያላቸው ሰዎች መረጃ ለመስጠት ያላቸው አመለካከትም ኋላ ቀር ነው፡፡
የችግሩን ምንጭ ለማወቅ በጉዳዩ ዙሪያ ጥናት ማካሄድ እንደሚያግዝ የሚገልፁት ወይዘሮ አማረች፤ በተለይም የህዝብ ግንኙነት አደረጃጀቱን ማብቃትና ማጠናከር ችግሩን ለመፍታት ዋነኛ መፍትሄ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ የመንግሥት ተቋማት ለህዝብ ግንኙነት ዘርፍ የሚሰጡት ትኩረት ዝቅተኛ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በአጠቃላይ የህዝብ ግንኙነቱና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያው ተመሳሳይ ሙያ ያላቸው እንደመሆኑ ተናቦ መስራቱ አስፈላጊ ነው፡፡
በመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የሚዲያ ልማትና አብዝህነት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ታምራት ደጀኔ ሰሞኑን እንደገለጹት፤ መረጃ በመስጠት በኩል መሻሻሎች ቢኖሩም፣ክፍተቶችም ይስተዋላሉ፡፡
መረጃ በመስጠት በኩል በጤናና መንገድ ዘርፍ የሚሰሩ ባለሙያዎች እንደሚታወቁ ጠቅሰው፣ በአንጻሩ የማይሰጡ ባለሙያዎች በርካታ መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡እሳቸው እንደሚሉት፤ መረጃ ላለመስጠት ምክንያት እየሆኑ ከሚገኙት ምክንያቶች መካከል የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት አዋጁን በሚገባ አለማወቅ አንዱ ሲሆን፣ ተቋማት የኮሙኒኬሽን ባለሙያውን የማኔጅመንት አካል በማድረግ ውሳኔዎችን እንዲያውቅ አለማድረጋቸው ሌላው ምክንያት ነው፡፡

 

ዜና ሀተታ
አስናቀ ፀጋዬ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829550
TodayToday1180
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7270
This_MonthThis_Month29730
All_DaysAll_Days2829550

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።