የባከነውን ጊዜ ለማካካስ እንሥራ Featured

16 Apr 2018

የሀገራችንን የኋላ ታሪክ ስንመለከት የተለያዩ ተቃርኖዎችን እናገኛለን፡፡ በአንድ በኩል የሰው ልጅ መገኛና የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት፣ ለውጭ ወራሪ ሃይሎች ያልተንበረከከችና ነፃነቷን አስከብራ የቆየች፤ በሌላ በኩል ደግሞ በሂደት ከነበረችበት የሥልጣኔ ደረጃ እየተንሸራተተች የድህነትና የኋላ ቀርነት መገለጫ መሆናችን የኋላ ታሪካችን ያስታውሰናል፡፡
ባሳለፍነው የአንድ ምዕተ ዓመት ጊዜ ውስጥ የነበረውን ታሪክ ስንመለከት ኢትዮጵያ በአብዛኛው ለህዝቦቿ ያልተመቸችና ድህነት መገለጫዋ የሆነች ጊዜ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ከ19ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ በአንድ በኩል የከተሞች መስፋፋትና የህዝብ ቁጥር እየጨመረ መሄድ በሌላ በኩል ደግሞ ለህዝብ ፍላጎት ተገቢውን ትኩረት ባልሰጡ መሪዎች የተነሳ የህዝብ ቅሬታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣበትና ለጦርነት ብሎም ለኢኮኖሚ ችግር የተዳረግንበት ዘመን አሳልፈናል፡፡
ያለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ደግሞ አገራችን ከቆየችበት የጦርነትና የኋላቀርነት ታሪክ ወጥታ ፊቷን ወደ ልማት ያዞረችበትና ህዝቦቿም የሠላም አየር መተንፈስ የጀመሩበት ወቅት ነው፡፡ ባለፉት አሥራ አምስት ዓመታትም ኢትዮጵያ በጀመረችው የልማት ትግል ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ለዘመናት የተንሰራፋውን ድህነት የኋላ ታሪክ ለማድረግ ተጨባጭ ፍንጭ አሳይታለች፡፡
ያም ሆኖ ግን አገራችን የጀመረችው የልማት ጎዳና ለዘመናት ተንሰራፍቶ ከኖረው ድህነትና ኋላቀርነት እንዲሁም በየጊዜው እያደገ ከመጣው የህዝብ ፍላጎት ጋር ተዳምሮ ህብረተሰቡን በሚፈለገው ደረጃ ሊያረካ አልቻለም፡፡ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የኅብረተሰቡ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች በወቅቱና በተገቢው ሁኔታ ምላሽ ባለማግኘታቸው ህብረተሰቡን ለቅሬታና ለአመፅ ዳርጎታል፡፡
በአንድ በኩል ገና ከወደቀበት ቀና ማለት የጀመረው የአገራችን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣውን የህዝቡን ፍላጎት ለማርካት የሚያስችል አቅም አለመገንባቱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን የህዝብ ፍላጎት ተረድቶ በቁርጠኝነት ለማስፈፀም አቅሙንና ጉልበቱን ለዚህ ብቻ ማዋል የሚችል አስፈፃሚ ሃይል በሚገባው ደረጃ አለመፈጠሩ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማርካት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የራሱን አሉታዊ ጫና ፈጥሮ ሁከቱን ይበልጥ አባባሰው፡፡
በዚህ የተነሳም ኅብረተሰቡ በተለይ ወጣቱ በየአካባቢው በመንግሥት ላይ ቅሬታ ማሰማት ብቻ ሳይሆን ለተጀመረው የልማት እንቅስቃሴ ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል፡፡ አጋጣሚውን መጠቀም የፈለጉ ሃይሎችም በተነሳው እሳት ላይ ቤንዚን በማርከፍከፍ አገራችን ወደ እርስ በርስ ጦርነትና ወደማያባራ የእርስ በርስ ግጭት እንድትገባ የበኩላቸውን ግፊት ሲያደርጉ ሰነበቱ፡፡
ያም ሆኖ ግን አገሪቱን ከድህነት ማላቀቅ ዋነኛ ዓላማው አድርጎ የተነሳው የኢትዮጵያ መንግሥት ለዓመታት በልማቱ ሥራ ላይ ያካበተውን ልምድና ተሞክሮ በመጠቀም በሃገሪቱ ሰላምን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ አቋም ወስዶ በመንቀሳቀስ ስኬት አስመዝግቧል፡፡ መንግሥትም በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከአንድም ሁለት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ቢገደድም ችግሩን በራሱ አቅም ለመፍታት ለህዝቡ በገባው ቃል መሰረት መንስኤውን በጥልቀት ከመረመረ በኋላ በበሰለ የአመራር ጥበብ በመፍታት ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል፡፡
ያም ሆኖ ግን ባለፉት ሁለት ዓመታት የተነሱት ግጭቶችና የተከሰተው ውድመት “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው ገና ዳዴ ማለት ለጀመረው የአገራችን ኢኮኖሚ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ በተለይ በነዚህ የግጭት ወቅቶች የታየው የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን የማውደም፣ ፋብሪካዎችን የማቃጠልና የዜጎችን ንብረት የማጥፋት እንቅስቃሴ በአገርም ሆነ በዜጎች ህይወት ላይ ያሳደረው ተፅእኖና ጫና ቀላል አይደለም፡፡
ለአመታት ላባቸውን አንጠፍጥፈው ያፈሩት ሃብትና ንብረት በድንገት የወደማቸው ዜጎች ጉዳት የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጉዳት ሆኖ ሊሰማን ይገባል፡፡ መንግስት ከህዝብ በሚሰበስበው ግብር የሚገነቡና ነገ ራሳችን የምንጠቀምባቸው የጋራ ሃብቶቻችን መጥፋትም የሁላችንም ጉዳት በመሆኑ ሊቆጨን ይገባል፡፡
ይህ ቁጭታችን ግን ባለፈው ለመፀፀት ብቻ ሆኖ መቅረት የለበትም፡፡ ዋናው ቁምነገር ካለፈው ስህተት ተምሮ ነገን የተሻለ ማድረግ ነው፡፡ ከትላንት ይበልጥ ነጋችን የተሻለ እንዲሆንም መስራት ብልህነት ነው፡፡ ስለዚህ ያለፈውን ስህተት እንደትምህርት ወስደን ለነገዋ ኢትዮጵያ የተሻለች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ያለፈውን ጥፋት በማካካስና የባከነውን ጊዜያችንን ማካካስ ይጠበቅብናል፡፡
ትላንት የአባቶቻችን ነው፣ ነገ ደግሞ የልጆቻችን ነው፤ ዛሬ ግን የኛ ነው፡፡ ስለዚህ የኛ የሆነውን ዛሬ በአግባቡ መጠቀም የኛ ሃላፊነትና ግዴታም ጭምር ነው፡፡ የበሰለ ማህበረሰብ ከራሱም በላይ ለልጆቹ የተሻለ ነገር ትቶ ለማለፍ ይጥራል፡፡ ለነገው ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማውረስ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና ካስቀመጥነውም ጊዜ ፈጥነን ከድህነት እንድንወጣ መትጋት ይገባል፡፡ ለዚህም በአንድ በኩሉ ከባለፈው ተምረን ዳግም የሰላም መደፍረስ እንዳይከሰት ተግተን መጠበቅ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ፊታችንን ወደ ልማት በማዞር በመደበኛ የስራ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከእንቅልፍና ከእረፍት ጊዜያችን ጊዜ ቀንሰን ለስራ እንጠቀምበት፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829487
TodayToday1117
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7207
This_MonthThis_Month29667
All_DaysAll_Days2829487

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።