የሐይቆቻችን የድረሱልን ጥሪ Featured

16 Apr 2018

የኢትዮጵያ ሐይቆች የሚሰጡትን ግልጋሎት ያክል ጥበቃ ስለማይደረግላቸው ለአደጋ እየተዳረጉ መሆኑን የዘርፉ ምሑራን ይናገራሉ፡፡ ሰዎችም በሐይቆቹ ላይ ባደረሱት ጉዳት ተመልሰው ለጉዳት እየተዳረጉ በመሆኑ ተገቢው እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባም ይመክራሉ፡፡

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ዝናቡ ገብረማርያም እንደሚገልጹት፤ አብዛኛዎቹ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች በፍጥነት እያደጉ ካሉ ከተሞች አካባቢ ያሉ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ከከተሞች በሚወጡ በካይ ነገሮች ጫሞ፣ ዓባያ፣ ሐዋሳ፣ ዝዋይ እና ቆቃን የመሳሰሉ ሐይቆች ለብክለት እየተዳረጉ ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ የብክለቱን መጠን መጨመር ያህል ችግሩን ለመከላከል እየተደረገ ያለ እርምጃ ባለመኖሩ ሐይቆቹ እጅግ አስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡
በአርሲና ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲዎች ጥምረት እአአ በመጋቢት 2017 ትኩረቱን በዝዋይ ሐይቅ ላይ አድርጎ በባቱ ከተማ በተካሄደ መድረክ ላይ የቀረበ ጥናት፣ በስምጥ ሸለቆ ያሉ በርካታ ሐይቆች የደህንነት ስጋት የተጋረጠባቸው መሆኑን ያሳያል፡፡ በዚህ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የከተሞች እድገት፣ ሐይቆች ላይ የተመሰረተ የመስኖ ልማት መስፋፋት፣ የደን መጨፍጨፍና የአፈር መከላት፣ የኢንዱስት ሪዎችና የእርሻ ግብዓት ኬሚካሎች እንዲሁም ከከተሞች የሚለቀቁ ቆሻሻዎች ለሐይቆች ደህንነት ስጋት ላይ መውደቅ ተጠቃሽ መሆናቸውንም አስፍሯል፡፡
ከ25 ዓመት በፊት የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዝዋይ ሐይቅ ላይ ማከናወናቸውን የሚያስታውሱት በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል የውሃ ሳይንስ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ግርማ ጥላሁን፤ በድጋሚ ከ10 ዓመት በፊት የሐዋሳ ሐይቅና የጫሞ ሐይቅን ጨምሮ በዚሁ ሐይቅ ላይ የዶክትሬት ዲግሪ ጥናታቸውን ማከናወናቸውን ይናገራሉ፡፡ በዚህም በተለይ የዝዋይ ሐይቅ ፊዚካላዊ /የመጠን/፣ ኬሚካላዊና ሥነ ሕይወታዊ ለውጥ ማሳየቱን በመጠቆም፤ ይሄም በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት እንደደረሰበት አመላካች መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም እነዚህ ሐይቆች ከጥቅማቸው አንጻር ጉዳታቸውን ለመከላከል የሚወሰድ እርምጃ አለመኖሩን ይገልጻሉ፡፡
እንደ ዶክተር ግርማ ገለጻ፤ በሰው ልጆች እንቅስቃሴ ከከተሞች ከሚለቀቁ ቆሻሻዎች ጀምሮ ከኢንዱስትሪዎች እስከሚወጡ ኬሚካሎች የውሃውን ይዘት እየበከሉት ይገኛል፡፡ በሐይቆቹ አካባቢ ያሉ ደኖች በመመንጠራቸውም ሐይቆች በደለል እየተሞሉ መጠናቸው እየቀነሰ ነው፡፡ ሆኖም ለጥፋቱ የተዘረጉ እጆች፤ ችግሩን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ሐይቆቹን ለማልማት በሚገባው ደረጃ አልተንቀሳቀሱም፡፡ ይህ ደግሞ ካለው ከፍተኛ የሕዝብና የከተሞች እድገት፤ እንዲሁም የፋብሪካዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ሐይቆቹን በከፍተኛ ደረጃ የሚጎዱ ሁኔታዎች አብረው እንዲያድጉ፤ በብዝሃ ሕይወትም ሆነ በሰው ላይ ጉዳት እንዲደርስ ያደርጋል፡፡ ከችግሩ ስፋትና ፍጥነት አንፃርም ሐይቆቹን የመታደግ ሥራው ተዘንግቷል፡፡
ዶክተር ዝናቡ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ማንኛውም የውሃ አካል ሲበከል መጀመሪያ የሚጎዳው በውሃ አካል ውስጥ ያለው ብዝሃ ሕይወት ነው፡፡ ከዚያም ወደ ሰውና አካባቢ ይሄዳል፡፡ ለምሳሌ ውሃው ሲበከል የሐይቆቹ መጠን ይቀንሳል፤ በሳር ይወረራሉ፤ አሁን ላይ ለሐይቆች እጅግ እያስፈራ ያለው የእምቦጭ አረምም ስጋት ይሆናል፡፡ ከሐይቁ የሚወጡ ወንዞች ካሉም መጠናቸው ይቀንሳል፡፡ በውስጡ ያሉትንም ፍጥረታት ይጎዳሉ፡፡ የተበከለ ዓሣ ካለ ደግሞ የሰውን ጤና ይጎዳል፡፡ ስለዚህ የሐይቆች መበከል ከብዝሃ ሕይወት ጀምሮ እስከ ሰው ጤና ድረስ ተጓዳኝ የሆኑ ችግሮችን ይፈጥራል፡፡
«አንድ ሰው መርዝ ቢጠጣ የጉዳት መጠኑ የሚለካው በጠጣው መርዝ መጠን ሳይሆን በመርዙ ጥንካሬ ነው፤» የሚሉት ዶክተር ዝናቡ፤ የሐይቆች ብክለት ሰዎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በብክለቱ መጠን ሳይሆን በበካይ ነገሩ ጥንካሬ ላይ የሚመሰረት እንደመሆኑ ሐይቆችን የመጠበቅ ሥራው ቸል ሊባል አይገባውም ይላሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም የዝዋይ እና የሐዋሳ ሐይቆች እጅጉን ለተወሳሰበ ችግር የተጋለጡ በመሆናቸው ከሐይቆቹ መጠቀም ብቻ ሳይሆን ሐይቆቹን መጠበቅ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
እንደ ዶክተር ግርማ ገለጻ ደግሞ፤ ለሐይቆች እንደሚደረገው ጥበቃና እንክብካቤ ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ውሃው ውስጥ ባለው ነገር ይጠቀማሉ ወይም ይጎዳሉ፡፡ ምክንያቱም የተፈጥሮ ሚዛኑ ባልተዛባበትና ብክለት በሌለበት ሁኔታ ላይ ያሉ ሐይቆች ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ የሚፈልጉትን ነገር ስለሚያገኙበት ጤናማ ይሆናሉ፡፡ የተፈጥሮ ሚዛናቸው ካልተጠበቀ ውሃውን የሚጠቀሙት ሁሉ አደጋ ላይ ይወድቃሉ፡፡ ሰዎችም በሐይቆ ላይ ባደረጉት ነገር ተጎጂ ይሆናሉ፡፡
በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት ከተፈለገ ችግሩ መፈጠሩን ከማመን ይጀምራል፡፡ ችግሩን ለሕዝቡ ከማሳወቅ ጀምሮ ጉዳዩን ወደውሳኔ እስከማምጣት ሊሰራበትም ያስፈልጋል፡፡ የሐይቆች ጥቅምም ሆነ ጉዳት ለሁሉም እኩል የሚደርስ ስለሆነም ሥራው ለአንድ ወገን ብቻ ሳይተው በጋራ መስራትንም ይጠይቃል፡፡
ዶክተር ዝናቡም እንደሚናገሩት፤ እነዚህን ሐይቆች ከችግር ለመታደግ ሥራው የእከሌ ተብሎ የሚተው ባይሆንም፤ የሚመለከታቸው አካላት በኃላፊነት ስሜት ተቀናጅተው ከመስራት ይልቅ ኃላፊነታቸውን ቸል ማለት ይታይባቸዋል፡፡ በተመሳሳይ በአገሪቱ «የኢትዮጵያ የውሃ ሀብት አስተዳደር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ_ ቁጥር ፻፲፭/፲፱፻፺፯»ን ጨምሮ የአዋጅ፣ የደንብና መሰል ወረቀት ላይ የተቀመጡ ሕጎችና እነዚህን የሚያስፈጽሙ ተቋማት ያሉ ቢሆንም፤ የተቋማቱ ተቀናጅቶ አለመስራት እና ሕጉን ተፈጻሚ ያለማድረግ ለሐይቆቹ መጎዳት አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ችግሩን ከመከላከል አኳያ በተግባር የተተረጎመ ሕግ ባለመታየቱም፤ ሕጎች ተግባራዊ በሚሆኑበት ዙሪያም ከትላልቅ የመንግሥት ተቋማት ጀምሮ በሐይቆቹ አካባቢ እስከሚኖረው ኅብረተሰብ ችግሩን ለመከላከል በቅንጅት መስራትና ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡
በዝዋይ ሐይቅ ዙሪያ የተከናወኑ ጥናቶች፣ እንደሚያሳዩት፤ እአአ እስከ 2017 መጀመሪያ ባለው ጊዜ ከአበባ ማሳዎችና ሌሎች ቦታዎች ወደ ሐይቁ ከሚገቡ በካይ ኬሚካሎችና ቆሻሻዎች ባሻገር፤ ከመቂ ወንዝ ጋር ብቻ በሊትር 0.28 ሚሊ ግራም ማዳበሪያ ወደ ሐይቁ ይቀላቀላል፡፡
«ከየትኛውም ሐይቅ በላይ በሰው የተነካካ ሐይቅ ቢኖር ዝዋይ ሐይቅ ነው፡፡ ይሄም በግልጽ ይታያል፤» የሚሉት ዶክተር ግርማ፤ «ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል» እንዲሉ የሐይቁ ውሃ ከመበከል አልፎ ያለ እየመሰለ ሊደርቅ እንደሚች ልም ይገልጻሉ፡፡
ከላይ የተጠቀስነው ጥናትም የተለያዩ የጥናት ውጤቶችን ዋቢ በማድረግ፣ የሐይቆቹ የደህንነት ችግር በዚህ መልኩ ከቀጠለም በ2021 የዝዋይ ሐይቅ በ25 ስኩዬር ኪሎሜትር እንደሚቀንስ፤ አቢጃታም ሊደርቅ እንደሚችል ጥናቱ አመልክቷል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታም ለሐይቆቹ ሕልውና ሳይሆን ጥፋት እየተሰራ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ግርማ በበኩላቸው፤ ይህን ተገንዝቦ የመፍትሄ እርምጃዎች ካልተወሰደ የሐሮማያ ሐይቅ እንደመድረቁ፤ የአቢጃታ ሐይቅም 40 በመቶው እንደመጥፋቱና ወፎች ጭምር እንደመሰደዳቸው በሌሎች ተመሳሳይ ችግር ላለመድረሱ ዋስትና አለመኖሩን ይገልጻሉ፡፡ ወደፊት የኢትዮጵያን እድገት ጠፍሮ ይይዛት የሚባለው የውሃ ችግርም በከተሞች እድገት ውስጥ አሁንም እየታየ መሆኑን በመጠቆምም፤ አደጋውን ለመቀነስ በየመድረኩ የሚገቡትን ቃል ጥናቶችን መሠረት አድርጎ ወደተግባር መቀየር የግድ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ለትውልድ ተሻጋሪ የሆነ ሥራ መስራት ከወዲሁ እንደሚያስፈልግም ይመክራሉ፡፡

ዜና ትንታኔ
ወንድወሰን ሽመልስ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829488
TodayToday1118
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7208
This_MonthThis_Month29668
All_DaysAll_Days2829488

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።