የፍቅርና የአንድነት ኪዳን Featured

16 Apr 2018
የፍቅርና የአንድነት ኪዳን ፎቶ - በሐዱሽ አብረሃ

ዕለቱ እሁድ የዳግማዊ ትንሳኤ ቀን ነው፡፡ ይህ በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከሚከበሩ በዓላት አንዱ ቢሆንም፣ የአደባባይ በዓል አይደለም፡፡ ቦሌ አካባቢ ግን ምን በዓል አለ? በሚያስብል ድምቀት በየተለያዩ የአገር ባህል አልባሳ ትና በሰንደቅ ዓላማ ባሸበረቁ ቲሸርቶች የደመቁ በርካታ ዜጎች መንገዱን አጨናንቀውታል፡፡ 

እኛም የሚሌኒየም አዳራሽ መግቢያ ከሚገ ኝበት መንገድ አሳብረን ወደ ውስጥ ዘለቅን፡፡ በርካ ቶች የበልጉ ወቅታዊ ቅዝቃዜ ሳይበግራቸው አምረ ውና ደምቀው በግራና ቀኝ በሚገኘው የእግረኞች መንገድ ላይ ቆመዋል፡፡ ሌሎች ‹‹ስንኖር ሰው ስንሞት ሀገር እንሆናለን›› በሚል ዶክተር አብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በተሰየሙበት ወቅት ከተናገሩት ውስጥ የተቀነጨበ የአንድነት መንፈስን የሚዘራ ንግግርና የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ መለያ በሆኑት ሦስት ቀለማት የተዘጋጁ ቲሸርቶችን እየገዙ ይለብሳሉ፡፡ ዕለቱም ዳግም ትንሳዔ ነውና በስፍራው የሚታዩት ኩነቶች ድርብ ድርብርብ በዓል አስመስለውታል፡፡
በሥፍራው ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ከቀትር በኋላ ለሚካሄደው ውይይት ማልደው የተገኙት ታዳሚዎችም በዳግም ትንሳዔ ዕለት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሲከሰት የነበረውን አለመረጋጋት ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ድባቅ በመምታት ዳግም ለሰው ልጆች ሁሉ የተባለውን ሰላም ለማምጣት ቆርጠው እንደተነሱ መላ ሁኔታቸው ይናገራል፡፡ ከግል መኖሪያ ቤታቸው ወጥተው ለጋራ መጠለያ አገራዊ ቤታቸው የተነገረውን ታላቅ ቃል የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በተገኙበት ዕውን እንዲሆን ለአብሮነትና ለሰላም ቃል ሊገቡ ሰዓቱ ደረሰ አልደረሰ ስሜት ውስጥ በጉጉት ሲጠባበቁ አንዳንዶቹን ጠጋ ብለን አሁን ያለውን ሁኔታ እንዴት ይመለከቱታል ስንል አነጋገርናቸው፡፡
ህዝቡ አብሮ የመኖር እሴቱ ተሸርሽሮና እየተለያየ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን ሰላም የተፈጠረ መሆኑን ከአምቦ ለዚሁ መድረክ በስፍራው በማለዳ አዲስ አበባ የመጣው ወጣት ኪታባ ቀጄልቻ ይናገራል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ተዘዋውረው ችግሮችን ለማርገብና ወደ አንድነት የሚወስድ ሥራ መስራታቸው መልካም መሆኑን በመግለጽም ለወጣቱ ጥያቄዎች ግን ፈጣን ምላሽ መስጠት ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ተናግሯል፡፡ በመንግሥት የተገባው ቃል ተፈፃሚ ከሆነ ህብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም የአገሪቱን የሰላምና የልማት ጉዞ ለማስቀጠል ዝግጁ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡
መንግሥት ከህዝብ ጋር የመግባባት ችግር አጋጥሞት እንደነበር ያጫወቱን ደግሞ የአዲስ አበባ ነዋሪው አቶ ኃይለማርያም አበበ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን የመልካም አስተዳደር እና የሥራ አጥነት ችግሮች በመኖራቸው የህብረተሰቡ ቅሬታ ነበር፡፡ ይህም በአገሪቱ የሰላም እጦት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡ከዚህ ባለፈም በአንዳንድ አካባቢዎች ይስተዋል የነበረው የኋላቀርነትና የዘረኝነት አስተሳሰብ የህዝቡ ስነልቦና አንድነትና ስሜት ላይ ክፍተት እንዲፈጠር አድርገው ቆይተዋል፡፡
እንደ አቶ ኃይለማርያም ገለፃ መንግሥት በአሁኑ ወቅት ችግሮችን ለመፍታት እየወሰደ ባለው የለውጥ እርምጃ የተረጋጋ ሁኔታ እየመጣ ነው፡፡ በቅርቡም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር የገቡት ቃል በህዝቡ ውስጥ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡ በመሆ ኑም በእያንዳንዱ ተግባር የጋራ መግባባት ከተፈጠረና ህብረተሰቡን ባለቤት አድርጎ ከተሰራ ለውጥ እንደሚመጣ የተስፋ ጭላንጭል ማየት ተችሏል፡፡
«የፍቅርና የአንድነት ኪዳን» በሚል መሪ ሃሳብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመንግሥት ቀጣይ የሥራ አቅጣጫ አሳውቀዋል። በመድረኩ ላይ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎት የተውጣጡ ከ25 ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን ከመነሻው እስከመጨረሻውም በአን ድነት በመዘመር ለሰላምና ለአብሮነት ያላቸውን ተነሳ ሽነት አሳይተዋል፡፡
የዕለቱ መርሐግብር የተጀመረው በሃይማኖት አባቶችና በአገር ሽማግሌዎች ምርቃት ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ የታየው የተሳታፊው ድባብም ልብን የሚነካ የአብሮነትና የአንድነት ስሜትን ያንፀባረቀ ነው፡፡ በዚህ ቦታ ላይ የተገኘ ሁሉ አገሪቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከነበረችበት የሰላም ችግር ተላቃ ወደ አንድነትና ሰላም መምጣቷን ይረዳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገና ንግግር እንዲያደርጉ ሲጋበዙ በአዳራሹ የነበረው ስሜት ደግሞ የተለየ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ጥቂት ቀናት በተለያዩ አካባቢዎች ያደረጓቸው ንግግሮች ተስፋ የሚሰጡና አነቃቂ መሆናቸው ለዚህ ምክንያት እንደነበር በርካቶችም ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ንግግራቸው እንደተለመደው ለወደፊቷ ተስፋ ያላት ኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ ንግግር አድርገዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየመሃሉ በተሳታፊ ጭብጨባ ታጅበው ባደረጉት ንግግርም በርካታ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ዳሰዋል፡፡ በንግግራቸው መጀመሪያም ከዚህ ቀደም እንዳደረጓቸው ንግግሮች ሁሉ የኢትዮጵ ያን ታሪኮች ዳስሰዋል፡፡ በተለይ የአገራችን የኋላ ታሪኮች ጥንካሬን እንጂ ድክመትን እንዳላሳዩን በመጠቆም ይህንን ጥንካሬአችንን በተግባር ለመተ ርጎም መስራት እንደሚገባንም በአፅንኦት ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን የአብሮነትና የአንድነት ስሜትም ምን ያህል የጠነከረና በመደመር ላይ የተመ ሰረተ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ለዚህም የጋራ ትግል፣ ፅትና የአብሮነት መንፈስ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከቃላት በተረፈ የገቡትን ቃል በተግባር ለመፈፀም ቁርጠኛ መሆናቸውንም በንግግራቸው ውስጥ አካተዋል፡፡ ሰሞኑን ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያደረጓቸው ውይይቶች ዓላማም የጀመርናቸውን የልማት ሥራዎች በህዝባዊ ድጋፍ አጅበን ወደ ተግባር ለመግባት ጠቃሚ በመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡
«እኛ ሚሊዮኖች ሆነን እንደ አንድ ቤተሰብ መስራት ይገባናል» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለአገሩ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የመንግሥትን ኃላፊነት በተመለከተም ሲገልፁ «መንግሥት ህብረተሰቡ የሚፈልገውን ብቻ ሳይሆን የሚያስፈል ገውን የማሟላት ኃላፊነት አለበት ብለዋል»፡፡ በተለይ እያደገ የመጣውን የህዝብ ፍላጎት ለማሟላት መንግሥታቸው የማስፈፀም አቅም ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን፣ ጉቦና የጥቅም ሽርክና ጎጂ መሆናቸውን አውቆ መስራት እንደሚገባ በአፅንኦት ጠቁመው፣ በመንግ ሥት መዋቅር ውስጥ የሚደረግ ምደባም በእውቀትና በችሎታ ብቻ እንዲሆን ይደረጋል ብለዋል፡፡
የመልካም አስተዳደር ከሆኑ ችግሮች ውስጥ አንዱ በስብሰባ የሚባክን ጊዜ መሆኑ ህብረተሰቡ በተደጋጋሚ ቅሬታ እንደሚያሰማ ይታወ ቃል፡፡ ይህንን በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጤታማ ባልሆነ ስብሰባ የሚባክነውን ጊዜ ለማስተካከል አሰራሮችን በቀልጣፋና ዘመናዊ አሰራር መተካት ይገባናል ብለዋል፡፡
የአገሪቱ ኢኮኖሚ ሊለወጥና ሊያድግ የሚች ለው በህዝቡ የጋራ ጥረት በመሆኑም ህዝቡ በመደበኛ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቶ መስራት እንዳለ በት አስገንዝበዋል፡፡ ከዚህ በፊት ያጋጠመው ችግር ጊዜያዊ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ «እንዲህ አይነት ወደኋላ የመመለስ ችግሮች በዚያው መቅረት ካለ እንጂ ካለበለዚያ ግን እንደመንደርደሪያ ተጠቅመን ባቸው ወደፊት ልንራመድ ይገባል» ብለ ዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በተለይ የባከነውን ጊዜ ለማካካስ መስ ራት አለብን ብለዋል፡፡
ቀጣዩ ምርጫም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የንግግር አንዱ ጉዳይ ነበር፡፡ በዚህም ንግግራቸው ተአማኒና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ከወዲሁ በቅንጅት ለመስ ራት ቃል ገብተዋል፡፡
በንግግራቸው ትኩረት የሰጡት ሌላው ጉዳይ ወጣቱን በተመለከተ ነው፡፡ ሥራ አጥነት ወጣቶችን ለሱስ፣ ለስደትና ላልተገቡ ድርጊቶች እንደዳረጋቸው የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ ለወጣቱ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል፡፡ ወጣቶችም ይህንን ወርቃማ ጊዜ ለሥራ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ንግግራቸው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የዳሰሱ ሲሆን፣ ሁሉም ለአገራዊ አንድነት በጋራ እንዲሰለፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዜና ሐተታ
ፍዮሪ ተወልደ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829486
TodayToday1116
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7206
This_MonthThis_Month29666
All_DaysAll_Days2829486

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።