አስተውሎ የሚራምድ ብዙ ርቀት ይጓዛል! Featured

16 Apr 2018

አንዲት ትንሽዬ ከተማ ውስጥ የሚኖር አንድ አይነስውር ሰው ነበር። ይህ አይነስውር ሰው ምሽት ላይ ከከተማው መውጫ ላይ ወደሚገኘው ወንዝ እየሄደ ንፁህ አየር መቀበል ያዘወትር ነበር። ታዲያ በዛ በጨለማ ሲሄድና ሲመለስ በእጁ የበራ ፋኖስ ይዞ ነበር የሚንቀሳቀሰው። ይህን የበራ ፋኖስ ይዞ ንፁህ አየር የመቀበል ጉዳይ የሰርክ ተግባሩ አድርጎታል።
ከዕለታት በአንዱ ምሽት እንደልማዱ የበራ ፋኖሱን ይዞ በመንሸራሸር ላይ ሳለ ሶስት ወጣቶች እርስ በርስ ሲያልፉ ያገኙታል። አይነስውሩ በድቅድቅ ጨለማ በፋኖስ ብርሃን እየተመራ በመጓዙ ይገረሙና አይነስውር መሆኑን በመጠራጠር ያናግሩታል። እርሱም በጥያቄያቸው ተገርሞ በርግጥም ሲወለድ ጀምሮ አይነስውር መሆኑን ይነግራቸዋል።
«አንተ አይነስውር ከሆንክ እንዴት እንደሚያይ ሰው የበራ ፋኖስ ይዘህ ትዞራለህ?» ብለው ይስቁበታል፣ ይሳለቁበታል። ሰውዬውም በወጣቶቹ መሳቅና መሳለቅ ሳይበሳጭ በእርጋታ እንዲህ በማለት መለሰላቸው።
«ልክ ናችሁ፤ በርግጥም እኔ አይነስውር በመሆኔ አይኔ አያይም፤ ነገር ግን የፋኖሱ ብርሃን ይጠቅመኛል፤ ምክንያቱም በፋኖሱ ብርሃን እኔ በቀጥታ ባልጠቀምበትም በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቅሜ እጠቀምበታለሁ። ምክንያቱም ሰዎች በጨለማው ምክንያት ሳያዩኝ ሊገፈትሩኝ ይችላሉ። ከገፈተሩኝ በኋላ ከምናደድባቸውና ከማዝንባቸው ፋኖሱን ይዤ ባበራላቸው ሁለታችንም እንጠቀማለን» ብሏቸው ሄደ። ወጣቶቹም በሰውዬው ቅን አስተሳሰብ ተደነቁ። በአይነስውሩ ማፌዛቸው አሳፈራቸው። በርግጥም ከነርሱ የተሻለ ቅን ልብ ስላለው ከራሱ አልፎ ለሌሎች እየኖረ መሆኑ አስደነቃቸው። ከማየት ማስtዋል እንደሚበልጥ ተረዱ። ከዛን እለት ጀምሮ ህይወታቸውን ለሌሎች በማሰብና በቅንነት ለማሳለፍ ወሰኑ።
በርግጥም የምናየው በህሊናችን ሲሆን ማስተዋላችን የበዛ ይሆናል። ለሰዎች የምናደርገው በጎ ነገር በራሱ ተመልሶ በእጥፍ ይከፍለናል። ቅን ልቦች ሁልጊዜም የሚጠቅሙት ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡን እንደሆነ እንረዳለን።
አንዳንድ ጊዜ ማስተዋል ሲሳነን ነገሮችን የምናያቸው እራሳችን ለመረዳት በፈለግነው ልክ ይሆናል። አንዳንድ እውነታዎች ተዛብተው የሚተረጎሙት ለነገሮቹ በሰጠነው የፍላጎት ግመታ ሊሆን እንደሚችል ልብ ልንል ይገባል። እውነታው እኛ እንደፈለግነው ወይም ለምንፈልገው ጉዳይ ጋር ሳይገጣጠም ሲቀር ልንበሳጭ እንችላለን። ምክንያቱም እኛ የተረዳንበትና ነገሩ የተገለፀበት መንገድ የተለያያ ሊሆን ይችላልና። በተለይ ደግሞ ወጣቶች ስንሆን ነገሮችን በሰከነ መንፈስ የማየት እድላችን ሊጠብ ይችላል። ለዚህም ነው የአይነስውሩን እውነት ወጣቶቹ እራሳቸው በፈለጉትና በመሰላቸው መንገድ በመረዳታቸው የተሳሳቱት። መሳሳት በራሱ ውድቀት አይደለም፤ ከስህትት ተምሮ ወደተሻለ አስተሳሳብ መምጣት ይቻላልና። ከወጣቶቹ ታሪክ የተረዳነውም ይህንኑ ነው።
በወጣትነት ዕድሜ በርካታ ምርጫዎች ከፊታቸው ይደቀናሉ። አንዳንዶቹም በሕይታቸው ላይ ዘላቂ ተጽዕኖ ሊኖራቸው ይችላል። በአሁኑ ጊዜ የምናደርጋቸው አንዳንድ ውሳኔዎች የወደፊት ሕይወታችንን ሊያበላሹት ይችላሉ። በመሆኑም ካለፉ በኋላ ይቆጩናል። በአንፃሩ ደግሞ ጥንቃቄና ጥበብ የታከለባቸው ምርጫዎች አስደሳችና የተሳካ የሕይወት መስመር ያመላክቱናል ወይም ያደርሱናል። የዚህን ትክክለኛነት ለማየት በሕይወታችን የምናደርጋቸውን ምርጫዎች አመዛዝኖ በሚነግርን ህሊናዊ አይናችን ልናዳምጠው ይገባል።
የሀገራችን ወጣቶች የተሻለች ኢትዮጵያን ለማየት ብዙ የህይወት መስዋእትነት ከፍለዋል። ይህ መስዋእትነታቸው የታሪክ መዝገብ ከትቦት ይገኛል። አሁንም ብዙ ታሪክ የሰሩና ለመስራት የተዘጋጁ ወጣቶች አሉን። ወደፊት ታሪክ ለመስራት የሚያስብ ወጣት ደግሞ አኩሪ ታሪኮቹን ጠብቆ ለትውልድ በማስተላለፍ ረገድ የራሱን ገንቢ ሚና መጫወት ይገባዋል፡፡ እንደ ባለተራ ትውልድ የጀግኖች አባቶቹን አደራ ተቀብሎ የማስቀጠል ታሪካዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል።
ወጣቶች የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታውን ከኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ ጋር ለማስተሳሰር የሚያስችል አንድነት ሊኖራቸው ይገባል። ይህን አንድነት ለመፍጠር ደግሞ በሀገራዊ አስተሳሳቦች ላይ የጋራ ግንዛቤ ይዘው እንዲንቀሳቀሱ እድሉ ሊመቻችላቸው ይገባል።
ዛሬ ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ ወጣቶች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ውይይት አንደሚያደርጉ ይጠበቃል። ይህ ከሚፈጠሩት መልካም አድሎች መካከል ተቀዳሚው ነው። ከዚህ ውይይት የወጣቶች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ ለሀገር እድገት በሚኖራቸው አስተዋፅኦና በመሰል ጉዳዮች መግባባት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። በመመካከር የተሻለች ኢትዮጵያን መፍጠር እንችላለን። የዚህ ሁሉ ማጠንጠኛው ደግሞ አስተውሎት የተሞላበት አስተሳሰብን ማጎልበት ነው። ከቅርብ ጊዜ ታሪካችን የተረዳነው አስተውሎት በጎደለው ጉዟችን ብዙ ስህተቶችን ፈፅመናል። በቀላሉ ልንመልሳቸው የማንችላቸውን የህይወትና የንብረት ጥፋት አድርሰናል። ይህ ስህተት መሆኑን ካመን ከስህተት መማር ብልህነት በመሆኑ ዛሬ በአዲስ አስተሳሰብ ለኢትዮጵያችን ብልፅግና መስራት ይኖርብናል። አስተውሎ የሚራምድ ብዙ መንገድ ሊጓዝ ይችላልና።

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829498
TodayToday1128
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7218
This_MonthThis_Month29678
All_DaysAll_Days2829498

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።