በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት አውሮፓዊው ጤፍ Featured

16 Apr 2018

የጤፍ ምርትን የማቀነባበር የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት መብት (ፓተንት) በአውሮፓው የኔዘርላንድ ኩባንያ ከአሥር ዓመት በፊት ተይዟል። ኢትዮጵያ የባለቤትነት መብቱ ያለአግባብ ተወስዶብኛል እያለች ስትጠይቅ ብትቆይም እስካሁን ጉዳዩ እልባት አላገኘም።

የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማርዮ እንደሚሉት፤ በጀርመን እና ሌሎች አምስት አገራት ውስጥ ጤፍ በዱቄት መልክ አዘጋጅቶ ወይም በዱቄቱ ኬክ ሰርቶ ለመሸጥ ተቀባይነት ያለው የጤፍ ብቸኛ የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤት የሆነው የኔዘርላንዱ ኩባንያ ነው።
‹‹ጤፍ ግሉቲን ከሚባል አሚኖ አሲድ ነፃ ነው›› የሚሉት ዶክተር መለሰ፣ ይህ የተፈጥሮ ይዘት ከጤና አንፃር ተፈላጊነቱ በዓለም ላይ መጨመሩን፣ ጤፍ በቀጣይ ዓመታት የሚኖረውን ተፈላጊነት በማሰብ ኢትዮጵያ በበላይነት ገበያውን ለመቆጣጠር ያላትን ዕድል ለመጠቀም የመብት ባለቤትነቷን መረከብ እንደሚኖርባት ያብራራሉ። ይህ ከሆነ በህጋዊ መንገድ ጤፍን ለአውሮፓ ገበያ ማቅረብ ይቻላል። ጤፍን በውድ ዋጋ ለዓለም ገበያ የማቅረብ ዕድል እንዲፈጠር፣ አርሶአደሮችም የበለጠ ለማምረት እንዲነሳሱ ማድረግ እንደሚያስችል ያብራራሉ፡፡ የባለቤትነት መብት ማግኘቱ ለአገርም ዕውቅና ያሰጣል ይላሉ፡፡
ድርጊቱ ከኢኮኖሚ ጉዳትም በላይ የማንነት ማጭበርበርን የሚያሳይ ክስተት የታከለበት ነው የሚሉት ዶክተር መለሰ፣ የባለቤትነቱን መብት ወደ ኢትዮጵያ ማስመለስ መቼም ቢሆን ችላ ሊባል እንደማይገባ ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ጊዜያዊ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤርሚያስ የማነብርሃን እንደሚገልጹት፣ በአሁኑ ወቅት የጤፍ ምርት በአምስት የአውሮፓ አገራት የሚታወቀው የኢትዮጵያ በሚል ሳይሆን በአንድ የኔዘርላንድ ኩባንያ በሚዘጋጅ የምግብ አይነት ነው። ይህ ስሙን የሚቀያይር ኩባንያ፣ በአውሮፓ አዕምሯዊ ንብረት (ፓተንት) ቢሮ በኩል በተወሰኑት የአውሮፓ አገራት የጤፍ ማቀነባበር መብትን አግኝቷል።
በቅድሚያ ኩባንያው በተጭበረበረ መንገድ ያገኘውን የባለቤትነት መብት ማሰረዝና ቀጥሎም ጤፍ የኢትዮጵያ መሆኑን ማስመዝገብ እንደሚገባ የሚገልጹት አቶ ኤርምያስ፣ ለዚህም ድርድርን፣ ህዝባዊ ዘመቻን እና የህግ አግባብን መጠቀም እንደሚገባ ያመለክታሉ።
‹‹የጤፍ ጀነቲክ ሃብት የተጠበቀበት ሁኔታ ደካማ ነው›› የሚሉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሳይንስ፣ መገናኛ እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው መለሰ ናቸው። ጉዳዩ መነሳት ከጀመረ ከአሥር ዓመታት ወዲህም ቢሆን ኢትዮጵያ ውጤታማ ተግባር አለማከናወኗን ይጠቁማሉ፡፡የውጭ ሀገሩ ኩባንያ በየአገራቱ የተሰጠው ፈቃድ በአንዳንዶቹ በኩል በሁለት ዓመታት ውስጥ ስለሚጠናቀቅ ማሳደስ እንደሚጠበቅ ይገልጻሉ።ይህ የጊዜ ገደብ ደግሞ ለመጠናቀቅ የሚቀሩት የተወሰኑ ወራት መሆናቸውን በመጥቀስም፣ ኩባንያው ፈቃዱን ከማሳደሱ በፊት ኢትዮጵያ የቤት ሥራዋን ማጠናቀቅ እንደሚገባት ያመላክታሉ።
‹‹የድርጅቱ የጤፍ ማቀነባበር የባለቤትነት መብት እንዲሰረዝ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ጥረት ቢደረግም ወጤቱ አዝጋሚ ነው›› የሚሉት ዶክተር መለሰ፣ ወደ ህግ አግባብ የመግባት አስፈላጊነትን ይጠቁማሉ፡፡ ኩባንያው ከአንዴም ሦስት ጊዜ ስሙን እየቀያየረ እና መብቴን ለሌላ ድርጅት ሸጫለሁ እያለ ማወናበዱ የመብት ጥያቄውን ውስብስብ እንዳደረገው ያመለክታሉ፡፡ አሁን በአገር አቀፍ ደረጃ መብቱን ለማስመለስ የሚደረገውን ጥረት እንዲከታተል የተቋቋመው ኮሚቴ ጉዳዩን በትኩረት ሊይዘው እንደሚገባም ያስገነዝባሉ።
እንደ ዶክተር መለሰ ማብራሪያ፤ በጤፍ የባለቤትነት መብት ላይ ኢትዮጵያ ያነሳቸውን ጥያቄ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ለማቅረብ ጥናት እየተደረገ ይገኛል። ለፍርድ ሂደቱ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ማሰባሰብ ይገባል። በተለይ በጤፍ እና በጤፍ ምርት ሂደቶች ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሁፎች እና ጥልቅ መረጃዎችን ማደራጀት ያስፈልጋል። ይህም በፍርድ ቤት አሸንፎ ህገወጥ መብቱን በማሰረዝ ኢትዮጵያን ባለመብት ለማድረግ ወሳኝ ነው።
አቶ ኤርሚያስም በዚህ የዶክተር መለሰ ሀሳብ ይስማማሉ። እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ጉዳዩ የህግ መፍትሄ ያስፈልገዋል። ኢትዮጵያም በድርድር፣ በህዝባዊ ዘመቻ እና በህግ መንገዶች ተጠቅማ መብቱን ለማግኘት ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። የድርድሩ ውጤት ብዙም አጥጋቢ ባይሆንም በዘመቻ መልክ በሰፊው ጤፍ የኢትዮጵያ መሆኑን ዓለም እንዲያውቀው ማድረግ ይገባታል። ያለፈውን እየወቀሱ ከመቀመጥ ጉዳዩ በህግ አግባብ እንዲፈታ ማድረግ ሁነኛው አማራጭ መሆን አለበት።
ጉዳዩን በህግ ፊት አቅርቦ በፍትህ መንገድ ፈቃዱን ማሰረዝ እንደሚገባ የሚናገሩት አቶ ኤርምያስ፣ ለኢትዮጵያ ጠበቃ ቀጥሮ ተከራክሮ በመርታት የኩባንያውን መብት ማሰረዝ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ።
አቶ ጌታቸው እንደሚገልጹት፤ የዓለም አቀፉ የአዕምሯዊ ንብረት ተቋም በኢትዮጵያ የጤፍ መብት ላይ በሚነሳው ጥያቄ ተመስርቶ ባቀረበው ሃሳብ መሰረት የጤፍ ምርት ባለቤትነትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከመጠየቅ አስቀድሞ በአገር ውስጥ ማስመዝገብ ይገባል። እስከ አሁን ጤፍ በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት አልተመዘገበም። የኩባንያውን ፈቃድ ለማሰረዝ ጥረት ከማድረግ አስቀድሞ በአገር ውስጥ ማስመዝገብ ያስፈልጋል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የዓለም አቀፍ ባለመብትነት እውቅና ማግኘት በብቸኝነት ምርቱን በተፈለገው መንገድ ለመሸጥ እና ለመጠቀም ፍቃድ እንደ ማግኘት ይቆጠራል። በኢትዮጵያ እና ሄልዝ ኤንድ ፐርፎርማንስ ፉድ ኢንተርናሽናል በሚባል የኔዘርላንድ ኩባንያ መካከል በተደረገ ስምምነት መሰረት ኩባንያው በኢትዮጵያ የጤፍ ዝርያዎች ላይ 12 ዓይነት የምርምር ሥራ እንዲያከናውን ፍቃድ ተሰጥቶት ነበር። ኩባንያው ከአራት ዓመታት በኋላ 'ኪሳራ ደርሶብኛል' በሚል ሥራውን ቢያቆምም፣ ከአውሮፓ የአዕምሯዊ ንብረት ጤፍን በዱቄት፣ በፓስታ፣ በብስኩት እና በሌሎች መልኩ አቀነባብሮ የማዘጋጀት እና የመነገድ መብት አግኝቷል።
በኔዘርላንድ፤ በብሪታኒያ፣ ጣሊያን፣ ቤልጅየም፣ ጀርመን መብቱን አግኝቶ እየተጠቀመበት ይገኛል። ኢትዮጵያ ይህን ህገወጥ መብት ለማሰረዝም በአገር አቀፍ ደረጃ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚመራ ኮሚቴ ያዋቀረች ሲሆን፤ በኮሚቴው ውስጥም የውጭ ጉዳይ፣ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ፅህፈት ቤት፣ የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት በአባልነት ከተካተቱት መካከል ይገኙበታል።
ዶክተር መለሰ የክስ ሂደቱን በተጠናቀረ መረጃ በተደገፈ ሥርዓት አከናውኖ መርታት ካልተቻለ ከጤፍ ምርት ጋር ተያይዞ የሚደርሰው ኢኮኖሚያዊ እና የማንነት ኪሳራ አገሪቷን ይጎዳታል ሲሉ ስጋታቸውን ይጠቁማሉ። በተለይ ጤፍ አቀነባብረው ለመላክ በርካታ ሃብት ሥራ ላይ ያዋሉ ዜጎችን ተስፋ እንደሚያጨልም በማመልከት መጠንቀቅ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡
አቶ ኤርሚያስ ጤፍን አቀነባብሮ የመጠቀም እና የመሸጥ መብትን ከአውሮፓው ኩባንያ ማስመለስ ካልተቻለ ጤፍን በእንጀራ መልክ እና በዱቄት መልክ ወደአውሮፓ የሚልኩ ኢትዮጵያውያን ተቀባይነት እንደማያገኙ በመጠቆም፣ ይህም በአገሪቷ ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራዎች እንዲደርሱ ያደርጋል ይላሉ።
እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ፤ ኩባንያው ባለቤትነት መብቱን በየአገራቱ ከማሳደሱ በፊት ኢትዮጵያ በአገሯ ጤፍን በመመዝገብ መረጃዎችን ይዛ በመገኘት መከራከር ትችላለች። ለዚህ ደግሞ የአገር ውስጥ ምዝገባው መጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ወደ አውሮፓም ሆነ ዓለም አቀፉ የአዕምሯዊ ንብረት በመሄድ የመብት ጥያቄ ለማቅረብ መሞከር ትርፉ ኪሳራ እንደሚሆን በመጠቆምም ቅድሚያ በሀገር ውስጥ ምዝገባው መካሄድ እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡  

 

ዜና ትንታኔ
ጌትነት ተስፋማርያም

 

 

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829499
TodayToday1129
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7219
This_MonthThis_Month29679
All_DaysAll_Days2829499

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።