በ32 አልጋዎች 65 ጨቅላ ህፃናት Featured

16 Apr 2018

በክፍሉ በበራፍ ሁለት ጥበቃዎች በቀኝና በግራ ተቀምጠዋል። ወለሉ ላይ ደግሞ ህጻናቱን የሚጠብቁ ሰዎች ካርቶን አንጥፈው ስማቸው እስኪጠራ ጋደም ብለው ይጠባበቃሉ። በአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የጨቅላ ህፃናት ህክምና ክፍል ውስጥ ትርምስምስ ያለ እንቅስቃሴ ይስተዋላል። ወደክፍሉ ሲገባ የታመቀው አየር እንኳን ለህጻናቱ ይቅርና አዋቂውን ይረብሻል። በተለይ ደግሞ የተለያዩ አልኮል ነክ የህክምና መስጫ ግብዓቶች ሽታ ሲጨመርበት አስም ለያዘውና በቀላሉ መተንፈስ ለማይችል ሰው አስቸጋሪ ነው። ክፍሉ ውስጥ ያሉት ህጻናት ይህን መተፋፈግ እንዴት እንደተቋቋሙት ለመመልከት መግባት ነበረብኝና ወደ ውስጥ ገባሁ። 

በክፍሉ በስተግራ በ«ካንጋሮ ስታይል» የሙቀት ህክምና የሚሰጥበት ክፍል አለ። በስተቀኝ ደግሞ የመተንፈስ ችግር ያለባቸው፣ ሙቀት የሚያስፈል ጋቸውና ያለጊዜያቸው የሚወለዱ ህጻናት የሚያርፉ በት ክፍል ይገኛል። የሙቀት ክፍሉ የሚሰጠውን አገልግሎት ለመመልከት ወደ ውስጥ ገባሁ። በአንድ አልጋ ላይ ሦስት ህፃናት ተኝተዋል። ባስ ሲልም በአንድ አልጋ ላይ አራት ህጻናት እንደሚተኙ ያገኘኋቸው ነርስ ነግረውኛል።
በጠባቧ ክፍል ውስጥ ያሉት የሙቀት መስጫ መሳሪያዎች ደግሞ ይበልጥ ክፍሉን አጨናንቀውታል። አማራጭ ባለመኖሩ በክፍሉ ከ40 እስከ 65 የሚደርሱ ህጻናትን እንደሚቆዩ በአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የጨቅላ ህፃናት አይሲዩ ዲፓርትመንት ኃላፊ ሲስተር ትዕግስት ደሪባ አረጋግጠውልኛል።
ሲስተር ትዕግስት እንደሚናገሩት፤ በሆስፒታሉ የቦታና መሳሪያ እጥረት እንዲሁም የአልጋ ውስንነት በመኖሩ ጨቅላ ህፃናትን በተገቢው መንገድ ማስተናገድ አልተቻለም። በተለይም በሙቀት መስጫ መሳሪያ እጥረት የተነሳ በአንድ አልጋ ላይ የተለያየ ህመም ያለባቸው ህጻናት ይተኛሉ። የመተንፈስ ችግር ያለባቸውንና ሙቀት የሚያስፈልጋቸው ህጻናትም በአንድ አልጋ ላይ በማስተኛት አንድ አይነት የሙቀት መጠን ይሰጣቸዋል። ይህ ደግሞ የጨቅላ ህጻናቱን የሞት ቁጥር እንዲጨምር መንስኤ ሆኗል።
«በጤና ህግ መሰረት በተለያዩ በሽታዎች የተያዙ ህጻናትን እንኳን በአንድ አልጋ በአንድ ክፍል ውስጥ ማስተናገድ ያስጠይቃል» የሚሉት ሲስተር ትዕግስት፤ ከችግሩ ግዝፈት የተነሳ በአንድ አልጋ ላይ አንድ የማሞቂያ መሳሪያ ተጠቅሞ ሦስት ህጻናት እንዲተኙ ተደርጓል። በ24 ሰዓት ውስጥ በሆስፒታሉ ያለጊዜያቸው የሚወለዱ ህጻናት ቁጥር እስከ 20 ይደርሳል። ከተለያዩ የህክምና ተቋማት ሙቀት ፍለጋ ወደሆስፒታሉ የሚመጡ ህፃናት ደግሞ በየቀኑ በአማካይ እስከ 70 እንደሚደርስ ይገልጻሉ። ስለዚህም ህጻናቱን ለማትረፍ ሲባል በተጨናነቀ ቦታ ማከሙ ግድ እንደሆነባቸው ያስረዳሉ።
‹‹በክፍሉ ያሉት አልጋዎች 32 ብቻ ናቸው። ህጻናቱን ለደቂቃ ህክምናውን ካላገኙ እንደሚሞቱ ይታወቃልና በአንድ ጊዜ ከ40እስከ 65 ልጆች በክፍሉ እንዲቆዩ ይደረጋል። ለአንዱ የሚያስፈልገው የሙቀት መጠንና ለሌላው የሚያስፈልገው የሙቀት መጠን መለያየቱ ቢታወቅም አማራጭ ባለመኖሩ በአንድነት እንዲጠቀሙም ይደረጋል›› ይላሉ ሲስተር ትዕግስት። አሰራሩ ህክምና ያገኙትንም ሆነ የማያገኙትን ህጻናት ለከፋ ጉዳት እየዳረጋቸው መሆኑ ግልጽ መሆኑን ያስረዳሉ። በተጨማሪም የባለሙያ አለመሟላት አስፈላጊውን አገልግሎት ለመስጠት እንዳላስቻለ የሚናገሩት ሲስተር ትዕግስት፤ በቂ ነርሶች መሟላት እንዳለባቸው ያሳስባሉ። የቅጥር ሁኔታው በደረጃ ሲቀመጥ ለሁለት ጨቅላ ህጻናት አንድ ነርስ ቢያስፈልግም በክፍሉ ያሉት ነርሶች ግን 6 ብቻ ናቸው። በአማካይ ለ65 ህጻናት እያገለገሉ ይገኛሉ። በመሆኑም ኮሌጁ በቂ የሰው ኃይል፤ ግብዓትና አስፈላጊው የህክምና ስታንዳርድ ለመሟላት አስቸኳይ ምላሽ ይሻል ይላሉ።
የሆስፒታሉ ፕሮቮስት ዶክተር ስለሺ ጋሩማ በበኩላቸው፤ በተጣበበ ቦታ ላይ ህክምናው እየተሰጠ መሆኑን አምነው ችግሩን ለማቃለል ከጤና ቢሮና ከአጋር አካላት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ያስረዳሉ። ነገር ግን በተቋሙ የመሳሪያ እጥረት አለ በሚለው አይስማሙም። በቂ የህክምና መሳሪያ ቢኖርም ቦታ ባለመኖሩ ተመላሽ በመሆኑ አገልግሎቱን በበቂ ሁኔታ መስጠት አለመቻሉን ያስረዳሉ። ነገር ግን ወደሌላ ህንፃ ለማዛወር በመታሰቡ በቂ የሙቀት መስጫ መሳሪያ እንዲኖር የሚያግዝ እንደሚሆን ይገልጻሉ። አዲስ ህንጻ እየተገነባ በመሆኑ እና ከሌሎቹ የህክምና ክፍሎች የተለየ ትኩረት በመሰጠቱ በሳምንታት ውስጥ ለህጻናቱ የተሻለ ክፍል እንደሚዘጋጅ ይናገራሉ።
የነርሶችን ጉዳይ በተመለከተም በውጭ አገራት ያለውን ደረጃ ማለትም ለአንድ ጨቅላ ህጻን ሦስት ነርስ መጠቀም ላይ ለመድረስ ትኩረት ሰጥተው በመስራት ላይ መሆናቸውን የሚናገሩት ዶክተር ስለሺ፤ በየጊዜው የተገልጋዩ ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ ችግሩ አዲሱ ህንጻ ውስጥ ቢገባ በቀላሉ እንደማይፈታ ይናገራሉ። ስለዚህ ቋሚ መፍትሄ ለማበጀት በየጊዜው የቦታም ሆነ የግብዓት እንዲሁም የነርሶችን ቁጥር ለማሳደግ ተጨማሪ ጥረት ይጠይቃል። መንግሥትም ተጨማሪ ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል።
ያለጊዜያቸው የተወለዱ ህጻናት በብዛት እንዲሞቱና የተጠቃሚዎች ቁጥር እንዲበራከት ያደረገው ዋነኛ ምክንያት የሙቀት ህክምናን የሚሰጡ ተቋማት በአካባቢው ያለመኖራቸው መሆኑን የሚያስረዱት ዶክተር ስለሺ፤ አሁን ላይ አገልግሎቱ በጤና ጣቢያ ደረጃ እንዲሰጥ ለማድረግ የህክምና መሳሪያ ከአጋር አካላት በመረከብ ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።
የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ዋቆ እንደሚሉት፤ ተገቢውን ሙቀት አለማግኘት ለጨቅላ ህጻናት ሞት ምክንያት በመሆን ሰፊውን ድርሻ ይይዛል። ስለዚህም ችግሩን መቅረፍ የሚቻለው በቂ መሳሪያዎች ሲኖሩና ቦታዎች ምቹ ሲሆኑ ነው። በመሆኑም በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የህክምና የመሳሪያ ችግር በተቻለ መጠን እንዲፈታ ዩኒሴፍ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁሟል።
በአገሪቱ በአማካይ በቀን29 ህጻናት የሚሞቱ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከልም ብዙውን ቁጥር የሚይዙት ካለጊዜያቸው የሚወለዱ ህጻናት መሆናቸውን ዩኒሴፍ ያወጣው መረጃ ያመላክታል። ለሞታቸው መንስኤ የሆነውም የህክምና መሳሪያ እጥረትና ለህጻናቱ ትኩረት አለመስጠት መሆኑንም ያስቀምጣል። 

 

ዜና ሐተታ
ጽጌረዳ ጫንያለው

 

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829512
TodayToday1142
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7232
This_MonthThis_Month29692
All_DaysAll_Days2829512

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።