በፓርቲዎች መካከል ያለው ልዩነት ከአገር በላይ አይደለም Featured

14 Apr 2018

ኢትዮጵያ የምትከተለው የመድበለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ነው።በዚህም የተነሳ በአገሪቱ ከ60 በላይ የፓለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው በህጋዊና በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገሪቱ የዲሞክራሲን ስርዓት ከማጎልበት አኳያ ከፍተኛ ሚና መጫወት ቢችሉም በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈለገውን ሚና እየተወጡ አይደሉም፡፡
በአገራችን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት አለመጎልበት መንስኤ ዙሪያ ደግሞ መንግስትና ተፎካካሪ ፓርቲዎች አንዱ ሌላውን ጥፋተኛ ያደርጋል፡፡መንግስት በአገሪቱ ዲሞክራሲን ማስፈን የሕልውና ጉዳይ ስለሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል የመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርዓት ተፈጥሯል ቢልም በአንጻሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የፖለቲካ ምህዳሩ ‹‹ጠቧል መፈናፈኛም አጥተናል››የሚል ሮሮ ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሰየማቸውን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር ከዚህ በፊት የነበረውን ሁኔታ ለመለወጥ መንግስት እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡ ከኢህአዴግ ውጭ ያሉ ፓርቲዎችን እንደ ተቃዋሚ ሳይሆን እንደ ተፎካካሪ፣ እንደጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም፣ አማራጭ ሃሳብ አለኝ ብሎ እንደመጣ አገሩን እንደሚወድ የዜጋ ስብስብ እንደሚታዩም ገልጸዋል። የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎችን ደግሞ አብሮነታችንንና ሰላማችንን አደጋ ላይ ከሚጥሉ፤ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንንም አሳልፈው ከሚሰጡ የአስተሳሰብ መስመሮችን ወጥተው በአርቆ አስተዋይነትና ሀገራዊ ፍቅር፤ በሰጥቶ መቀበል መርህ የተሻለ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር መንግስት የሚያደርገውን ጥረት እንዲያግዙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ይህን ተከትሎም የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለመነጋገር የገቡትን ቃል የሚቀበሉትና ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረትም ድጋፍ እንደሚያደርጉ በተለያየ መንገድ አሳውቀዋል፡፡ይህ መልካም ጅምር ነው፡፡በሃገር ጉዳይ ሁሉም የጋራ አመለካከት እንዲይዝ፣ልዩነትን በሰለጠነ መንገድ የማሥተናገድ ባሕል እንዲዳበር በር ይከፍታልና ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
አገርን ዋና ማዕከል አድርጎ የተለያዩ ፍላጎቶችና ጥቅሞች ተቀራራቢ ወደ ሆነ ፍላጎትና ጥቅም ለመምጣት በመንግስት በኩል የውይይትና የክርክር መድረኮች በማዘጋጀት የዳበረ ዲሞክራሲን በአገር ደረጃ ለማምጣት ወሳኝ ነው፡፡ለዚህ ደግሞ በዋናነት መንግስት ከፍተኛውን ሚና መጫወት አለበት።
መንግስት የዲሞክራሲ ተቋማት በማጠናከርና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ውይይትና ክርክር በማካሄድ፣ በተመሳሳይ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በጣም ጽንፍ ከወጣ አቋም ወጥተው ልዩነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ በሚያደርጉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ አብሮ መስራትን ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል፡፡ይህም የዲሞክራሲያዊ ስርዓቱን ለማጎልበትና መድበለ ፓርቲ ፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የሚያስችል ይሆናል።
ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ ሀሙስ ሚያዚያ 4 ቀን 2010 ዓ.ም ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ለሲቪክ ማህበራት መሪዎች፣ለኪነጥበብ ባለሙያዎች፤ታዋቂ ግለሰቦችና ሌሎችም ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች በብሄራዊ ቤተ መንግስት የእራት ግብዣ ባደረጉበት ንግግር ‹‹ኢትዮጵያ ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ከመቼውም ጊዜ በላይ በምትፈልግበት ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን ለለውጥ ዝግጁ ማድረግ አለባቸው፡፡ከፓርቲ አጥር የሚሻገር የሰውነትና የኢትዮጵያዊነት ድልድይ ያስፈልገናል፡፡ ሁላችንም ትላንት ያለፍንበትን ምስቅልቅል ከመማሪያነት ባለፈ ላናስበው በመዝጋት ለተሻለች ነገ በጋራ ልንገነባ ይገባል›› ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት መንግስት ያለውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል፡፡
የዴሞክራሲ ግንባታ ካለ ፖለቲካ ፓርቲዎች ቀጥተኛ እና ሙሉ ተሳትፎ ሊሳካ ስለማይችል ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ፣ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮቻችን ላይ የእኔነት ስሜት ኖሯቸው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነት ከአገር በላይ ስለማይሆን ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ በተለያዩ የጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ አብረው መስራት አለባቸው፡፡ ልዩነቶች ሲኖሩም ምክንያታዊ በሆነ መልኩ መፍታትና የማስተናገድ ዕድልን መፈጠር ይኖርባቸዋል፡፡ መቻቻልና ሰጥቶ የመቀበል መርህን በማጎልበት ለህዝብ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት ተገቢ ነው፡፡
ለመድበለ ስርዓቱ መጎልበት ፓርቲዎች ያለባቸውን አገራዊና ህዝባዊ ኃላፊነት በአግባቡና በብቃት ለመወጣት ዝግጁና ቁርጠኛ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡አሁን የተጀመረው በጎ ጅምር ዳር በማድረስ የህዝቡንም ሆነ የአገሪቱን ጥቅም ማስጠበቅ ይቻላል፡፡ ገዥው ሆነ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰለጠነ የፖለቲካ መድረክ ያለመግባባቶችንና ልዩነቶችን ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ማጥበብ ለአገር ሰላም፣ ዲሞክራሲና ልማት ግንባታ ወሳኝ ሚና መጫወት የነገ የቤት ስራቸው መሆን አለበት፡፡ምክንያቱም ያላቸው ልዩነት ከሃገር በላይ አይደለምና፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829503
TodayToday1133
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7223
This_MonthThis_Month29683
All_DaysAll_Days2829503

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።