ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ Featured

14 Apr 2018

የብዙዎችን ቀልብ ከሚስቡ ፍክክሮች መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች ውድድር በዓለም ወደር የማይገኝለት ሆኗል፡፡ እንደዚህ ዓይነት የሞቀ ፉክክር በኢትዮጵያ ከታዩባቸው ጊዜያት ውስጥ ደግሞ የ1997ቱ ምርጫ የማይዘነጋ ሆኖ አልፏል፡፡ ከዛን ጊዜ ወዲህ ፉክክሩ የህዝብን ቀልብ በመሳብ በኩል ሳይዋጣለት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክር አስመልክቶ አጀንዳ የመሆኑም ጉዳይ ተቀዛቅዟል፡፡
በሠላማዊ የሥልጣን ሽግግሩ ግን የብዙዎችን ቀልብ በሳበው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ንግግር በተላለፉ መልዕክቶች የፖለቲካ ፓርቲዎችን የተመለከተው ሃሳብ ተጠቃሽ ሆኗል፡፡ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካፓርቲዎች በአዲስ መንፈስና ጉዞ እንዲንቀሳቀሱ ደማቅ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡ አማራጭ ሃሳቦችን በመያዝ ለህዝብና ለአገር ልማት የመትጋት ግብዣ ተላልፎላቸዋል፡፡ መንግሥት የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ ፓርቲዎችን በንቃት የማሳተፍ ፅኑ ፍላጎት እንዳለው በአደባባይ ተነግሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ «ከኢህአዴግ ውጪ ያሉ ፓርቲዎችን የምናይበት መነፅር እንደተቃዋሚ ሳይሆን እንደተፎካካሪ፣ እንደጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም፣ አማራጭ ሃሳብ አለኝ ብሎ እንደመጣ አገሩን እንደሚወድ የዜጋ ስብስብ ነው» ማለታቸውን ተከትሎ ጠንካራ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ይኖራል የሚል ተስፋን አጭሯል፡፡ በእርግጥ ጠንካራ ፖለቲካ ፓርቲ መገለጫ ምንድን ነው?
የወለጋ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ አቶ ዳባ ዱቤ ‹‹ ህዝብን የሚጠቅም አጀንዳና ያንንም የሚያስፈፅም ስትራቴጂ ያለው ፓርቲ ጠንካራ ፓርቲ ነው›› ሲሉ፤ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቱ ዶክተር አባተ ጌታሁን በበኩላቸው፤ አንድ ፓርቲ ዘመን ተሻጋሪ ትልቅ ራዕይ ያለው መሆን አለበት ይላሉ፡፡
እንደ ዶክተር አባተ ገለፃ፤ ፓርቲ ራዕዩን ለማስፈፀም የራሱ ደንብና ህግ ሊኖረው ይገባል፡፡ ህግ አውጪው፣ ህግ ተርጓሚውና ህግ አስፈፃሚው በነፃነት እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ይጠበቅበታል፡፡ መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ የዴሞክራሲ ተቋማት በነፃነት እንዲሰሩ የሚፈቅድ፤ በህዝብ ፍላጎት የሚያምን፤ የሃሳብ የበላይነትን የሚቀበል መሆን አለበት፡፡ አንድ ፓርቲ ፖሊሲ ስላለው ብቻ ጠንካራ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ፖሊሲው ሊተገበር የሚችልና የህዝብን ፍላጎት ማዕከል ያደረገ ከመሆኑም በላይ የማስፈፀሚያ ስትራቴጂ ሊኖረው ይገባል፡፡ ፖሊሲው ከህዝብ ጋር ያልተቆራኘለት ፓርቲ ጠንካራ አይደለም፡፡
‹‹አፄ ቴዎድሮስ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ለማስፈን ጥረት አድርገዋል፤ በታክስ እና በቤተክርስቲያን አስተዳደር ላይ ማሻሻያ አድርገዋል፡፡ ይህ ስህተት ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በህዝቡ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው አድርጓል፡፡ 100ሺ የነበረው የሠራዊታቸው ቁጥር ወደ 10ሺ አሽቆልቁሏል›› የሚሉት ዶክተር አባተ፤ ጠንካራ ፓርቲ ህዝብ የሚቀበለውንና ሊተገበር የሚችልን ፖሊሲ ማውጣት ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡ ህዝቡ ፓርቲውን ካልተከተለውና ካልተቀበለው ምንም ያህል ፖሊሲና ስትራቴጂ ቢኖረው ጥንካሬው እንደሚጠፋ ይናገራሉ፡፡
በህዝብ ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ለሙያቸው ክብር የሚሰጡ ምሁራኖችና በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሙያዎችን ቢያካትት ፓርቲው ይበልጥ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችልም ዶክተር አባተ ይጠቁማሉ፡፡ ትልቅ ሃሳብ ይዞ መነሳት ሌላው የፓርቲ ጥንካሬ መሰረት መሆኑን አክለዋል፡፡ ‹‹ዓለምን እየመራ ያለው ሃሳብ (አይዲያ)›› በማለት፡፡
ጠንካራ ፓርቲ በህዝብ ተቀባይነት ያለው መሆን እንዳለበት የሚናገሩት የዲላ ዩኒቨርሲቲው መምህሩ አቶ ሙህዲንም የፓርቲው አባላት የእርስ በርስ ግንኙነትና ቁርጠኝነት የጠንካራ ፓርቲ መገለጫ ነው ይላሉ፡፡ ሁሉም የፓርቲው አባላት ተጨባጭ ግብ አስቀምጠው ለስኬቱ መንቀሳቀስ እንደሚኖርባቸው ያስረዳሉ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ በበኩላቸው፤ ህዝባዊ መሰረት ያለው፣ ዴሞክራሲያዊ፣ የሌሎችን ሃሳብ የሚቀበል፣ የአገሪቷን ብሔራዊ ጥቅም አስጠብቆ ወደ ፊት የሚጓዝ ጠንካራ ፓርቲ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ፓርቲ መውደቁና መሞቱ አይቀርም›› ይላሉ፡፡ ተቀባይነትን ያገኘ ፓርቲ ‹‹የሃብት ችግር አያጋጥመውም፤ ህዝብ ይደግፈዋል፤ ያዋጣለታል፤ በስብሰባ ይሳተፍለታል›› በማለት የህዝብን ተቀባይነት ማግኘት ወሳኝ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ዶክተር ሃብታሙ ተካም ለፓርቲ የህዝብ ተቀባይነት ወሳኝ እንደሆነ ያሰምሩበታል፡፡ የጠንካራ ፓርቲ መገለጫ በዋናነት የህዝብን ፍላጎት ማዳመጥና መተግበር መቻል ነው ይላሉ፡፡ የህዝብን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ የቻለ ተቀባይነቱ እንደማያጠያይቅ ይገልፃሉ፡፡
የህዝብን ፍላጎት ለማርካት ራዕይ ያለው፣ ተልዕኮውን በትክክል ቀርፆ ለስኬት የበቃ ፓርቲ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት እንደማይቸገር ዶክተር ሀብታሙ ያስገነዝባሉ፡፡ ይህም የጠንካራ ፓርቲ መገለጫ መሆኑን በማውሳት ፓርቲው ሁሉንም እኩል ሊያይ እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡ የህዝብን እኩል ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚጠበቅበትም ያክላሉ፡፡
ያለዕውቀት አገርን መምራት አይቻልም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ የወደፊቱን የሚያስብ፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን የሚገምቱና የሚያውቁ ተገቢውን ዕውቀት የጨበጡ አባላቶች ሊኖሩት ይገባል፡፡
እንደምሁራኑ ገለፃ፤ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘት፤ ትልቅ ራዕይን መሰነቅ፤ በህግና መመሪያ መመራት፤ ሁሉንም እኩል ሊጠቅም የሚችል ፖሊሲ ቀርፆ በስትራቴጂ በመመራት ለውጥ ማምጣት የጠንካራ ፓርቲ መገለጫዎች ናቸው፡፡

 

ዜና ሐተታ
ምህረት ሞገስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829504
TodayToday1134
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7224
This_MonthThis_Month29684
All_DaysAll_Days2829504

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።