የመረጃ እጦትና የፍትህ መዘግየትን የሚፈታ ሥርዓት ይዘረጋል Featured

14 Apr 2018

አዲስ አበባ፡- የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የመረጃ እጦትና የፍትህ መዘግየትን በመቅረፍ ጥራት ያለው፣ ቀልጣፋ፣ ተገማችና ተደራሽ የፍትህ ሥርዓት ለማስፈን የሚያስችል ብሄራዊ የተቀናጀ የመረጃ ሥርዓት ለመዘርጋት ከሦስት ኩባንያዎች ጋር ተስማማ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ከትናንት በስቲያ ስምምነቱን የፈረመው ጨረታውን ካሸነፉት ኢሲክስ (ISYX) ቴክኖሎጂና አልረዋድ (ALROWAD) ኩባንያዎችና ከአገር በቀሉ አፍሪኮም ቴክኖሎጂጋር ነው።
ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ህጓ ወይዘሮ መህቡባ አደም፤ ፕሮጀክቱ 14 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚደረግበት፣ 28 ወራት እንደሚፈጅና ሙሉ ወጪው በኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚሸፈን ጠቁመዋል፡፡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ፕሮጀክቱን የማማከር ሥራ እንደሚያከናውንና ክፍያው በአፈጻጸሙ ልክ በየደረጃው እንደሚ ከናወንም ስምምነቱ በተደረገበት ወቅት ተናግረዋል፡፡
የተቀናጀ የፍትህ ሥርዓት መረጃ አያያዝ ባለመኖሩ የመረጃ እጦትና የፍትህ መዘግየት ችግሮች ሲፈጠሩ እንደነበር በማስታወስ፤ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ጥራት ያለው፣ ቀልጣፋ፣ ተገማችና ተደራሽ የፍትህ ሥርዓት ለማስፈን እንደሚረዳም ገልጸዋል፡፡ በፍትህ አካላት ላይ ያለውን ጫና እንደሚቀንስ፣ በተገልጋዮች የሚነሳውን ቅሬታ እንደሚያስወግድና ከዕድገቱ ጋር እኩል ሊራመድ የሚያስችል የፍትህ ሥርዓት ለመዘርጋት እንደሚያስችልም ወይዘሮ መህቡባ ተናግረዋል፡፡
ሥርዓቱ ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉትን ፖሊስ፣ዓቃቤ ህግ፣ፍርድ ቤቶችንና ከፍትህ ተቋማት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ተቋማት በማስተሳሰር አንድ አገራዊ የመረጃ ቋት እንደሚፈጥርም ነው የተናገሩት፡፡ይህም መረጃዎችን፣ሰነዶችንና ምስሎችን ፈጣን ልውውጦችን ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡
የአገር በቀሉ አፍሪኮም ኩባንያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ባህሩ ዘይኑ፤ ኩባንያዎቹ በመካከለኛው ምስራቅ ብዙ የቴክኖሎጂ ሥራዎችን በመስራት ሰፊ ልምድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ከእነርሱ ጋር መስራትም የዕውቀት ሽግግር ለማምጣት፣ የሥርዓቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥና ለመደገፍ እንደሚያስችላቸው ጠቁመዋል፡፡ በተለያዩ የአገር ውስጥ ቋንቋዎች አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ቀላል አጠቃቀም እንደሚዘረጋም ገልጸዋል፡፡
ቴክኖሎጂው ህብረተሰቡ የወንጀል ድርጊቶችን ሲፈጸሙ ከተመለከተ በተንቀሳቃሽ ስልኩ አማካኝነት በመጠቆም የፍትህ ሥርዓቱን የሚያግዝበት አሰራር እንደሚዘረጋ በመጠቆምም፤ ቀልጣፋ፣ ግልጽና ተዓማኒነትን ያተረፈ የአገልግሎት አሰጣጥ እንደሚያሰፍንና በፍትህ ተቋማት መካከል ትስስር በመፍጠር የመረጃ ልውውጥን እንደሚያፋጥንም ገልጸዋል፡፡ አስተማማኝና ደህንነቱ የተጠበቀ የመረጃ ቋት እንደሚቀመጥ አቶ ባህሩ ጠቁመዋል፡፡
ሥራውን የሚያማክረው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ፕሮጀክት ማናጀር ኢንጂነር ረዳ ወልደ ብርሃን ፕሮጀክቱ አገራዊ ፋይዳውም የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የውጭ ኩባንያዎች መሳተፋቸው ለዕውቀት ሽግግር እንደሚረዳ ጠቁመዋል፡፡
አሳሳቢ የሆነውን የተሽከርካሪ አደጋ ለመቀነስ የትራፊክ ባለሙያዎች በተወሰኑ ሥፍራዎች የተሽከርካሪ ፍጥነት ቁጥጥር እያደረጉ እንደሚገኙ ያስታወሱት ኢንጂነር ረዳ፤ ሥርዓቱ ሲዘረጋ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሸፍን ሥራ ለመስራት እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡
በየደረጃው የቁጥጥር ሥራ ይሰራል ያሉት ኢንጂነሩ በጥራት በኩል እንደማያሳስብ ገልጸዋል፡፡ ጨረታው ዓለም አቀፍ ሂደት ማለፉን፣ ለሦስት ወራት መቆየቱንና 30 የሚደርሱ ኩባንያዎች በጨረታው መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢሲክስ (ISYX) ቴክኖሎጂ ምክትል ዳይሬክተሩ ሺቫ ካትሪሰንና የአልረዋድ (ALROWAD) ኩባንያ ዋና ዳይሬክተር ፓትሪክ ኦስታ ፕሮጀክቱ መረጃ ለማግኘት ይወጣ የነበረውን ጊዜና የሰው ጉልበት እንደሚቆጥብ ጠቁመዋል፡፡ ወንጀልን በመከላከልም ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱን አጠናቅቀው ከማስረከባቸው አስቀድሞም የሥራውን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ለአገር በቀሉ አፍሪኮም ኩባንያ ባለሙያዎች ያላቸውን ሰፊ ልምድ በማጋራት በቂ የዕውቀት ሽግግር እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል፡፡

 ዘላለም ግዛው
 


ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829501
TodayToday1131
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7221
This_MonthThis_Month29681
All_DaysAll_Days2829501

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።