ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ማስፋፊያ ያደርጋል Featured

14 Apr 2018
ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ማስፋፊያ ያደርጋል ፎቶ-ፀሐይ ንጉሴ

አዲስ አበባ:- የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ699 ሚሊዮን ብር የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የማስፋፊያ ግንባታ ለማከናወን ከዮቴክ ኮንስትራክሽንና ከኦቦን ቪያጅ አርክቴክቶችና መሐንዲሶች አማካሪ ድርጅት ጋር ትናንት ውል ተፈራርሟል፡፡ 

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት ፕሬዚዳንቱ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሚገነባው ማስፋፊያ 12 ፎቅና ሁለት ምድር ቤት ያለው ሕንፃ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ 699 ሚሊዮን ብር እንደሚወጣበትና በሁለት ዓመት ተኩል እንደሚጠናቀቅ፣ ወጪው ሙሉ በሙሉ በመንግሥት እንደሚሸፈን አመልክተዋል፡፡ ተቋራጩ በግልጽ ጨረታ መመረጡንም ገልጸዋል፡፡
ግንባታው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተገኘ 13 ሄክታር መሬት ላይ እንደሚገነባ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ ሆስፒታሉ በርካታ ተገልጋዮችን የሚያስተናግድ በመሆኑ ከፍተኛ የቦታ እጥረት እንዳለበት አስታውሰዋል፡፡ ለዚህም የማስፋፊያ ግንባታው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ክትትል እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡
የዮቴክ ኮንስትራክሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮሐንስ ተክላይ፤ ተቋራጩ ደረጃ አንድ ፍቃድ ያገኘና በመንገድና በሕንፃ ግንባታ የተሰማራ መሆኑን ተናግረው፤ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በርካታ ግንባታዎችን አጠናቅቆ ማስረከቡንና አሁንም ግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች እንዳሉት ገልጸዋል፡፡
አቶ ዮሐንስ፤ በ900 ቀናት ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት ከውጭ ምንዛሬ ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ሁኔታ ያጋጠመው የግንባታ ዕቃ ግብዓት አቅርቦት ችግር ግንባታውን እንዳያጓትተው ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ከማህበራት ጋር በመነጋገር እየተንቀሳቀስን ነው ብለዋል፡፡ ችግሮቹም ወደፊት እንደሚቀረፉ ያላቸውን ተስፋም ተናግረዋል፡፡
ኦቦን ቪያጅ አርክቴክቶችና መሐንዲሶች አማካሪ ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኢንጂነር አለሙ መረራ በበኩላቸው፤ የሚገነባው የተማሪዎች ማደሪያ ሕንፃ አራት ሺ ካሬ ሜትር ላይ ያርፋል፡፡ በድምሩ ሁለት ሺ አራት መቶ ተማሪዎችን የመያዝ አቅም ይኖረዋል፡፡ ጊቢው በማስፋፊያዎች በመጣበቡ በተገኘው የማስፋፊያ ቦታ ላይ ከሚገነቡት ሕንፃዎች አንዱ ሲሆን፤ የአስተዳደራዊ ሕንፃዎች፣ የተማሪዎች ማማከሪያና የጥናት ማዕከል በቀጣይ ይገነባል፡፡
67 ተቋራጮች በውድድሩ ተሳትፈው ዮቴክ ኮንስትራክሽን መመረጡ ታውቋል። ኢንጂነር አለሙ «ግንባታው የሰው ሕይወት የሚታደግበት ስፍራ በመሆኑ በልዩ ኃላፊነት ጥራቱ ተጠብቆ እንዲገነባ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እንደርጋለን» ብለዋል፡፡
የጥቁር አንበሳ ሆስፒታልና የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ዳዊት ወንድማገኝ፤ የሆስፒታሉ ማስፋፊያ ሰፊ የህክምናና የትምህርት ተቋም መገንባት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ «ወደፊት አስር የሚደርሱ ሆስፒታሎች ይገነቡበታል ብለን እናስባለን፣ ከሆስፒታሎቹ ጎን ለጎንም የአገልግሎት መስጫና መማሪያ ክፍሎች ይኖሩታል፡፡ ከፕሮጀክቱ መካከል አሁን የሚገነባው የተማሪዎች ማደሪያ ነው» ብለዋል፡፡ የተማሪዎችን ማደሪያ መሰራቱ ሆስፒታሉ በብዙ ግንባታዎች በመጣበቡ ጊቢ ውስጥ ያሉትን የተማሪ ማደሪያዎች በማዘዋወር ክፍሎቹን ወደ ህክምና አገልግሎት ለመለወጥ እንደሚያግዝም ገልጸዋል፡፡
የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ላለፉት 60 ዓመታት በህክምና ዘርፍ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ተቋም መሆኑ ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓመት 500 ሺ ሰዎችን የሚያስተናግደው ይህ ተቋም፤ ከተገልጋዮቹ መካከል 50 ሺ የድንገተኛ አገልግሎት ተጠቃሚዎች፣ 50 ሺ ደግሞ አልጋ ይዘው የሚታከሙ ናቸው፡፡ 70 በመቶ የህክምና አገልግሎት የሚሰጠው ለዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍሎች ነው፡፡

ዘላለም ግዛው

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829502
TodayToday1132
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7222
This_MonthThis_Month29682
All_DaysAll_Days2829502

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።