የምግብ ደህንነት ፖሊሲ አለመኖር ምን አስከተለ? Featured

13 Apr 2018

ለምግብነት የሚውሉ የእንስሳት ተዋጽኦ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ሌሎች ሰብሎች አመራረት፣ ቅንብር፣ ስርጭትና ለተጠቃሚ የሚደርስበትን ሂደት ጤናማና ደህንነቱ የተጠበቀ ማድረግ ተገቢ ቢሆንም በሀገር ደረጃ ይህን ሊያስገድድና ሊያረጋግጥ የሚችል የምግብ ፖሊሲ፣ የአፈጻጸም መመሪያና ደንብ አለመኖር ችግሮችን እያስከተለ መሆኑን የዘርፉ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ 

የምግብ ፖሊሲ አለመኖር ሀገሪቱ ማግኘት ያለባትን የውጭ ምንዛሬ ከማስቀረቱ ባሻገር አምራቾች ከምርቶቻቸው አኳያ ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም እንዳያገኙ አድርጓል የሚሉም አሉ፡፡ በሀገር ደረጃ የምግብ ደህንነት ፖሊሲ አለመኖር ምን ችግሮችን አስከትሏል?
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር፣ የሦስተኛ ዲግሪ ዕጩና የስነ-ምግብ ተመራማሪ አድማሱ ፈንታ እንደሚሉት፤ የምግብ ፖሊሲ በሀገር ደረጃ አለመኖር ለምግብነት መዋል የሚገባቸውና የማይገባቸው ምግቦች እንዳይለዩ ከማድረጉ ባሻገር ምርቶች ካላቸው ንጥረ ምግብና ከሚሰጡት ጥቅም አኳያ ዋጋ እንዳያወጡ አድርጓል፡፡ ይህም በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ሸማቹ ምርቱን በዓይኑ በማየት ብቻ እንዲገዛ እያደረገ ሲሆን፤ አምራቾች ለሚያቀርቡት ምግብ ፍትሐዊ ዋጋ እንዳያወጡ ከማድረጉ ባሻገር ተጠቃሚዎች ካለምንም መስፈርት እንዲሸምቱ ያስገድዳል፡፡
በሀገር ደረጃ የትኛውም ዓይነትና በየትኛውም የጥራት ደረጃ ላይ ያለ ምርት ከነጉድለቱ ገበያ ላይ እየቀረበ መሆኑ በተጠቃሚ ጤና ላይ ከሚያደርሰው ችግር ባሻገር ሀገሪቱ እየሠራችበት ያለውን የምግብ ዋስትና የሚጎዳ ነው፡፡ የምግብ ዋስትና ፕሮግራሙ ጥራትና ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ ማቅረብ እንደሚገባ ያስቀምጣል የሚሉት መምህር አድማሱ፤ ከኢኮኖሚያዊ ጥቅም አንጻር በወጪ ንግዱ ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ የበረታ ነው፡፡ ለአብነት በበርበሬ ላይ አልፎ አልፎ የሚከሰት ‹‹አፍላቶክሲን›› ምርቱ በዓለም ገበያ ተቀባይነት ሲያሳጣና አምራቾችን ለኪሳራ ሲዳርግ ይስተዋላል፡፡ ይህም የምግብ ደህንነት ፖሊሲ አለመኖር ዋናው ችግር አርሶ አደሩ የምግብን ደህንነት በሚያበላሹና በሚጎዱ ነገሮች ላይ በቂ ግንዛቤ እንዳያገኝ ያደርጋል ይላሉ፡፡
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምግብ ሳይንስ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር፣ መምህርና የስነ-ምግብ ተመራማሪ ዶክተር ይሁኔ አየለ፤ በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ የህዝብ ብዛት እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በምግብ ላይ ቅየጣዎች ወይም ባዕድ ነገሮች እንዲቀላቀሉ እየተደረገ ነው፡፡ እንዲሁም ለጤና ጎጂ የሆኑ መጠጦች ካለ ማንም ከልካይ ሁሉም እንዲጠቀማቸው እየተዋወቁ ነው፡፡ በተለይ በሽልማት መልክ የሚተላለፉ ማስታወቂያዎች በርካቶች ‹‹ዕድሌን ልሞክር›› በማለት ስለሚጠቀሟቸው ያለባቸውን በሽታ የሚያባባስ ኬሚካል እየወሰዱ ነው፡፡ ይህ የፖሊሲ ማዕቀፍ አለመኖር ችግር ነው ይላሉ፡፡
በተጨማሪም ከውጭ የሚገቡም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምግቦች ላይ እንደ መድሃኒት በማስተዋወቅ ለመሸጥ የሚደረግ ዘመቻ አለ፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ምግብ በመድሃኒት ስም ሲቸበቸብ ይታያል፡፡ ሰው ወደ ትክክለኛ ጤና ጣቢያ በመሄድ ጤንነቱን መከታተልና የባለሙያ ምክር መከተል ሲገባው ለመሸጥ ሲባል መድሃኒት ናቸው፤ ለተለያዩ በሽታዎች ፈውስ ይሆናሉ፤ በማለት የተሳሳተ መንገድ እንዲከተል ሲደረግ ይስተዋላል የሚሉት ዶክተር ይሁኔ፤ ለአብነት ከዚህ ቀደም የውጭ ድርጅቶች ምግብን በመድሃኒት ስም ሲሸጡ ነበር፡፡ በሀገሪቱ ሞሪንጋ፣ ጥቁር አዝሙድ ወዘተ... ለሦስት መቶ በሽታዎች መድሃኒት ነው እየተባሉ ሽያጭ ላይ የሚውሉትም ትክክል እንዳልሆኑ ይገልጻሉ፡፡
እንደ ዶክተር ይሁኔ ገለጻ፤ ምግብ ያድናል ተብሎ የማስተዋወቅ ዘመቻ ሊደረግበት አይገባም፡፡ ምግብ ሰዎች በበሽታ እንዳይጠቁና ጤንነታቸውን እንዲጠብቁ እንደሚያደርግ ግልጽ ሆኖ ሳለ ለዚህ በሽታ ፈውስ ይሆናል እየተባለ ሊሸጥ አይገባም፡፡ እነዚህንና የመሳሰሉትን ችግሮች እልባት ሊሰጥ የሚችል ፖሊሲ ማውጣት ካልተቻለ ችግሩ እየተወሳሰበና በተለያየ መልኩ ደህንነታቸው ያልተጠበቁ ምግቦች የሚቀርቡበት አማራጭ አየሰፋ ይሄዳል፡፡
በኢትዮጵያ ሆላንድ ንግድ ትብብር ለግብርና እድገት ፕሮግራም የቅመማ ቅመም፣ ሃመልማላማና ማዕዛማ ዘይቶች ተመራማሪና አማካሪ አቶ አዲሱ አለማየሁ ሲያብራሩ፤ የምግብ ፖሊሲ አለመኖር ከምግብ አመራረት ጀምሮ ለተጠቃሚ እስከሚቀርብ ድረስ ባለው ሂደት ችግሮችን እያስከተለ ነው፡፡ በቅመማ ቅመም ዘርፍ በርበሬ በጥንቃቄ ጉድለት ምክንያት ለአፍላቶክሲን ሲጋለጥ ይስተዋላል፡፡ አርሶ አደሩን እንዲሁም ነጋዴውን የሚገድበው የምግብ ደህንነት ፖሊሲ፣ ህግና መመሪያ ባለመኖሩ የሚሸጠው ምርት ሚዛን እንዲያነሳ ውሃ የሚያርከፈክፍበትና ለፈንገስ እንዲጋለጥ የሚያደርግበት ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ ይህ በሰዎች ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል፡፡ በርበሬም ሆነ ሌሎች በጥንቃቄ ጉድለት በአፍላቶክሲ የተመረዙ ምግቦች ለሕፃናት መቀንጨርና ለጉበት ካንሰር ምክንያቶች ናቸው፡፡ ይህም የማህበረሰቡ ጤና በአግባቡ እንዳይጠበቅ እያደረገ ነው፡፡
የምግብ ፖሊሲ አለመኖር ምርቶች ጥራታቸው እንዲጠበቅ ባለማድረጉ በማህበራዊ ህይወት ቀውስ ከማስከተሉ ባሻገር ወደ ውጭ በሚላኩ ምርቶች ላይ የተለያዩ ሀገራት ገደቦችን እንዲጥሉና ምርቱ ጥራቱ ተፈትሾ የሚያልፍበት ውጣ ውረድ(ቢሮክራሲ) አሰልቺ ሆኗል፡፡ ይህም የሀገር ውስጥ ላኪዎች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው እንዳይሸጡና አጠቃላይ ወደ ውጭ የሚላከው ምርት በተወሰነ መጠን እንዲቀንስ አድርጓል ያሉት ተመራማሪው፤ አርሶ አደሩ የሚያመርተውን ምርት በአግባቡ እንዳይሸጥ እያደረገ ከመሆኑ ባሻገር ተወዳዳሪነት በሀገር ደረጃም እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ አርሶ አደሮች ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለማምረት ከፍተኛ ወጪ አውጥተውና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው ቢያመርቱም፤ ጥራቱን የጠበቀው ካልጠበቀው ጋር በተመሳሳይ ዋጋ የሚሸጥበት ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ ይህም ተጠቃሚነታቸውን ዝቅ አድርጎታል ብለዋል፡፡
‹‹በሀገሪቱ በምግብ ራስን መቻል የሚለው ሃሳብ ቅድሚያ የሚሰጠው ቢሆንም የምግብ ጤናማነት ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ምግብ የሚወሰደው ጤንነትን ለመጠበቅ እንጂ ርሃብን ለማስታገስ ብቻ አይደለም፡፡ የተወሰደው ምግብ ጤንነትን የሚጎዳ ከሆነ ምግብ አለመውሰድ ሊያስከትለው ከሚችለው ችግር የተለየ አይደለም፡፡ ይህም የፖሊሰው ክፍተት ያመጣው ችግር ነው፡፡
«በሀገሪቱ የምግብ ፖሊሲ አለመኖር የአውሮፓ ህብረትና ሌሎች ሀገራት ከኢትዮጵያ በሚገቡ የቅመማ ቅመም ምርቶች ላይ አዲስ መመሪያና ደንብ እንዲያወጡ አድርጓል፡፡ ይህም በዘርፉ ያሉ ባለሀብቶች መመሪያውን አሟልተው ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ፍትሕዊ ያልሆነ የንግድ ውድድር ላይ እንዲገቡ፣ በሌሎች ሀገር አምራቾች በቀላሉ እንዲበለጡና ተጎጂ እንዲሆኑም አድርጓል፡፡›› በማለት ተመራማሪው ያብራራሉ፡፡
በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስነ-ምግብ ተመራማሪ ወይዘሮ አረጋሽ ሳሙኤል፤ ምግቦች ቢታሸጉ ከምን እንደተሠሩ፣ የያዙት ንጥረ-ነገር፣ የተመረቱበትና የሚበላሹበት ጊዜ በትክክል ይቀመጣል፡፡ በሀገሪቱ ሁኔታ ይህን የሚያስገድድ ነገር ስለሌለ አገልግሎት ሰጭዎችም ሆኑ በምግብ ንግድ ዘርፍ ያሉ ነጋዴዎች ምንነታቸው ያልታወቁ ምርቶችን ያቀርባሉ፡፡ በርካታ ጊዜ ሰዎች በአንድ አጋጣሚ በተመገቡት ምግብ ከፍተኛ የጤና መታወክ ሲደርስባቸውና ለሞት ሲዳረጉ ይስተዋላል፡፡ ይህ የሚሆነው በምግብ ደህንነት ዙሪያ ወጥ የሆነ ፖሊሲ፣ መመሪያና ደንብ ባለመኖሩ መሆኑን ያብራራሉ፡፡
ዓለም አቀፍ የምግብ ፖሊሲ ደህንነት ደረጃ (ስታንዳርድ)፤ ሁሉም ምግቦች ከአመራረታቸው ጀምሮ በገበያ ላይ እስኪቀርቡ ድረስ የሄዱበት የአመራረት ሂደት፣ የያዙት ንጥረ-ነገር፣ የተመረቱበትና የሚበላሽበት ጊዜ፣ የምርቱ የጥራት ደረጃ በትክክል እንዲቀመጡ ያዝዛል፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ ራሱን የቻለ ፖሊሲ፣ ህግና መመሪያ ያልተወጣለት በመሆኑ ምግብ በዘፈቀደ ለተጠቃሚዎች የሚቀርብበት ሁኔታ ተስፋፍቶ እንደሚገኝ ባለሙያዋ ያስረዳሉ፡፡
እንደ አቶ አዲሱ ገለጻ፤ ቅመማ ቅመምም ሆኑ ሌሎች ምግቦች የሰው ልጅ የሚመገቧቸው በመሆናቸው ጤናማነታቸውና ደህንነታቸው ሊረጋገጥ፤ ምንም ዓይነት አሉታዊ ተጽዕኖ አለማድረሳቸውም መታመን ይኖርበታል፡፡ ምግቦች በአጭር ጊዜም ሆነ በረጂም ጊዜ የጤና እንከን ማስከተልም አይገባቸውም፡፡ ለአብነት በቅመማ ቅመም ዘርፍ የምግብ ደህንነት ፖሊሲ የሚያስፈልገው ዋናው ምክንያት ከሚመረተው ምርት ውስጥ 85 በመቶ ቅመማ ቅመም ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል በመሆኑ ደህንነቱ ሊረጋገጥ ስለሚገባ ነው፡፡ እንዲሁም 15 በመቶው ወደ ውጭ ሀገር የሚላክ ቢሆንም ሀገራት ለዜጎቻቸው ጤንነት ሲሉ ወደ ሀገራቸው ስለሚገቡ ምርቶች ጥራትን የተመለከተ የራሳቸው መስፈርት ህግና ደንቦች ያላቸው በመሆኑ ችግሩ መፍትሔ ካልተሰጠው በወጪ ንግዱ ተወዳዳሪነት ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ እየበረታ ይሄዳል፡፡
እንደ ዶክተር ይሁኔ ገለጻ፤ ለሀገር ውስጥ ገበያ መቅረብ ያለባቸው የምርቶች የጥራት ሁኔታ አለመታወቅና ለወጪ ንግዱ ብቻ ትኩረት መሰጠቱ የጥራት ጉድለት ያለባቸው ምርቶች ሀገር ውስጥ ገበያ ላይ እንዲቀርቡ እያደረገ ነው፡፡ በመሆኑም ሀገር ውስጥ የምግብ ደህንነትን የሚያረጋግጥ ፖሊሲ ማውጣትና መተግበር ካልቻለ በወጪ ንግዱ ላይ ከሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዕኖ ባሻገር ለዜጎች ተስማሚና ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ ለማቅረብ ተግዳሮቱ የበረታ ይሆናል፡፡

ዜና ትንታኔ
ዑመር እንድሪስ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829506
TodayToday1136
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7226
This_MonthThis_Month29686
All_DaysAll_Days2829506

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።