የፌዴራል ሥርዓቱ እንዴት ይጠናከር? Featured

02 Dec 2017

ዜና ትንታኔ

ኢትዮጵያ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ የተመራችበት የፌዴራል ሥርዓት ሀገሪቱን ዴሞክራሲያዊ ገጽታ እንድትላበስና በልማት ጎዳና እንድትጓዝ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።ይሄ አበረታች ለውጥ እንዳለ ሆኖ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም የራሱ ተግዳሮቶች እንዳሉት አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። ሥርዓቱ ብዝሀነትና አንድነትን አጣምሮ እንዴት ይጠናከር?

ፌዴራሊዝም ብዝሀነትና አንድነትን በእኩል አጣምሮ የማስኬድ ጥበብ ይፈልጋል። አንድነቱ ካመዘነ ሥርዓቱ ከፌዴራሊዝም ወደ አሃዳዊ መሄዱ አይቀርም ፤በተመሳሳይ ብዝሀነቱ ከጨመረም ወደ መበታተን ያመራል ሲሉ ሃሳባቸውን ያስቀመጡት በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር የማነ ካሳ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ይህንን በመቆጣጠሩ ረገድ ክፍተት እንዳለ ያስቀምጣሉ፡፡ይህንንም ሲያብራሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ህገ መንግሥቱን የማስጠበቅና የመተርጎም ስልጣን ተሰጥቶታል። የብሄር ብሄረሰቦችም ተወካይ ነው። ነገር ግን ሥራውን የሚያከናውነው እንደ ትርፍ ሰዓት ሥራ ነው።

በተግባርም ወንበሮቹ ሲታዩ የተያዙት በክልል ፕሬዚዳንቶች፤ በክልል አፈ ጉባዔዎች፤ ምክትል አፈ ጉባዔዎች፣ የክልል ምክትል ኃላፊዎችና ሚኒስትሮች ነው።በአዋጁ መሰረት የሚገናኙትም በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ ነው።በዓመት ሁለቴ ሲገናኙ ተሰብስቦ የቆያቸውን ነገር ይሰራሉ እንጂ እንደ ትልቅ ሥራ ታስቦ ህገ መንግሥትንና ህገ መንግሥታዊነትን የማስከበር ትልቅ ኃላፊነትን በአግባቡ ሊተገብሩ አይችሉም ሲሉ ይሞግታሉ። የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም አሁን ያለበት ተግዳሮት ሚዛኑን የሚያስጠብቅ ተቋም የማቋቋምና ያለማቋቋም ጉዳይ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ያክላሉ።

ረዳት ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት በአንድ በኩል ክልሎች ፌዴራል መንግሥት በኛ ስልጣን ገባ ብለው አቤት የሚሉበት ተቋም ይኖራል።ይህም ህገ መንግሥቱን ተርጉሞ መልስ ይሰጣቸዋል። በሌላ በኩል ብሄርን መሰረት ያደረገ ክልል ሲቀመጥ በክልሎቹ ውስጥ ሌሎች አነስተኛ ብሄሮች መኖራቸው አይቀርም።እዚያም ያለውን መብት ማስጠበቅ ያስችላል። አሁን መንግሥት ችግር ሲፈጠር ወንጀለኞችን ለፍርድ የማቅረብ ግጭቶችን የማረጋጋት ሥራ እየሰራ ነው። ነገር ግን አስቀድሞ መከላከል የሚቻልበትም ዕድል እንዳለ ይናገራሉ።

በየክልሉ አነስተኛ ብሄር ሆነው የተቀመጡ ጭቆና እየደረሰባቸው አለመሆኑ፤ በህገ መንግሥቱ በተቀመጠላቸው መሰረት መብታቸው የተጠበቀላቸው መሆኑን የሚከታተል ተቋም በኢትዮጵያ አለ ለማለት አያስችልም ባይ ናቸው። ስለዚህም ጣልቃ ሳይገባ ችግር ሊፈጠር የሚችልባቸውን ቦታዎች የሚከታተልና ቀድሞ የሚጠቁም ተቋም ማቋቋም ተገቢ ነው። ይሄ ሳይሆን ቀርቶ ፌዴራሉ ተጠናክሮ ክልሎች ከተዳከሙ ወደ አሀዳዊ፤ ፌዴራል ተዳክሞ ክልሎች ከተጠናከሩ ደግሞ ወደ መበታተን በማምራት ለሀገር ህልውናና ለተጀመረውም ልማት ስጋት ይሆናል ይላሉ።

«ፌዴራላዊ ሥርዓቱ የሚመሰረተው ለዘላቂ አንድነትና ዴሞክራሲ ተብሎ ነው አላማውም መሆን ያለበት የአንድነትንና የዴሞክራሲ ጉዳዮችን እያጎለበተ መሄድ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን ከመነሻው ይሄ መስመር አልተያዘም የመገንጠልን ጉዳይ በማበረታታ የተጀመረ ነው» የሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበርና የመድረክ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጥላሁን እንደሻው ናቸው።

እንደ አቶ ጥላሁን ማብራሪያ ፌዴራል መንግሥት ክልሎች በሚካለሉበት ወቅት አንድነትን ሊያጠናክር የሚችል የህዝቦችን ግንኙነት በማያፈርስና የድንበር ግጭቶችንም ሊፈጥር በማይችል በጥንቃቄ መካሄድ አለበት፡፡ የብሄር ብሄረሰቦች የማንነት ጥያቄ አንዱ ሲሆን ፣ በተጓዳኝ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጉዳይም የህዝብ ጥያቄ በመሆኑ በእኩል ሊፈታ በሚችል መልኩ መደራጀት አለበት ሲሉ ይከራከራሉ።

አቶ ጥላሁን እንደሚሉት የክልል ድንበር መስመር ይዞ የሚሄድ ነው፡፡የብሄረሰቦች ቋንቋና ባህል ግን መስመር አይጠብቅም፤ድንበር አይወስነውም።በድንበር አካባቢ ሁለቱንም ቋንቋ የሚናገሩ ሁለቱንም ባህል የሚካፈሉ ማህበረሰቦች አሉ።ስለዚህ ችግር እንዳይከሰት ዝቅተኛ የአከላለል ድንበር መዘጋጀት አለበት፡፡ክልሎችም በውስጣቸው ያሉ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት ማስከበር ይገባል፡፡ ዜጎች ባሉበት ክልል በራሳቸው ቋንቋ የመማር፣ የመስራት፣ የመኖር ፣የመመረጥ እኩል መብት አላቸው።ለዚህ ደግሞ አጠቃላይ የመንግሥት መዋቅር የህግ የበላይነትን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡በአጠቃላይም መከፋፈልን የሚታገልና አንድነትን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን መስራት ይጠበቃል።

በተጨማሪም ሥርዓቱ በቅርጽና በስም ብቻ ሳይሆን በይዘቱም ዴሞክራሲያዊ መሆን አለበት። ህዝብ በትክክል ራሱን የሚያስተዳድርበት በነጻነት መምረጥና መሻር የሚችልበት በማዕከልም ደረጃ የጋራ ጉዳዮቹን በጋራ የሚያከናውንበት ሥርዓት መዘርጋት አለበት፡፡ በዚህም ረገድ የፌዴራል ሥርዓቱ በተግበር እየሰራነው ማለት ያስቸግራል፡፡በዴሞክራሲያዊ ማእከላዊነት የአደረጃጀት መርህ ነው የሚመራው። ይሄ ዴሞክራሲያዊ አይደለም። ምክንያቱም አንድ ማእከል አለ ሌሎች አደረጃጀቶች በሙሉ የዚህ ማእከል ተቀጥያ ናቸው።በዚህ ሥርዓት ትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት እውን ሊሆን አይችልም በማለት የስርዓቱ ተግዳሮት ናቸው ያሉትን ጠቅሰዋል።

ፌዴራሊዝም በህዝቦች ተሳትፎና በዴሞክራሲው ረገድ ጥንቃቄን የሚፈልግ ሥርዓት በመሆኑ ሥርዓቱ አሁን ባለው አካሄድ የሚቀጥል ከሆነ ጠንከር ያለ ችግር በተለይም የመከፋፈልና የመለያየት ዕድል የሚገጥመው ይሆናል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልፃሉ።

«የፌዴራል ሥርዓት ልዩነቶችን ማቻቻል ይጠበቅበታል። በኢትዮጵያም የተዘረጋው ሥርዓት ለዚህ ምቹ ነው። ነገር ግን አተገባበሩ ላይ ትልቅ ክፍተት አለ» የሚሉት ደግሞ አቶ ሞላ ታረቀኝ ናቸው። አቶ ሞላ በፌዴራሊዝም የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የሰሩ ናቸው። በአተገባበሩ ረገድ አለ ያሉትን ክፍተትም ሲያብራሩ በመጀመሪያ አመራሩ ራሱ በበቂ ሁኔታ ያለመገንዘብ ችግር አለ። ስለዚህ ከአመራሩ ጀምሮ በየደረጃው ሀገሪቱ የምትከተለውን ፌዴራላዊ ሥርዓት በጥልቀት ማስረጽ ያስፈልጋል። ከዚህም በላይ ሀገሪቱ የምትተዳደርበት እስከሆነ ድረስ ለሀገር ተረካቢውም ትውልድ በትምህርት ተቋማት በሥርዓተ ትምህርት አካቶ መስጠት ይገባል።ከዚህ ባለፈም ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ሂደት በመሆኑና ከዴሞክራሲ ስለማይለይ በየወቅቱ ዴሞክራሲው እያደገ መሄድ አለበት።በተለይ ከምርጫና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ጋር በተያያዘ ምህዳሩ ሊሰፋና ዴሞክራሲያዊነቱ ሊጎለብት ይገባል። የዴሞክራሲ አስፈጻሚ አካላትም ነፃና ገለልተኛ ሆነው መስራት አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ኢህአዴግ ትልቁን ኃላፊነት ሊወስድ ይገባል ብለዋል።

ፌዴራሊዊ ሥርዓቱ ችግር ስላለበት ኢትዮጵያ ትፈርሳለች እንበታተናለን የሚለው ስጋት ግን አይሰራም ሲሉ የአቶ ጥላሁንን ስጋት ያጣጥላሉ።ይልቁንም ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ያለመረጋጋት ተፈጥሮ በመሀከል ህዝብ ላይ ችግር ሊፈጠር ይችል ይሆናል ሲሉ ያክላሉ።

ፓርቲው ላለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት ሀገሪቱን አስተዳድሯል ። በመሆኑም በዚች የተወሳሰበ ችግር ባለባት ሀገር ከሁሉም የተሻለ ልምድ አለው። ስለዚህ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የበለጠ ተቀራርቦ መስራት ይጠበቅበታል። በቀጣይም የራሱን አመራሮች እያበቃ የማስተካከል ሥራ መስራት እና እነዚህን አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቃል።

አቶ ጥላሁን ስጋቱ ቢኖራቸውም መፍትሄ በማለት የጠቆሙት የፌዴራል ሥርዓቱን ሙሉ ለማድረግ የክልሎች የተጠናከረ ተመጣጣኝ ውክልናና ተሳትፎ ማረጋገጥ ያስፈልጋል በማለት ነው።

ረዳት ፕሮፌሰር የማነ የፌዴራል ሥርዓቱን አቅጣጫ እያየ እየገመገመ ማስተካከያዎችን እያደረገ በቋሚነት የሚሰራ ተቋም ሊቋቋም ይገባል።የሚመሰረተውም ተቋም ስልጣንን የማከፋፈልና አንድ የማድረግም ሥራ የሚሰራ መሆን አለበት። ይሄ ከሆነ ዛሬ የሚታየው የፌዴራል ሥርዓቱ ችግር መፍትሄ ያገኛል ይላሉ።

 

ራስወርቅ ሙሉጌታ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0000767155
TodayToday1349
YesterdayYesterday1235
This_WeekThis_Week1643
This_MonthThis_Month24649
All_DaysAll_Days767155

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።