ሕብረ ብሔራዊነትና ሕዝባዊነት ለላቀ ኃላፊነት Featured

26 Nov 2017

ዜና ሐተታ

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ ህብረ ብሔራዊ አደረጃጀታቸውና ሕዝባዊ ባህርያቸው የተሰጣቸውን ህገ መንግሥታዊ ተልዕኮ በብቃት እንዲፈጽሙ አቅም ሆኗቸዋል፡፡ ከአገር አለኝታነት አልፈው የጎረቤት አገሮች የሰላም ዋስትናም መሆን ችለዋል፡፡ ይህ ውጤት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በየትኛውም አካልና ሥፍራ ፍጹም ፍጹምነት አይኖርምና በእነዚህ ክፍሎች ያሉ መልካም ነገሮች እንዲሁም መታረም ያለባቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው? ይሄን ለማድረግስ ምን መከናወን ይኖርበታል? ሕብረብሔራዊነትና ሕዝባዊነትስ እንዴት ይገለጻል? በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ የሚነሱ ሀሳቦች አሉ፡፡

አቶ ሲሳይ መንግስቴ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ የመከላከያ ሠራዊትም ይሁን የፌዴራል ፖሊስ ሕብረ ብሔራዊነት እንዲኖራቸው የሚደረግበት አንዱና ዋነኛው ምክንያት በህገመንግሥቱ አንቀጽ 39 የውክልና መርህ መሰረት ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በፌዴራሉ መንግሥት ውክልና እንዲኖራቸው ስለሚደነግግ ነው፡፡ በተመሳሳይ በአንቀጽ 87/1 መሰረት የመከላከያ ሠራዊት የብሔር ብሔረሰቦችን ተዋጽኦ ያካተተ ሚዛናዊ ውክልና እንደሚኖር ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም ህብረ ብሔራዊነቱ ይሄን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡

እንደ አቶ ሲሳይ ገለጻ፤ ሕዝባዊ ባህሪያቸውም ተመጣጣኝ ውክልናን ከማስተናገድ የሚጀመር ሲሆን፤ የመከላከያና የፖሊስ አባላት ህዝባዊነትን መላበስም መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ሕገመንግሥቱን ከመተግበር የሚመነጭ ነው፡፡ ሁሉም ያገባኛል ብሎ ተልዕኳቸውን እንዲወጡ፤ በእኩልነት መንፈስ አገራቸውንና ህዝቡን ለማገልገል በተነሳሽነት እንዲሰሩ፤ ህዝቡም ሁሉንም ማንነቶች በመከላከያም ሆነ በፖሊስ አባላቱ ውስጥ እንዲያይና ሁሉንም የራሱ አድርጎ እንዲቀበል ሕብረ ብሔራዊነታቸውና ህዝባዊነታቸው የበለጠ ሚና ይኖረዋል፡፡ የዳር እና የማዕከል ፖለቲካንም በማስወገድ የበለጠ አንድነትን ያጠነክራል፤ መተማመንንም ይፈጥራል፡፡

በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት ረዳት ኮሚሽነር የማነ ገሠሠ እንደሚናገሩት፤ የፌዴራል ፖሊስ ወደ ሥራ ከመሰማራቱ በፊት ከምልመላ ጀምሮ ስልጠናውን አጠናቆ እስኪወጣ ድረስ ለድርድር የማይቀርቡ ሦስት ዋና ዋና መሰረታዊ ጉዳዮችን ማሟላት ይኖርበታል፡፡ እነዚህም ሙያዊ ብቃት፣ በሥነምግባር የተገነባ ሰብዕና እና ብዝሃነትን/ህብረ ብሄራዊነት ያከበረ መሆን ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ የባህል፣ የቋንቋና የሃይማኖት ብዝሃነት ያለባት አገር እንደመሆኗ የፌዴራል ፖሊስ ሕግን እስካልተቃረኑ ድረስ በአደረጃጀቱም ሆነ በአመለካከቱ ብዝሃነትን ያከበረ መሆን ስላለበት፤ በአደረጃጀቱም ሆነ በአመለካከቱ ብዝሃነትን ያከበረ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ብዝሃነትን መላበሱ በስምሪት ላይ ሕዝባዊ ባህሪን ተላብሶ እንዲሰራ አስችሎታል፡፡ በየትኛውም የግዳጅ ሥራው ያለምንም አድሎ ህግን መሰረት በማድረግ የራሱን ሕይወት ሰጥቶ ህዝቡን ለማዳን እየሰራ ይገኛል፡፡ ሰንደቅ ዓላማውን ይዞ በተሰማራበት ቦታ ሁሉ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ከማስቆሙ ባለፈ ሕዝቡ የእኔ ብሎ እንዲቀበለውና እንዲተባበረው አስችሎታል፡፡

አቶ ሲሳይ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ የመከላከያ ሠራዊቱንም ሆነ የፖሊስ ኃይሉን ሕዝባዊ የሚያሰኘው ተግባሩ ነው፡፡ በተግባር ለህዝብ ተቆርቋሪነቱን እያሳየ ሌት ተቀን ሲሰራ፣ የህዝብን ችግር ለማስወገድ ሲጥርና ህዝቡን በአግባቡ ሲረዳ ነው፡፡ አሁን የመከላከያ ሠራዊቱም ሆነ የፌዴራል ፖሊስ ወደ ህብረብሔራዊነትና ሕዝባዊነት እየመጣ ነው፡፡ ባለፉት ሃያ ዓመታት የመከላከያ ሠራዊቱን ቁጥር ለማመጣጠን ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እንዲገቡ የማበረታታትና የማካተት፣ ወደ አመራርነትም እንዲመጡ እየተደረገ ነው፡፡ በፖሊስ በኩል በአንጻራዊነት እስከ አመራሩ ድረስ ጎልቶ የሚታይ የህብረብሔራዊነት ስብጥር አለ፡፡ መከላከያ ሠራዊቱም በዓለም አቀፍ መድረኮችም ሆነ በአገር ውስጥ የሚያከናውነውን ተግባር ጨምሮ ሕብረ ብሔራዊነቱንም ሆነ ህዝባዊነቱን ሊያሳዩ የሚችሉ መልካም ገጽታዎች አሉ፡፡ ባጠቃላይ በሁለቱም አካላት የህዝቡን ችግር ለመጋራት፣ ለማስወገድ ከመስራትና ህዝቡን ከመደገፍ አኳያ የተሻለ ነገር አለ፡፡

ረዳት ኮሚሽነር የማነ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በሕብረብሔራዊነቱ ታጅቦ ውጤታማ የሆነው የፌዴራል ፖሊስ ይሄን ጠብቆ እንዲሄድ ከማድረግ አኳያ ክልሎች የተሰጣቸውን ኮታ በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡ በሌላ በኩል የፌዴራል ፖሊስ ገለልተኛ ሆኖ እየሰራ ቢሆንም ትክክለኛ ሥራ እንደማይሰራ አድርገው የሚያወሩ የጥፋት አካላት፤ እንዲሁም በየክልሉ ሕብረብሔራዊ አደረጃጀት የሌላቸው ነገር ግን የፌዴራል ፖሊስን አደረጃጀት ይዘው የተዋቀሩ ኃይሎች በመኖራቸውም እነዚህ መልክ ሊይዙ ይገባል፡፡

መከላከያ ሠራዊቱም ሆነ የፖሊስ ኃይሉ ላይ የሚታየው የመንግሥት ባህሪ እንደመሆኑ ህብረ ብሔራዊነትና ህዝባዊነት አጠናክሮ ለመሄድ በመጀመሪያ መንግሥት ራሱ ለመርህ የሚገዛና ዴሞክራት መሆን እንዳለበት የሚገልጹት አቶ ሲሳይ፤ መንግሥት ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን በአግባቡ በመተግበርና ለህዝብ በመቆም በመስራት፣ የሚታዩ ጉድለቶቹንም በመሙላት በአሰራር ምክንያት በሚፈጠሩ ችግሮች የመከላከያም ሆነ የፖሊስ አባላት በሚወጡት ተልዕኮ ውስጥ የሚፈጠር ችግርን ማስቀረት እንዳለበት ያብራራሉ፡፡ እነዚህን ኃይሎች የእኛ ናቸው የሚል ስሜት እንዲፈጠር ከማድረግ አኳያ በሕዝቡ ዘንድ የግንዛቤ መፍጠርን፤ ፍጹምነት ስለማይኖርም አባላቱም የህዝብ መሆናቸውን በቃልም ሆነ በተግባር ማሳየትን፤ ምሁራንም በጥናት የታገዘ ሥራ ማከናወን እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፤ ሕብረ ብሔራዊ የሆነው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሕዝባዊነቱን ተላብሶ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ መሆኑንና ሕዝቡም ለመከላከያ ሠራዊቱ ትልቅ ፍቅር እንዳለው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ በልማቱም ሆነ በፀጥታ ማስከበር ሂደቱ ከሕዝቡ ጋር የሚሰራ እንደመሆኑ ይሄው ሕዝባዊ ባህሪው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም መግለጻቸው ይታወቃል፡፡ በአንጻሩ፣ በክልሎች ያለውን ልዩ ኃይል በተመለከተም ምን ዓይነት የፖሊስ አደረጃጀትና ሥርዓት መኖር እንዳለበት ስታንዳርድ ተቀምጦ ሊመለስ እንደሚገባው እና ይሄን ጥናት ለማካሄድም ረቂቅ ህጎችን መዘጋጀታቸውን በመጠቆም፤ ይሄን የመወሰን መብቱም ስልጣኑም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

 

ወንድወሰን ሽመልስ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0000767153
TodayToday1347
YesterdayYesterday1235
This_WeekThis_Week1641
This_MonthThis_Month24647
All_DaysAll_Days767153

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።