ካንሰርን ለመከላከል Featured

17 Sep 2017

ወጣት ርብቃ ግርማን ያገኘናት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የካንሰር ህክምና ማዕከል ውስጥ ነው፡፡ ርብቃ የ22 ዓመት ወጣት ስትሆን የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዓመት የምህንድስና ተማሪ ናት፡፡ በሆስፒታሉ የተገኘችው ጡቷ አካባቢ ህመም ስለተሰማት ለመታከም ነበር፡፡ ህመም ሲጀምራት ‹‹በሂደት ይቀንሳል›› በማለት ትኩረት ሳትሰጠው ከስድስት ወር በላይ መቆየቷን ትናገራለች፡፡

ወደ ሆስፒታሉ እስከመጣችበት ጊዜ ድረስ ህመሟ ካንሰር እንደሚሆን እንዳልገመተች የምትናገረው ርብቃ ‹‹እያንዳንዱን ምልክቶች በትክክል ለይቼ ባላውቅም ስለ ካንሰር ግንዛቤው አለኝ ብዬ ነበር የምገምተው፡፡ ህመሜ ካንሰር እንደሆነ ባለሙያዎቹ ሲነግሩኝ አላመንኩም ነበር፡፡ በሽታው የማይድንበት አጋጣሚ ስላለ ደነገጥኩ፡፡ በዚህ ዕድሜዬም ካንሰር ይይዘኛል ብዬ አላስብኩም፡፡ ሙሉ መረጃውንም ያገኘሁት ሆስፒታል ከመጣሁ በኋላ ነው›› በማለት ትናገራለች፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የክሊኒካል ሰርቪስ ዳይሬክተርና የጽንስና ማህጸን ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ይርጉ ገብረሕይወት በማህጸን ካንሰር ላይ ለረጅም ዓመት ሰርተዋል፡፡ እንደ ርብቃ ሁሉ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ስለ ካንሰር ምንነት ትክክለኛ ግንዛቤ እንደሌለው ይናገራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የካንሰር ህሙማን ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በኢትዮጵያ የካንሰር ህመም እየጨመረ የመጣበት ምክንያትም ከአኗኗር ዘይቤ መቀየር በተጨማሪ ስለ ካንሰር በቂ ግንዛቤ አለመኖሩ ዋነኛ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡

እንደ ዶክተር ይርጉ ገለጻ፤ ህብረተሰቡ ስለ ካንሰር ምንነት፣ መንስኤና ምልክቶች በትክክል እንዲያውቅ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ያስፈልጋሉ፡፡ በተለይ ካንሰር አስቀድሞ ከታወቀ ታክሞ የሚድን መሆኑን ህብረተሰቡን በማስገንዘብ ማንኛውንም የተለየ ምልክት ሲያጋጥም በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋማት መሄድ እንደሚገባና በየጊዜው ቅድመ ካንሰር ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ ማስገንዘቡ ላይ ብዙ መስራት ይገባል፡፡

«እስከ 30 በመቶ የሚሆኑትን የካንሰር ዓይነቶች መከላከል ይቻላል›› በማለት መንስኤውን በማወቅና ክትባት ያላቸውንም በመስጠት ካንሰርን አስቀድሞ የመከላከል ሥራን ማስፋፋት እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡ እያንዳንዱን ምልክቶች በጊዜ ባለማስተዋል፣ አስተውሎም ‹‹ይሻለኛል›› ከማለትና በየጊዜው ምርመራ ካለማድረግ ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ የካንሰር ህሙማን በሽታው ሦስትና አራተኛ ደረጃ ከደረሰ በኋላ ስለሚመጡ ህክምናውን ከባድና ውስብስብ እንደሚያደርገው ዶክተር ይርጉ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በተለይ ወጣቶችን የቅድመ ካንሰር ምርመራ በማድረግ ያሉበትን ሁኔታ እንዲያውቁ ማስገንዘብ አንዱ ካንሰርን የመከላከል መንገድ ነው›› ይላሉ፡፡

ካንሰርን የመከላከል ትልቁ ሥራ ግንዛቤውን ማስፋት ላይ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር ይርጉ፤ ‹‹ካንሰርን የመከላከል ሥራው አቅም ይጠይቃል፡፡ በአገሪቱ ያለው የካንሰር ተቋም ጥቁር አንበሳ ብቻ ነው፡፡ በማህጸን ካንሰር ላይ የምንሰራው ባለሙያዎች አራት ብቻ ነን፡፡ የመከላከልና የጥናት እንዲሁም ህክምናውንም ጭምር በዚህ አቅም ለመስራት ከባድ ነው» ይላሉ፡፡ የካንሰር ማዕከላትን ማስፋፋትና የባለሙያዎችን ቁጥር መጨመርም አስቀድሞ ለመከላከል ሥራውም ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ያመለክታሉ፡፡ ካንሰርን አስቀድሞ የመከላከል ሥራው በአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ጥናትና ምርምር መደገፍ እንዳለበት በመጠቆም፤ የመከላከል የጤና ፖሊሲውም ካንሰር ላይ ለውጥ እንዲያመጣ ግንዛቤ መፍጠሩ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባም ይጠቁማሉ፡፡

ካንሰር በምን ያህል ደረጃ እንደተስፋፋና መንስኤውን በትክክል ኢትዮጵያ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚያሳይ ጥናት በየጊዜው በማድረግ ካንሰርን የመከላከል ሥራውን ውጤታማ እንዲሆን ያግዛል ይላሉ፡፡ የካንሰር መከላከልና ህክምናውን አገር አቀፍ ማድረግ እንደሚያ ስፈልግም ነው ያስገነዘቡት፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ቡድን መሪ ዶክተር ብስራት ደሳለኝ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ሚኒስቴሩ ካንሰርን ለመከላከል በሲጋራ፣ በአመጋገብና በአኗኗር ዘይቤ ለውጦች ላይ አተኩሮ እየሰራ ነው፡፡ ህዝብ የተሰበሰበበት ቦታ ሲጋራ እንዳይጨስና የሲጋራ ምርት ላይ ከፍተኛ ታክስ እንዲጣል በማድረግ ምርቱ እንዲቀንስ አቅዶ እየሰራ ቢገኝም ሊሳካ የቻለው በተወሰኑ አካባቢዎች ሲጋራ እንዳይጨስ ማድረጉ ብቻ ነው፡፡ ህብረተሰቡ ጤናማ የሆነ የአመጋገብ ዘይቤ እንዲያዘወትር፣ የአልኮል መጠጥ እንዲቀንስ የማስተማር ሥራዎችና የቅድመ ካንሰር ምርመራን በየጤና ተቋማት እንዲስፋፋ የማመቻቸት ሥራዎችም እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

ስለ ካንሰር ምንነት መንስኤና ምልክቶች ለህብረተሰቡ የሚሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች የቀድሞዋ ቀዳማዊ እመቤትን ጨምሮ የተለያዩ ታዋቂ ሰዎችን በመጠቀም የሚከናወን ሥራ አለ፡፡ በተጨማሪም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጫና ጥናት ለማካሄድ ቡድን ተቋቁሟል፡፡ ይሁንና ይህ በቂ አለመሆኑን ቡድን መሪው ያምናሉ፡፡ «በተለይም የካንሰር ህመም የሀብታም አገሮች ችግር እንደሆነ በመቁጠር ሳይሰራባቸው የቆዩት ጊዜያት አሁን ላይ በታዳጊ አገሮች ላይ በሽታው እየጨመረ እንዲመጣ ምክንያት ነው» ይላሉ፡፡

የካንሰር ግንዛቤ፣ መከላከል፣ ቁጥጥርና ጥናት ሥራ የተቀናጀ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ የካንሰር መከላከል ሥራው የጤና ጥበቃ ብቻ ሳይሆን የሌሎች ተቋማትንም ትብብር የሚጠይቅና እርስ በርስ የተያያዘ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ለአብነት የሚጠቅሱትም ሲጋራ የሚጨስበትን ቦታና መጠን ለመቀነስ ግንዛቤው በተሰራ ቁጥር ከሲጋራ ገቢ የሚያገኙ ሌሎች አካላት ስላሉ ሥራውን ለመስራት ቀላል አላደረገውም፡፡ ስለዚህ በካንሰር መከላከል ሥራ ላይ ገና ብዙ መስራት ይገባል፡፡ 

አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሚያዝያ 4 ቀን 2010 ዓ.ም
በሰላማዊት ንጉሴ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829536
TodayToday1166
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7256
This_MonthThis_Month29716
All_DaysAll_Days2829536

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።