ሕብረቱ ከፋይናንስ ጥገኝነት ነፃ ለመውጣት የተግባር ጅምር አሳየ Featured

04 Jul 2017

የመሪዎቹ ጉባዔ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ በማሳለፍ ዛሬ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፤

 

ዚምባብዌ አንድ ሚሊዮን ዶላር ለገሰች

የአፍሪካ ሕብረት ከያዛቸው የለውጥ ዕቅዶች መካከል አንዱ የሆነውን ሕብረቱን ከሌሎች አካላት የድጋፍ ጥገኝነት ነፃ የማውጣት ዕቅድ ወደ ተግባር የሚያሸጋግሩ ጅምሮችን አሳየ፡፡ ለዚሁ ዓላማ የሚሆን አንድ ሚሊዮን ዶላር ከዚምባብዌ በድጋፍ ተገኝቷል፡፡

የአፍሪካ ሕብረት 29ኛ መደበኛ የመሪዎች ጉባኤውን ትናንት በአዲስ አበባ የሕብረቱ አዳራሽ ማካሄድ በጀመረበት ወቅት፤ የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ‹‹ሕብረቱን ከፋይናንስ ጥገኝነት ለማላቀቅ›› በሚል አንድ ሚሊዮን ዶላር አገራቸው መለግሷን አስታውቀዋል ፡፡ ፕሬዚዳንት ሙጋቤ ከ300 የቀንድ ከብቶች ሽያጭ የተገኘውን ይህን የአንድ ሚሊዮን ዶላር ቼክ ለሕብረቱ ሲያስረክቡ፤ የገንዘብ ድጋፉ የሕብረቱን የውስጥ አቅም ለማጠናከር የታሰበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቀንድ ከብት ድጋፉ የአፍሪካን የከብት ሀብት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ያሉት ፕሬዘዳንት ሙጋቤ፤ ገንዘቡን የማሰባሰብ ሃሳብ የመጣላቸው ከሁለት ዓመት በፊት በደቡብ አፍሪካ በተሰናዳ የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ግብዣ ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የድጋፍ ሃሳቡን ለአገራቸው ሕዝብ በማሳወቅ ሃሳቡ ድጋፍ በማግኘቱም የከብት ስጦታውን ለማሰባሰብ መቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከሌሎች የገንዘብ ድጋፍ ጥገኝነት መላቀቅ ቀላል ጉዞ ሊሆን እንደማይችል ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ሂደቱ ፈታኝ ቢሆንም ለአህጉሩ ቀጣይ ትውልድ ሲባል እውን መሆን እንደሚገባው ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹የዛሬው ስጦታም ለቀጣይ እርምጃ ዓርአያ ነው›› በማለትም ሌሎችም በዚሁ መንገድ ዕቅዱን ማሳካት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

የገንዘብ ልገሳውን የተቀበሉት የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሐመት፤ የፕሬዚዳንቱ ተግባር ለሌሎችም ዓርአያ የሚሆን መሆኑን በመጥቀስ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ አህጉር በርካታ ፈተናዎችን መጋፈጧን ጠቅሰው፣ ተስፋ ሰጪ የልማት ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የዓለም ነዳጅ ዋጋ መዋዠቅን ተከትሎ የሀብት እጥረት ማጋጠሙ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ የመጣው የሽብርተኝነት አደጋ፣ በየአካባቢው የሚስተዋሉ የእርስ በእርስ ግጭቶች እየተበራከቱ መምጣታቸው እንዲሁም ሌሎች መሰል ስጋቶች አህጉሪቱን መረጋጋት ያሳጡ ፈተናዎች መሆናቸውን ሊቀመንበሩ ጠቅሰዋል፡፡ክስተቶቹ ሕብረቱ በቀጣይ ለማሳካት የነደፈውን የአጀንዳ 2063 ዕቅድ የሚፈታተኑ ሁኔታዎችም መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

‹‹በአህጉሩ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች እየተስፋፉ መጥተዋል›› ያሉት የኮሚሽኑ ሊቀመንበር፤ በገጠራማ አካባቢዎች የአፍሪካውያን የሞባይል ስልክ ተጠቃሚ ቁጥር ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ እያደገ መምጣቱ፣ የወጣቶች የፈጠራ አቅምና መንፈስ መጎልበቱ የአህጉሪቱን መፃይ የእድገት ተስፋ ብሩህ ገፅታ የሚያላብሱ ሂደቶች መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

‹‹በአፍሪካ የተለያዩ ቀጣናዎች የሚስተዋለው የፀጥታ ችግር አሁንም ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል›› ያሉት የኮሚሽኑ ሊቀመንበር፤ በደቡብ ሱዳን የሚስተዋለው የእርስ በእርስ ግጭት፣ በሶማሊያ፣ ሊቢያ፣ ማሊ፣ ቡሩንዲ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ጊኒቢሳው እንዲሁም በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ከሚታዩ የፖለቲካ ትኩሳቶች ባሻገር፤ በቅርቡ በጂቡቲና ኤርትራ መካከል የተፈጠረው አዲስ ውጥረት ሕብረቱን የሚያሳስቡ የደህንነት ስጋቶች መሆናቸውን አስገንዝበዋል ፡፡

እንደ ሊቀመንበሩ ገለጻ፤ እነዚህን ችግሮች በጋራ ለመፍታት ባለፉት ወራት የተለያዩ የዲፕሎማሲ ተግባራት ከመከናወናቸው ባሻገር በአህጉሪቱ የተደቀኑ ችግሮችን ለመፍታት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በጥምረት የሚሠራ ይሆናል ፡፡

የአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ሊቀመንበርና የጊኒ ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ በበኩላቸው እንዳሉት፤ አፍሪካን ከጥይት ድምፅ ነፃ የሆነች አህጉር ለማድረግ ግብ ተይዞ ቢሠራም አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለው የፀጥታ ችግርና የእርስ በእርስ ግጭት በርካታ ዜጎችን ለስደት እየዳረገ ይገኛል፡፡ ለወጣቶች የሚፈጠረው የሥራ ዕድል እንዲያድግና ፀጥታውም አስተማማኝ እንዲሆን አገሮች በጋራ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሐመድ በበኩላቸው በአፍሪካ ከ226 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 24 ዓመት የሚገኙ ወጣቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ የአህጉሪቱ ቀጣይ ተስፋም ሆነ ፈተና በእነዚህ ወጣቶች ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቅሰው፣ ወጣቶችን ያማከለ ሥራ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በአህጉሩ ዘላቂ ልማትን እውን ለማድረግም የእርስ በእርስ ቀጠናዊ ትስስርን በማጠናከር በኢንዱስትሪ፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በግል ዘርፍ ልማት እንዲሁም በግብርና ምርታማነት ላይ ተባብሮ መሥራት ለወጣቶች ቀጣይ ዘመን መቃናት ወሳኝ እርምጃ ይሆናል፡፡ በአህጉሩ ዘላቂ ሰላምን እውን የማድረግ ሥራም በሕብረቱ ከሚከናወን የዲፕሎማሲ ሥራ ጎን ለጎን ወጣቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አዋጭ መሆኑንም ምክትል ዋና ፀሐፊዋ ገልጸዋል፡፡

በፀጥታ ችግር ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የሚፈናቀሉ አፍሪካውያን ስደተኞችን በመቀበል በኩል ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅኦ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች ከፍተኛ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

29ኛው የሕብረቱ ጉባኤ መክፈቻ ላይ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች የታደሙ ሲሆን፣ የፍልስጤሙ ፕሬዚዳንት ሙሐሙድ አባስ ንግግር አድርገዋል፡፡ ከቀናት በፊት የተጀመረው የሕብረቱ ጉባኤ ዛሬ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡

 

ብሩክ በርሄ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829537
TodayToday1167
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7257
This_MonthThis_Month29717
All_DaysAll_Days2829537

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።