የኢትዮጵያ የንግድ እጆች ወደ አፍሪካ ገበያም ተዘርግተዋል Featured

21 Jun 2017

ዜና ትንታኔ

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የፖለቲካና የጸጥታ መስክ ያላትን አስተዋጽኦና ስኬት ያህል በኢኮኖሚው መስክ እንዳልገፋችበት መረጃዎች ያሳያሉ። እያደገ ከመጣው ኢኮኖሚ አንጻር ወደፊት የሚፈጠረውን የገበያ ፍላጎት ለማሟላትም በአፍሪካ ላይ አተኩሮ መስራት እንደሚገባ ምሁራን አሳስበዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ እ..አ በ2016 ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው የአፍሪካ አገራት ለውጭ ገበያ ካቀረቡት ሸቀጥ መካከል ቤኒን 29 በመቶ፣ ቦትስዋና 29 ነጥብ 5 በመቶ፣ ኮትዲቯር 28 በመቶ፣ ሴኔጋል 46 በመቶ ለአፍሪካ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሽ አገራት ናቸው። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያን ጨምሮ የተቀሩት የአፍሪካ አገራት ያላቸው የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ በጣም ዝቅተኛና እዚህ ግባ የማይባል ነው።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የአፍሪካ ዓመታዊ የአገር ውስጥ ምርት 5 ነጥብ 809 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱን፤ አህጉሪቷ በአማካይ በየዓመቱ የአምስት በመቶ ዕድገት እያስመዘገበች መሆኑን፤ እ..አ በ2050 ላይም 29 ትሪሊዮን ዶላር የሚደርስ ኢኮኖሚ እንደሚኖራት ገልጿል። የወጪ ንግዷም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በ200 በመቶ አድጓል። ይህንን ዓይነት ዕድገትና ገበያ ባለባት አህጉር ውስጥ ኢትዮጵያ ያላት ተጠቃሚነት አነስተኛ መሆኑን አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው ምሁራን ይገልጻሉ።

በተጠቀሰው መረጃና እውነታ ከሚስማሙት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች መካከል በጅማ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህሩ ዶክተር ወንዳፈራሁ ሙሉጌታ አንዱ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉትም፤ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ጋር ያላት የንግድ ትስስር ዝቅተኛ የሚባል ነው። ለትስስሩ ዝቅተኛ መሆንም አገሪቱ ከአፍሪካ አገራት ጋር ተመሳሳይ ምርት ማምረቷ፤ ከአፍሪካ አገራት ጋር በመሰረተ ልማት በሚፈለገው ደረጃ አለመተሳሰሯ የሚሉት ናቸው።

እንደ ዶክተር ወንዳፈራሁ ገለጻም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፋብሪካዎች እየተስፋፉ ናቸው። የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰቱ እየጨመረ መጥቷል። እ..አ በ2025 በአፍሪካ በመካከለኛና ዝቅተኛ ማኑፋክቸሪንግ በአፍሪካ ቀዳሚ ለመሆን ግብ ጥላ እየሰራች ነው። በዚህ ምክንያት በቀጣይ ሦስትና አራት ዓመታት የአፍሪካ ገበያ ለኢትዮጵያ አስፈላጊ ነው።

የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤቶች ዋና ኃላፊና የኢኮኖሚ ምሁሩ አቶ ክቡር ገና በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ የንግድ ተሳትፎዋ ዝቅተኛና መቀየር ያለበት እንደሆነም ያመላክታሉ። በአፍሪካ አገራት መካከል ጠንካራ የንግድ ልውውጥ አለመኖሩ፣ ህብረተሰቡ ከአንዱ አገር ወደ ሌላው አገር በነጻነት አለመንቀሳቀሱ፣ የመሰረተ ልማት አለመስፋፋትና ሌሎችም አገራቱ የተሻለ የገበያ አማራጭ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል፤ ኢትዮጵያም በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ የአፍሪካ ገበያ ላይ ያላት ድርሻ አነስተኛ ሆኗል።

እርሳቸው እንዳሉትም፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ገበያ ለመግባት ያላት ዝቅተኛ የሆነ እንቅስቃሴ አሁን አገሪቱ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ የማይመጥን በመሆኑ መቀየር አለባት። በተመሳሳይ ዕድገት ላይ ያሉና ተመሳሳይ ምርት ስለማያቀርቡ የሚለው አስተሳሰብ እውነትነት ያለው ቢሆንም ድርጅቶች ሁልጊዜም የመስፋፋት ፍላጎት አላቸው። ንግድ የሚስፋፋው ውድድር ሲኖር በመሆኑና በአፍሪካ ያሉትን ድርጅቶች ለመወዳደር ተመጣጣኝ አቅም ስላለ በአፍሪካ ገበያ ላይ ትኩረት ማድረግ አማራጭ የለውም።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ህግ መምህሩ ዶክተር አንዳርጋቸው ሮባ እና በመለስ ዜናዊ የአመራር አካዳሚ የፖለቲካ፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነትና የሰላምና ጸጥታ ምሁሩ ዶክተር ጌታቸው ዘሩ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላትን ተሰሚነትና ተመራጭነት በንግድ ልውውጡ ላይ መድገም አልቻለችም የሚል ተመሳሳይ አመለካከት አላቸው። በዓለም ትላልቅ ገበያ ካላቸው አገራት ጋር መነገዱ መጥፎ ባይሆንም ለአካባቢ ገበያ ትኩረት መስጠቱ ቸል ተብሏል። አገሪቷ የአፍሪካ መዲናነቷንና የጥቁር ህዝብ ሞዴልነቷን ተጠቅማ ንግዷን በማሳለጥ ደረጃ በጣም ደካማ ናት። ትንሽ ቢሆን እየተንቀሳቀሰች ያለችው በምስራቅ አፍሪካ ነው። ያም ሆኖ ያለውን ዕድል አሟጥጣ አልተጠቀመችበትም።

በንግድ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ወንድሙ ፍላቴ በምሁራኑ ሃሳብ አይስማሙም። እርሳቸው እንዳሉትም ከአፍሪካ አገራት ጋር ያለው የንግድ ልውውጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል። በአሁኑ ወቅትም አገሪቷ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች ውስጥ የ21 በመቶ ድርሻ ያለው ወደ አፍሪካ አገራት የሚላከው ነው።

እንደ አቶ ወንድሙ ገለጻም፤ በተያዘው የበጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ያለው የወጪ ንግድ መረጃ የሚያሳየው ወደ ሶማሊያና ጅቡቲ ገበያዎች የተላከው ምርት መጠን 24 ነጥብ 9 በመቶ ድርሻ አለው። የተቀረው ምርት ወደ አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ እስያና መካከለኛው ምስራቅ አገራት የተላከ ነው። ወደ አፍሪካ አገራት ገበያ ለመግባት ያለውን ዕድል ለማስፋት መንግሥት የተለያዩ ድርድሮችንና ስምምነቶች እያደረገ ይገኛል። በዚህም አካባቢያዊ ውህደትን ለመፍጠር የአገሪቱን የፖሊሲ ምህዳር ሊያስጠብቅ የሚያስችል ድርድሮችን ማካሄድ ተችሏል፡፡

ምሁራኑ እንዳሉትም፤ እ..አ በ2025 ኢትዮጵያን በአፍሪካ በመካከለኛ አነስተኛ ማኑፋክቸሪንግ ቀዳሚ ለማድረግ የተቀመጠው ግብ፤ ጥሬ እቃ ከማምረት ጀምሮ በኢንዱስትሪዎች ሙሉ በሙሉና በከፊል በፋብሪካ የሚመረቱ ምርቶችን ወደ ማምረት እንሸጋገራለን የሚል ነው። ግብርናውም ወደ ገበያ መር ምርት ይሸጋገራል። እቅዱ ወደ ዘመናዊ ኢንዱስትሪ የሚያሸጋግርና ትልቅ ገበያ የሚፈልግ ነው። በመሆኑም በጎረቤት የአፍሪካ ገበያ ላይ ከአሁኑ መሰረት መጣል ይገባል። ይህ ካልሆነ አምራች ኢንዱስትሪው በገበያ እጦት መፈተኑ አይቀርም፤ ኢኮኖሚው ከግብርና ለመላቀቅ የሚያደርገው ጥረት ይስተጓጎላል።

 

አጎናፍር ገዛኸኝ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829496
TodayToday1126
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7216
This_MonthThis_Month29676
All_DaysAll_Days2829496

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።