ዕድገትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠች ያለች አገር- ኢትዮጵያ Featured

29 May 2017

26ኛው ዓመት የግንቦት 20 የድል በዓል በሚሌኒየም አዳራሽ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፤

 

ዜና ሐተታ

‹‹ግንቦት 20 ኢትዮጵያ በኢኮኖሚም ሆነ በዲፕሎማሲ እንዲሁም በሰላም ላይ ትልልቅ ለውጦች እንዲገኙ መሰረት የጣለ ትልቅ የድል ቀን ነው›› የሚሉት 26ኛውን የግንቦት 20 የድል በዓል ትናንት በሚሌኒየም አዳራሽ ሲያከብሩ ያገኘናቸው አቶ ባይሳ የባሳ ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ፤ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሲኖሩ በአካባቢው የነበረውን ድህነት እንደሚያውቁና እየተገኘ ባለው ዕድገት የዜጎችን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ መሆኑን አቶ ባይሳ ይናገራሉ፡፡ ‹‹የመጣው ዕድገትና የዜጎች ተጠቃሚነት በፍፁም የሚካድ አይደለም›› በማለት፤ ይህን ዕድገት ለማስቀጠል መንግሥትና ዜጎች ተባብረው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ነው የገለፁት፡፡

እንደአቶ ባይሳ ገለፃ፤ የብሔር ብሔረሰቦችና የሃይማኖት እኩልነት ተረጋግጧል፡፡ ነገር ግን ፍትሃዊነት የሰፈነበት አሰራር ለማስፈን ጥረት ቢደረግም ሙሉ ለሙሉ ፍትሃዊነት ተረጋግጧል ማለት አይቻልም፡፡ በተለይ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ፈተና ሆኗል፡፡ ይህን ለማስወገድ ህዝቡም መብቱን በገንዘብ ባለመግዛት፤ መንግሥትም ሙሰኞች ላይ እርምጃ በመውሰድ እያጋጠመ ያለውን ችግር መፍታት ይገባል፡፡

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነዋሪው ወጣት አብዱላዚዝ መሃመድም በበኩሉ ድሉ ለህዝቦች ተጠቃሚነት መሰረት የተጣለበት መሆኑን በማስታወስ፤ ወጣቱ ትውልድ ይህን ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ ራሱን ለማሳደግ መሥራትና አገሩንም መርዳት እንዳለበት ይናገራል፡፡ መንግሥት ለወጣቶች ተጠቃሚነት የፈጠረው ምቹ ሁኔታ ቀጣይነቱ መረጋገጥ እንደሚኖርበትና አልፎ አልፎ የሚታዩ የማስፈፀም ክፍተቶችን ለመሙላት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራባቸው እንደሚገባም ነው የገለፀው፡፡

የጨርቆስ ክፍለከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ኑሪት አህመድ በበኩላቸው፤ በብዙዎች መስዋትነት የኢትዮጵያ ዕድገት እንዲረጋገጥ መሰረት የተጣለበት ቀን በመሆኑ ድሉን ማክበራቸው ልዩ ስሜት እንደሚፈጥርባቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ልጆቼና እኔ በእጅጉ ህይወታችን ተቀይሯል፡፡ ይህ የሆነው ድሉ በመገኘቱና ልማት በመምጣቱ ነው፡፡ ልጆቼም ሆኑ እኔ እንደፈለግን እየተናገርንና እየሠራን፤ በፈለግንበት ሰዓት ወጥተን እየገባን ነው›› በማለት፤ በኢኮኖሚም ሆነ የዴሞክራሲ መብት በግለሰብ ደረጃ ሳይቀር የተገኘው ውጤት እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ሆኖም የድሉ ውጤት በስኬት እንዲቀጥል ከታች ያሉ አመራሮችን መከታተልና ለህዝቡ ተገቢውን አገልግሎት የማይሰጡትን ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የበዓሉ አክባሪ ሌላው ወጣት ያሬድ አበራ፤ ኢኮኖሚው እያደገና የወጣቶች ሥራ ፈጠራ እየጎለበተ የብዙዎች ተጠቃሚነት በመረጋገጥ ላይ መሆኑን ይገልፃል፡፡ ዕድገቱ የበለጠ እንዲጠናከርና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት ፖሊሲዎች እስከ ታች በአግባቡ እንዲተገበሩ አተኩሮ መሥራት እንደሚገባ ይናገራል፡፡ አያይዞም ወጣቶች ብዙ ጊዜ በተፈጠረ ዕድል ያለመጠቀም ክፍተት ይታይባቸዋልና ራሳቸውን ለማሳደግ ዕድሉን ለመጠቀም ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ይመክራል፡፡

በዓሉ በሚሌኒየም አዳራሽ «የህዝቦች እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ ፌዴራላዊ ሥርዓት እየገነባች ያለች ሀገር - ኢትዮጵያ» በሚል መሪ ቃል ትናንት በተከበረበት ወቅት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ እንደገለፁት፤ ድሉ የጭቆናና የአፈና ሥርዓትን የገረሰሰ ብቻ ሳይሆን፤ በህዝቦች እኩልነትና መፈቃ ቀድ ላይ የተመሰረተ ፌዴራላዊ ሥርዓት እንዲገነባ መሰረት የጣለ ትልቅ የድል በዓል ነው፡፡

በህገ መንግሥቱ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት በተገባው ቃል መሰረት እየተሠራ ያለው ሥራ ውጤት እያስመዘገበ ነው፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች መብት የተረጋገጠበት፤ መድሎና መገለል የቀረበት፤ የህግ የበላይነት የተረጋገጠበትና የኢትዮጵያ ህዳሴ ፍኖተ ካርታ የተቀየሰበት በመሆኑ ድሉን መላው ኢትዮጵያዊ እንደሚያከብረው ነው የተናገሩት፡፡

ድሉ ዜጎች በአገር ግንባታ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ዕድል በመስጠቱ ፈጣንና ተከታታይነት ያለውን ዕድገት ማስመዝገብ አስችሏል፡፡ በተለይ ባለፉት 15 ዓመታት በህዝቦች ተሳትፎ በተረጋገጠው ዕድገት የዜጎች ህይወት ከመቀየሩም ባሻገር፤ የአገሪቷን ተደማጭነት ከፍ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

እንደጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ በፈታኝ አህጉራዊ ቀጣና ውስጥ ሰላምን ማረጋገጥ ከመቻል አልፎ ለሌሎችም የሰላም አጋር መሆን ተችሏል፡፡ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ተራማጅ አቋም በመያዝ ለውጥ እንዲመጣ ተደርጓል፡፡ ሥልጣን በህዝቦች ይሁንታና በዴሞክራሲ ስርዓት ብቻ የሚገኝበት ደረጃ ላይ በመድረስ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል፡፡ ይህ ሁሉ የግንቦት ሃያ ድል ውጤት ነው፡፡

በእነዚህ ዓመታት የተገኙት ስኬቶች አልጋ በአልጋ በነበረ ጉዞ የተገኙ አይደሉም፡፡ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ልማትና ዴሞክራሲ በፍጥነት ቢያድጉም ኪራይ ሰብሳቢነት ፈተና ሆኗል፡፡ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን ቢቻልም፤ ትምክህትና አክራሪነት የሥርዓቱን ፍትሃዊነት በመደበቅ አንዳንዶች የራሳቸውን አጀንዳ እንዲያስተጋቡ ዕድል አግኝተዋል፡፡ ይህን ክፍተት ለማስተካከል መንግሥትና ህዝቡ ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚረባረብ ነው የተናገሩት፡፡

ያለፉትን 15 ዓመታት ጉዞ በመገምገም በጥልቅ ለመታደስ የተካሄደው ንቅናቄ ከድርጅት አልፎ ወደ ህዝብ ወርዷል፡፡ ይህም ችግሩን የመፍታት ጉዞ ልማትን ከማፋጠን ጋር በማስተሳሰር ውጤቱ በስኬት እንዲቀጥል ያስቻለ መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ያስታወቁት፡፡

 

ምህረት ሞገስ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829519
TodayToday1149
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7239
This_MonthThis_Month29699
All_DaysAll_Days2829519

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።