የቀን ገቢ ግምቱ ፍትሃዊነት ይጎድለዋል Featured

19 May 2017

ዜና ሐተታ

የዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ድርጅት(አይ ኤም ኤፍ) የአዲስ አበባን ዕድገት፣ የንግድ እንቅስቃሴና የኢንቨስትመንት ፍሰት መነሻ በማድረግ በቅርቡ ያካሄደው የዳሰሳ ጥናት እንደሚያመለክተው፤ ከከተማዋ በዓመት ከ40 እስከ 52 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ይቻላል፡፡ ሆኖም በ2008 የገቢ አሰባሰብ መነሻነት መሰብሰብ የተቻለው 52 ነጥብ 7 በመቶ ብቻ መሆኑን የባለስልጣኑ መረጃ ያሳያል፡፡ ይህም የከተማዋ የገቢ አቅምና በተጨባጭ እየተሰበሰበ ያለው ገቢ ያልተመጣጠነ መሆኑን መረዳት የሚቻል ሲሆን፤ በቀን ገቢ ግምት አወሳሰን ላይ ያለው ክፍተት ለችግሩ አንዱ ምክንያት መሆኑን የዘርፉ ሰዎች ይናገራሉ፡፡

ይህን ለማስተካከል የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ የገንዘብ የመግዛት አቅም፣ የዋጋ ግሽበትና ከዚህ ቀደም የሚስተዋሉ ክፍተቶችን መሰረት ያደረገ አዲስ የቀን ገቢ ግምት አሰራር ከሐምሌ 2009 ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ፡፡

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የግብር አወሳሰንና አሰባሰብ ፕሮግራም የልማትና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ፈቃደ ከ2003.ም ጀምሮ ላለፉት ስድስት ዓመታት የቀን ገቢ መረጃና ጥናት በወቅቱ ባለመካሄዱ በህግ ተገዥነት ላይ ተጽዕኖ የፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ለማስተካከልም የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ የገንዘብ የመግዛት አቅም፣ የዋጋ ግሽበት፣ የፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2009 ያስቀመጣቸው ድንጋጌዎችንና የከዚህ ቀደም ክፍተቶችን መሰረት ያደረገ አዲስ የቀን ገቢ ግምት አሰራር ከሐምሌ 2009.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ 74 በመቶ የፋይናንስ ምንጭ ግብርና ታክስ ቢሆንም የታክስ ጉዳይን ከሌሎች የልማት ተግባራት ጋር አቀናጅቶ የህዝቡ አጀንዳ በማድረግ በኩል ክፍተቶች መታየታቸው ከተማ አስተዳደሩ ማግኘት ያለበትን ገቢ እንዳያገኝ ሆኗል የሚሉት አቶ ያሬድ፤ በ2003 በቀን ገቢ ላይ የተደረገው ጥናት የወቅቱን ገበያ እና ትርፍ መሠረት ያላደረገ፣ የግምቱን ውጤት አስቀድሞ ለግብር ከፋዩ ለማሳወቅ የማያስችል፣ የፖለቲካ አመራሩ የተለያየ የቀን ገቢ እንዲገምት ያደረገ፣ ለአዋሳኝ ወረዳዎች ተመሳሳይ የቀን ገቢ ግምት አለማስቀመጥና ሌሎችም ችግሮች በሚሰበሰው ታክስ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥረው ነበር ይላሉ፡፡

ከነጋዴው ማኅበረሰብ ጋር በመደራደር የቀን ገቢ ግምትን ማሳነስ፣ ለድርድር ፈቃደኛ ባልሆኑት ላይ ግምቱን መጨመር፣ ከኮሚቴ ተነጥሎ ሄዶ ከግብር ከፋዩ ጋር መነጋገርና የግል ስልክ ማስቀመጥ፣ የቀን ገቢ ግምት መገመቻ ቅጽ ለድርድር እንዲያመች በእርሳስ መፃፍና ስርዝድልዝ ማብዛት ለችግሩ መንስኤ እንደነበሩ፤ በአሁኑ የግምት አወሳሰን ላይ ቀደም ሲል የነበሩትን መሰል ስህተቶች እንዳይፈጠሩ ጥንቃቄ እንደሚደረግ አቶ ያሬድ አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ያሬድ ገለጻ፤ በቀን ገቢ ግምት ጥናት ወቅት የንግድ ቦታ ዘግቶ መጥፋት፣ ከንግድ መደብሩ ዕቃ ማሸሽ፣ ሥራ የለም በማለት ለመረጃ ሰብሳቢ ኮሚቴ የተዛባ መረጃ መስጠት፣ ከ18ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን በማስቀመጥ መረጃ እንዳይሰበሰብ እንቅፋት መፍጠር፣ የቀን ገቢ ግምት እንዲቀነስ ለገማቾች መደለያ መስጠት የመሳሰሉት ተገቢ ታክስ እንዳይሰበሰብ ያደረጉ ምክንያቶች ነበሩ፡፡ አዲሱ የቀን ገቢ ግምት አማካኝ የቀን ገቢ ጥናት በማከናወን ከተማ አቀፍ የሆነ ተአማኒነት ያለው፣ ፍትሃዊ፣ ለቅሬታ ተጋላጭ ያልሆነና የግብር ከፋዮችን ትክክለኛ ደረጃ ማዕከል ያደረገ ሲሆን፤ ወደ ታክስ ስርዓቱ ያልገቡትን ህጋዊ መስመር ተከትለው እንዲሰሩ የሚያደርግ በመሆኑ በዘርፉ ያለውን ችግር በተወሰነ ደረጃ ማቃለል የሚያስችል ነው፡፡

በሾላ ገበያ በቅመማ ቅመም ዘርፍ ተሰማርተው የሚሰሩት አቶ መኩሪያ (ስም የተቀየረ) ፤ የቀን ገቢ ግምት አወሳሰን ላይ ችግር ይስተዋላል፤ ተመሳሳይ ስራ እየሰራን እንኳ የተለያየ መጠን ግምት ይጣልብናል፤ አንዳንዴ እንደዕድል ሆኖ ገበያ ይኖራል፣ አንዳንዴ ደግሞ ለተከታታይ ቀናት እንኳ ገበያ አይኖረንም፤ እርግጥ የተወሰኑ ቀናቶች ተወስደው አማካይ የገቢ ግብር ውሳኔ ቢኖርም ትክክለኛ አወሳሰን ነው ለማለት እቸገራለሁ ይላሉ፡፡

ከስድስት ዓመት በፊት የንግድ እንቅስቃሴው ካለፉት ዓመታት ጋር ሲወዳደር የትኛው የተሻለ ነው የሚል የቀን ገቢ ግምት ጥናት ተደርጎ ነበር፤ ይህን ሊያውቀው የሚችል በስራው ላይ የተሰማራው ነጋዴ ነው፡፡ ለምሳሌ ባለፈውና በዚህ ዓመት የንግድ እንቅስቃሴው ተቀዛቅዟል፤ ከሁለት ዓመት በፊት የነበረው ሥራ ከአምናውና ከዘንድሮው ጋር ሲነጻጸር ምንም አይገናኝም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሥራው አያስደስትም፡፡ ይሁን እንጂ ጥናቱን የሚያከናውኑ ባለሙያዎች ይህን ከግምት ውስጥ ያስገቡታል ለማለት ይከብደኛል፡፡ ለዚህም ነው በአወሳሰኑ ላይ ችግር ሊኖር ይችላል ይላሉ እኒሁ ነጋዴ፡፡

የቀን ገቢ ጥናት መካሄድ የሚገባው በየስድስት ዓመቱ በመሆኑና ከከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ማደግ ጋር ተያይዞ በህገወጥ መንገድ የሚሰሩ ነጋዴዎች እየተበራከቱ መምጣት ጥናቱ እንዲከናወን አድርጓል፡፡ ምክንያቱም ህገወጥ ነጋዴዎች እየተበራከቱ መምጣታቸው ህጋዊ መስመር ተከትለው በሚሰሩት ላይ ተጽዕኖ ከመፍጠሩ ባሻገር ከውድድር ውጭ እንዲሆኑም ያደርጋል የሚሉት ደግሞ በባለስልጣኑ የአዲስ አበባ ታክስ ፕሮግራምና ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ነጻነት አበራ ናቸው፡፡

እንደ ምክትል ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ የጥናቱ ዋና አላማ ወደ ታክስ ስርዓቱ ያልገቡትን ነጋዴዎች ለማስገባት ከመሆኑ ጋር የቀን ገቢ ጥናት በየስድስት ዓመቱ መስራት ካልተቻለ የታክስ ስርዓቱን ከንግድ እንቅስቃሴው ጋር አብሮ ማስኬድ አይቻልም፡፡ ይህም መንግሥት ማግኘት ያለበትን ጥቅም ያሳጣል፡፡

ከከተማዋ ከ40 እስከ 52 ቢሊዮን ብር የመሰብሰብ አቅም እንዳለ ጥናቶች ቢያመላክቱም ይህን ለመሰብሰብ የሚያስችል ምንም ሁኔታ የለም፡፡ አንዳንድ ነጋዴዎች ‹ከተማ አስተዳደሩ 40 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ነው መረጃ እየሰበሰበ ያለው› የሚሉት ሃሳብ የተሳሳተ ሲሆን፤ በጥናቱ የተገለጸው የገንዘብ መጠን አጠቃላይ የከተማ አስተዳደሩን አቅም ለማሳወቅ እንጂ ግብር ከፋዩ ይህን መክፈል አለበት ማለት አይደለም ያሉት ወይዘሮ ነጻነት፤ በወሬ ደረጃ እንደሚነገረው ከፍተኛ ገንዘብ ለመሰብሰብ የታቀደ ነገር አለመኖሩን፤ነገር ግን በ2009 በጀት ዓመት 26 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልፀዋል፡፡

 

ዑመር እንድሪስ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829516
TodayToday1146
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7236
This_MonthThis_Month29696
All_DaysAll_Days2829516

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።