ለኢንዱስትሪው ጥያቄ ጭላንጭሉ ተስፋ Featured

18 May 2017

ዜና ትንታኔ

በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ በሂደት ወደ ኢንዱስትሪው የመሪነት ሚና እንዲሸጋገር ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ለእዚህ መዋቅራዊ ሽግግር የሚሆን ብቁ የሰው ኃይል በብዛትና በጥራት በማፍራት በኩል ያለው ውጤት ብዙ እንደሚቀረው ይነገራል፡፡ በመሆኑም ይሄን የፍላጎት ክፍተት ሊደፍን የሚችል የትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ውጤታማነት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ትምህርት ሚኒስቴር ሰሞኑን አስታውቋል፡፡

በዝግጅት ላይ የሚገኘው ለቀጣዮቹ 15 ዓመታት የሚያገለግለው ፍኖተ ካርታ ስድስት ክፍሎች አሉት፡፡ በቅድመ መደበኛ፣ በመደበኛ፣ በሁለተኛ፣ በቴክኒክና ሙያ፣ በከፍተኛ ትምህርት እንዲሁም በመምህራን ልማትና በተቋማዊ ፖሊሲና አስተዳደር ላይ ትኩረቱን ያደርጋል፡፡ በአገሪቱ የትምህርት ፖሊሲ ማዕቀፍ ውስጥ የሚዘጋጁ እቅዶች በተለያዩ ወቅቶች ሲተገበሩ ቢቆዩም የአሁኑ ፍኖተ ካርታ ከቀደሙት የተለየ መሆኑን ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

የትምህርት ስትራቴጂ ማዕከል ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አድማሱ ሽብሩ፤ አሁን ያለው የአገሪቱ የኢኮኖሚ ጉዞ የሚፈለገው በአገር አቀፍ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ፣ ብቁ፣ ለፈጠራ የተዘጋጀ፣ ምክንያታዊ፣ የተሟላ ሰብዕና ያለው የሰው ኃይል መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም አሁን ያለውን የትምህርት ስትራቴጂ በአግባቡ መፈተሽ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

የፍተሻው አንድ አካል የሚሆነው ፍኖተ ካርታ የትምህርት ሥርዓቱን ውጤታማነት በማረጋገጥ፤ የትምህርት ተቋማት በየጊዜው የሚያፈሩት ባለሙያ ምን አይነት ዜጋ መሆን አለበት? የሚለውን ለመመለስ ያግዛል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚተገበሩ ዘላቂ የልማት ግቦችን ከግምት ከማስገባት ባሻገር ዕቅዶቹን ለማሳካት የሚያስችል የባለሙያዎችን ዝግጅት ማቀላጠፍ ያስችላል፡፡ በየዓመቱም በአነስተኛ፣ በመካከለኛና በከፍተኛ ደረጃ የሚያስፈልጉ ባለሙያዎችን ለማፍራት ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው፡፡

የሁለተኛው የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርና የሰው ኃይል ብቃት እንደማይነጣጠሉ ያስቀምጣል፡፡ ለአገሪቱ ዕድገት ዘላቂነት ወሳኝ በሆነው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ማረጋገጥ ሂደት እንዲሁም ወደ መካከለኛ ገቢ ኢኮኖሚ የሚደረገው ጉዞ ያለ ኢንዱስትሪ ልማት አስተማማኝ እንደማይሆን ይተነትናል፡፡ ለእዚህም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ መስፋፋት የአጠቃላይ ኢኮኖሚውን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ከማሳደጉም በላይ የቴክኖሎጂ አቅም ክምችት፣ የዜጐች የኢንዱስትሪ ሙያ አቅም እንዲጠናከር ማድረግ ወሳኝ መሆኑንም ያስቀምጣል፡፡

ከአምስት ዓመቱ ዕቅድ ባሻገር በ1994 .ም በወጣው የትምህርት ፖሊሲ መነሻም በየአምስት ዓመቱ የተለያዩ የትምህርት ልማት መርሀ ግብሮች ሲዘጋጁ ቆይተዋል፡፡ ይሄኛው ፍኖተ ካርታ ከእስካሁኖቹ ዕቅዶች የሚለይበትን ባህሪ በተመለከተ፤ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ጉዞ መነሻ በማድረግ ወደፊት የሚተነበይ መሆኑን ዶክተር አድማሱ ያብራራሉ፡፡

በዚህ መነሻ ‹‹አገሪቱ ትልቅ ራዕይ አስቀምጣ እየተንቀሳቀሰች ነው›› የሚሉት ምክልት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የግብርና መር ክፍለ ኢኮኖሚውን የመሪነት ሚና በሂደት ወደ ኢንዱስትሪ በማሸጋገር መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት እንዲቻል በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይጠይቃል፡፡ በዚህ ራዕይ የተቃኘው ፍኖተ ካርታ የሰው ኃይል ለማፍራት ተደራሽነት፣ ጥራት፣ ፍትሐዊነት እንዲሁም በአጠቃላይ የመማር ማስተማር ሥርዓቱ ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም፤ አገሪቱ ከግብርና መር ክፍለ ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ስትሸጋገር የፈፃሚዎች የአመለካከት፣ የክህሎትና የእውቀት ድምር ውጤት መዳበር ወሳኝ ነው ይላሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ፍኖተ ካርታው የትምህርትና ሥልጠና ሥርዓቱ ምን መያዝ አለበት የሚለውን የሚመልስ ጥናት ይሆናል ባይ ናቸው፡፡ ፍኖተ ካርታው በትምህርትና ሥልጠናው ዘርፍ የተለያዩ ጉዳዮችን የሚያካትት ቢሆንም ቁልፍ ማጠንጠኛውን በተደረሰበት የኢኮኖሚ አቅም ላይ የኢንዱስትሪ ልማቱ ምን አይነት የሰው ኃይል ይፈልጋል የሚለውን መመለስ ይችላል፡፡

‹‹መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው አገሮች ስንቃረብ ኢንዱስትሪው የመሪነቱን ሚና እንዲወስድ በትምህርትና ስልጠና ፖሊሲው ይሄንን የሚመግቡ ሥራዎች መከናወን አለባቸው›› የሚሉት ዶክተር ሽፈራው፤ የሰው ኃይል ዝግጅት የአንድ ጀምበር ሥራ ሳይሆን የተራዘመ ዝግጅት ስለሚፈልግ፤ እስካሁን የተገኙ ስኬቶችና ወደፊትም ሊቀጥሉ የሚገባቸው ተግባራት ምን እንደሆኑ የሚያመላክት ይሆናል፡፡

በአሁኑ ወቅት ፍኖተ ካርታውን ለማጠናቀቅ የንድፈ ሃሳብ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ በሁሉም ክልሎች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የመስክ ምልከታም ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ በቀጣይም ጥናቶቹ በተለያየ ደረጃ ለውይይት ከቀረቡ በኋላ የትኛው ተሞክሮ ይወሰድ? የትኛው ይቅር? የትኛው እንዳለ ይቀጥል? የሚሉ ሃሳቦችን ከአገሪቱና ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ በመነሳት ምክረ ሃሳብ ይወጣል፡፡

በፍኖተ ካርታው ዝግጅት ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከ80 በላይ ባለሙያዎች በጥናት መሳተፋቸውን የማዕከሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አድማሱ ይናገራሉ፡፡ በዝግጅት ምዕራፍ በሁሉም ክልሎች ያለው ሁኔታ እንዲዳሰስ ከማድረግ ባሻገር፤ ከየዘርፉና ከተለያዩ ተቋማት እንዲሁም የማህበረሰብ ክፍሎች መነሻ የሚሆኑ ሃሳቦች በግብዓትነት ተሰብስበዋል፡፡

በቀጣይም በሥራው የሚሳተፉ ባለሙያዎች ጉዳዩን በጥልቀትና በጥንቃቄ በማየት የወደፊቱን አገራዊ የትኩረት ነጥቦች መለየት እንደሚገባቸው ዶክተር አድማሱ ይመክራሉ፡፡ ሥራዎቹን ወደ ተግባር ለማሸጋገር ተግዳሮት የሚሆኑ ጉዳዮች አለመኖራቸውን በመጥቀስ፤ ሥራውን ቀድሞ ለማጠናቀቅ የሚያስችል ጅምር ቢኖርም በተለያዩ ምክንያቶች ለወራት መዘግየቱን ይገልጻሉ፡፡

እንደ ዶክተር አድማሱ ማብራሪያ፤ ሁሉን አቀፍ የሆነው ፍኖተ ካርታ አገሪቱ ለምትገኝበት ዕድገት ቀጣይነት ዋስትና እንደሚሆን ይታመናል፡፡ በጅምር ላይ ለሚገኘው የኢንዱስትሪ ክፍለ ኢኮኖሚም ብቁ ባለሙያዎችን በመመገብ ቀጣይ ጉዞውን የሚያፋጥን ይሆናል፡፡ ዛሬ ላይ ሆኖ ስለውጤቱ መግለፅ ባይቻልም የፍኖተ ካርታው አስፈላጊነት የሚለካው ዕቅዶችን ወደ መሬት ለማውረድ ሲያስችል መሆኑ አይካድም፡፡

ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪው የሚመጥነውን የሰው ኃይል እንደሚፈልግ የሚገልጹት ባለሙያዎች፤ የውጤታማነት መለኪያውም ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ሊያመጣ በሚችል መልኩ መሆን እንደሚገባው ይስማማሉ፡፡ በቅድሚያ ግን ገና በጅምር ላይ የሚገኘው ጭላንጭል የፍኖተ ካርታ ተስፋ ብርሐኑ ጎልቶ መታየት የግድ ይለዋል፡፡

 

ብሩክ በርሄ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829538
TodayToday1168
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7258
This_MonthThis_Month29718
All_DaysAll_Days2829538

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።