ብዙ ያልተደከመበት የኢኮኖሚው ዲፕሎማሲ Featured

17 May 2017

ዜና ትንታኔ

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስኬታማ እንደሆነ በመንግሥትና በአንዳንድ ምሁራን ይገለጻል። ስኬታማነቱ ግን የበቃለት ነው የሚባል እንዳልሆነና ብዙ ቀሪ ሥራዎች እንዳሉበት ዘርፉን ጠንቅቀው የሚያውቁ ባለሙያዎች እየተናገሩ ናቸው።

የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ውጤት መገለጫ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል ዋናው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መጠን ስለመሆኑ ምሁራን ይናገራሉ። ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተገኘው መረጃም ከዘርፉ የሚገኘው ተጠቃሚነት እየጨመረ መምጣቱን ይገልጻል። ባለፈው ዓመት ብቻ ሦስት ነጥብ 14 ቢሊዮን ዶላር፤ በዘንድሮው ስድስት ወራት ውስጥ ደግሞ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ወደ አገር ውስጥ ገብቷል። የዘንድሮው የስድስት ወራት መጠን ካለፈው ዓመት ተመሰሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም በ35 በመቶ ብልጫ አለው።

በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲውን "ለኢትዮጵያ አዲስ ግንባር ነው" ሲሉ ይገልጹታል። እንደ አገር በዚህ የዲፕሎማሲ መስክ ኢንቨስትመንትን በማምጣት፣ ቱሪስቶችን በመሳብ፣ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እንዲሳለጡ በማገዝ የተወሰኑ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል። ነገር ግን አገሪቷ ከምትጠበቀውና ህዝብ ከሚፈልገው አኳያ የተፈለገውን ያህል እርቀት ተሂዷል ማለት አይቻልም ነው የሚሉት።

የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ የፖለቲካ፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነትና የሰላምና ጸጥታ መምህሩ ዶክተር ጌታቸው ዘሩ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ትልቅ ቦታ ሰጥቷል ይላሉ። በማሳያነት የሚያነሱትም የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምን ወደ ጎን በማለት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ካላቸው ከማንኛውም አገራት ጋር እየሰራ መሆኑን ነው። መስኩ በኢንቨስትመንት፣ በእርዳታ፣ በብድር፣ በቱሪዝምና በሌሎች ዘርፎች ውጤት አምጥቷል። አገሪቱ እያስመዘገበቸው ያለው ፈጣን የኢኮኖሚው ዕድገትም የዚህ ውጤት ነው ሲሉም ይገልጻሉ።

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሣይንስ ስትራቴጂክ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪው ሰለሞን ገብረዮሐንስን ደግሞ፤ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ በአገራት፣ በአህጉራት፣ በዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ በሚሰራ ሥራ የአገሪቱን ድህነት እንዲቀነስ ብሎም እንዲጠፋ የማድረግ ዓላማ አለው ይሉና፤ ኢትዮጵያ ከዚህ አንጻር ስትመዘን በአፍሪካ አገራት ላይ እየሰራች ያለው ሥራ በቂ አይደለም የሚል ነጥብ ያነሳሉ። "ከጎረቤቶቻችንና ከአፍሪካ ጋር በኢኮኖሚው መስክ የተፈጠረው ትስስር ብዙም አርኪ አይደለም። ያደጉት አገራት አፍሪካ ላይ ትኩረት አድርገው እየሰሩ ናቸው። እኛም ብዙ አማራጭ ስላለን በትኩረት መስራት አለብን። ነገር ግን ስራችን ያን ያህል ነው። በተለይ አሁን ከኤሌክትሪክ ሀይል ልማቱ ጋር ተያይዞ ግብጾች ኢትዮጵያ ግድብ ልትሰራ የቻለችው ከአፍሪካውያን ጋር ተባብራ በመስራቷ ነው በሚል ወደ አፍሪካ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው መስክ በስፋት እየገቡ ናቸው። በመሆኑም ተወዳዳሪ የሆነ ሥራ መስራት ይገባል"

የወለጋ ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ኢኮኖሚክስ ምሁሩ ዶክተር ደምሴ ፍርዲሳ ደግሞ፤ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው መስክ ለውጦቹ መኖራቸውን የሚካድ ባይሆንም አሁንም ግን ድከመቶች እንዳሉ ያመለክታሉ። "የአገሪቷ የኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲ ማስተዋወቅ ላይ ያተኮረ ነው። ባለሀብቶችም ይሁኑ ቱሪስቶች አገር ቤት ከመጡ በኋላ የአያያዝ ችግር አለ። የመጣውን ኢንቨስተር ለማቆየት ከሌሎች አገራት ጋር ተወዳዳሪ መሆን ይገባል። ከዚህ አንጻር መንግሥትም እንደሚያምነው የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችገሮች አሉ። ክልሎችና የፌዴራል መንግሥት አንድ ቃል መናገርና ተጋግዘው መስራት ላይ ውስንነቶች አሉባቸውና ይህንን ማስተካከል ያስፈልጋል" ሲሉም አብራርተዋል።

በእርግጥ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ከ1990ዎቹ በፊት ከነበረበት አንጻር ሲታይ የተሻለ በሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ምሁራን ይናገራሉ። በተለይም አዲሱ የውጭ ጉዳይና አገራዊ ደህንነት ፖሊሲ ከመውጣቱም በፊት ይሁን በቀደመው የደርግ ስርዓት ዘመን የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ትኩረቱ በርዕዮተ ዓለም ላይ የተገደበ ስለነበር አገሪቷ ከኢኮኖሚው ይልቅ ለወታደራዊው መስክ ትኩረት ሰጥታ ኖራለች። በዚህም የኢኮኖሚ ዕድገት ብሎ ነገር የሚታሰብም ያልነበረም እውነታ ሆኖ ቆይቷል። አገሪቷም ከዓለም ጭራ ሆና ዘመናትን እንድትገፋ ስለመገደዷ ምሁራኑ ይገልጻሉ።

የመለስ አካዳሚው ዶክተር ጌታቸው አሁንም ቢሆን የውስጥ ፖለቲካ ችግር ካልተፈታ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ቀጣይ እንዳይሆን ያደርጋል። ይህን መፍታት ለነገ የማይባል የቤት ስራና የኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲው ቀጣይነት ማረጋገጫ ነው ይላሉ። "ዲፕሎማቶቻችን በአፍሪካ ያለውን የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መጠቀም ይጠበቅባቸዋል። በቂ ልምድ ሊያዳብሩ፤ ትምህርትም ሊሰጣቸው ይገባል። ይሄንን ማድረግ ከተቻለ አሁን ካለውም በላይ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል።

በኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲ ሀብት “የት አለ?” ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል የሚሉት ዶክተር ደምሴ፤ ኢትዮጵያ ያላት ሀብት ምንድን ነው? ብሎ ከየትኞቹ አገሮች ጋር ጥሩ አማራጮች እንደሚኖር በማስቀመጥና ርዕዮተ ዓለማዊ ሁኔታን በደንብ በማጥናት መስራት ከተቻለ በሌላው የዲፕሎማሲ መስክ የተገኙትን ድሎች በኢኮኖሚው መስክም መድገም ይቻላል።

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲው ተመራማሪው አቶ ሰሎሞን በበኩላቸው፤በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስኬታማ ሊያደርጉ የሚችሉ የተለያዩ የፖሊሲ ማዕቀፎችንና ህጎችን ማውጣትና በዚያ መሰረት መስራት ይገባል ባይ ናቸው። አማራጮችን ማስፋትና የመረጃ ፍሰቱን ማሳለጥ እንደሚገባም ያሳስባሉ። በአጠቃላይም የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስኬታማ ነው የሚባለው መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ሲቻል ነውና ዲፕሎማቶቹ ይህን ለማሳካት አገራትን መርጠው ቀጣይነት ያለው እንቅስቃሴ ማደረግ አለባቸው ሲሉም ያብራራሉ። የኤፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን በዚህ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጠን ያደረግነው ጥሪት አልተሳካልንም።

 

አጎናፍር ገዛኽኝ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829520
TodayToday1150
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7240
This_MonthThis_Month29700
All_DaysAll_Days2829520

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።