ከዓድዋ ምን - እንዴት እንማር? Featured

25 Feb 2017

ዜና ትንታኔ

የዓድዋ ድል የፓን አፍሪካኒዝም መሰረት መሆኑን የኢትዮጵያውያንን የአድዋ ውሎ ከዘከሩ የታሪክ ጠበብት መካከል የዋሽንግተኑ የታሪክ ሊቅ ፕሮፌሰር ራየሞንድ ጆናስ “ዘ ባትል ኦፍ አድዋ-አፍሪካን ቪክትሪ ኢን ዘ ኤጅ ኦፍ ኢምፓየር” በሚለው ጽሁፋቸው አስፍረዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ፤ በዚህ ጽሁፋቸው የአድዋ ድል ለአፍሪካውያን ቅኝ አገዛዝን ታግሎ መጣል እንደሚቻል ያሳየ፤ የኢትዮጵያንም ታላቅነት ያስመሰከረ ስለመሆኑ ደጋግመው ያወሳሉ፡፡

ዓድዋ ለእኔ ነጻነቴ ነው፤ ክብሬም ነው፤” የሚሉት የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፤ በ1888 .ም የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያንን ጀግንነት ያሳየ ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ህዝቦች የአሸናፊነት መንፈስን ያጎናጸፈ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ኢትዮጵያ የራሱ የሆነ ባህል፣ ታሪክና ማንነት፣ ያለው፣ በራሱ ቋንቋ የሚናገር ህዝብ ያላት አገር እንደሆነች ለዓለም ህዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስመሰከረችበትም እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ ህዝቡ በየአካባቢው በራሱ ባህል የሚኖር፣ እርስ በእርሱ የሚጣላ እንኳን ቢሆን የውጭ ወራሪ ሲመጣበት ልዩነቱን ወደጎን ትቶ በአንድ የሚተባበር፣ በአገሩ ጉዳይ ላይ የማይደራደር መሆኑን ጠላት በሚገባ የተገነዘበበት ድል መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡

ዓድዋ ሲከበር ውስጤ የደስታ ስሜት ብቻ ሳይሆን ኩራትም ይሰማዋል፡፡ ለአያት ቅድመ አያቶቻችን ትልቅ ዋጋ መስጠት እንዳለብን ይነግረኛል፡፡” የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ሲሳይ መንግስቴ ናቸው፡፡ የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ስልጣኔ፣ ጀግንነትና ብልህነት ለነጮች ብቻ የተተወ ይመስላቸው ለነበሩ አፍሪካውያን ሁሉ የነጻነት ጮራ የፈነጠቀ የይቻላል መንፈስ ያሰረጸ እንደሆነም ያምናሉ፡፡

የኢኮኖሚና ፖለቲካ ሙሁር የሆኑት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ ደግሞ፤ የዓድዋ ድል ለመላው ጥቁር ህዝብ ደስታ የፈጠረውን ያህል፣ አውሮፓውያንን ያስደነገጠም እንደነበር ይናገራሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት የአድዋው ድል ኢትዮጵያ ምንጊዜም በልጆቿ ተጋድሎ ነፃነቷ ተከብሮ ታሪኳና ባህሏ ተጠብቆ እንደኖረና እንደሚኖር ያረጋገጠ ነው። ሆኖም ግን የአድዋን ድል በዓመት አንድ ቀን በሚካሄድ ስብሰባ ከመዘከር ባለፈ ትውልዱ በሚፈልገው ልክ እንዲረዳው አልተደረገም፡፡

ልጅ ዳንኤል ጆቴ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ የአድዋ ጦርነት ወራሪ ጦር ድል የተመታበት ሲሆን የአሁኑ ጦርነት ደግሞ ድህነትን፣ ድንቁርናን፣ ሙስናና ብልሹ አሰራርን ታግሎ የማሸነፍ ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች ማሸነፍና ነገን እውን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ ለዛሬነታችን መሰረት የሆነውን ትናንትን ስናውቅና ዛሬን በትክክል ስንሰራ ነው፡፡

ወጣቱ የኢትዮጵያ የሰላምና የነጻነት ሰንደቅ ዓላማ በእጁ ነው፡፡ ይሄን መሬት ላይ ቢጥለው አብሮ ይከሰከሳል” የሚሉት ልጅ ዳንኤል ወጣቱ ከአድዋ ድልና ከድሉ ባለቤት ጀግኖች ይቻላል የሚለውን የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ተላብሶ ችግሮችን ለመፍታት ከራሱ መጀመርና በሚያከናውነው ተግባር ጥቅም ለማግኘት ሳይሆን አገራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ብሎ መስራት እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ ለዚህም “የአድዋ ጀግኖች ከየአቅጣጫው ወደአድዋ የተመሙት ከንጉሱ ወይም ከመንግስት ጥቅም እናገኛለን ብለው በማሰብ ሳይሆን አገርን ሊወር የመጣን ጠላት አንገት አስደፍቶ ከአገር ማባረርን ዓላማ አድርገው፤ የአገር ክብርና የወገን ዝናን አስቀድመው እንጂ፡፡” በማለት በአብነት ይጠቅሳሉ፡፡

አቶ ሲሳይም መንግስቴም በዚህ ሀሳብ ይስማ ማሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ዓድዋ ፖለቲካዊ ነጻነታችንን አረጋግጦልን ያለፈ ቢሆንም፤ በዚህ ዘመን ፖለቲካዊ ነጻነት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ የዳበረ ኢኮኖሚ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ከአድዋ ጀግኖች መተባበርን፣ ጽናትንና አሸናፊነትን ለመማርና ሀላፊነትን ለመወጣት የሁሉም ዜጋ በተለይም የወጣቱ ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡

የዓድዋ በዓል ለእኔ ከሁሉም በዓላት በላይ ነው፡፡ ምክንያቱም የነጻነት ዋጋ ያጣጣምንበት፣ ነጮችን ማሸነፍና ማንበርከክ እንደሚቻል ያሳየንበት ነው፡፡ ይሄን ካሰብን ዓድዋ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች በዓል ነው፡፡ የሚሉት አቶ ሲሳይ፤ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የፓርቲ አባላትና መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ትምህርት ቤቶችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ በአጠቃላይ ሁሉም ዜጎች ሊያከብሩት፤ ሊጠብቁትና ሊያስቡት፤ ለመጪውም ትውልድ ሊያስተላልፉት እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ እርሳቸው እንደሚናገሩት በዓሉ እንደ ታላቅነቱና እንዳለው ብሄራዊ ፋይዳ በደመቀና ሁሉንም በሚያንቀሳቅስ መልኩ እየተከበረ አይደለም፡፡ አፄ ኃይለስላሴ ለንግሥ በዓላቸው፣ ደርግም ለመስከረም ሁለት ይሰጡ የነበረውን ትኩረት ያህል ለአድዋ በዓል ሲሰጡ አልተስተዋሉም፡፡ አሁንም ቢሆን ለሌሎች በዓላት፤ ለድርጅቶችና ተቋማት ምስረታ በዓላት የሚሰጠውን የሚዲያ ሽፋን፣ የዶክመንተሪና ሌሎች መርሃ ግብሮች ለአድዋ በዓል እየተሰጠ አለመሆኑን ያወሳሉ፡፡

ይህን ሀሳብ የሚጋሩት ዶክተር ቆስጠንጢኖስም፣ “አሁን አንዱ የሚያስደነግጠው ነገር ድሮ የነበሩና ኢትዮጵያ የምትባል አገር ያስረከቡንን መሪዎቻችንን ማሞገስና መዘከር እንደተከለከለ አይነት ነው የማየው፡፡ ምክንያቱም፣ በስም እየተጠቀሱ ሲወገዙ እንጂ መልካም ስራቸው ሲነገር አይሰማም፡፡ በየአደባባዩም የእነዚህን የአገር ባለውለታ መሪዎች ሳይሆን፤ የተለያዩ ድርጅቶችን ማስታወቂያዎችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሰዎችን ሀውልት እየሰራን ነው ያለነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በአንድ ወቅት ጥቁሮችና ነጮች በአንድ አውቶቡስ የማይሄዱባት አሜሪካ አሁን በጥቁር እየተመራች ወደታላቅነት ስትገሰግስ፤ “እኛ ግን በ18ኛውና 19ኛው ክፍለ ዘመን በነበረ አስተሳሰብ በታሪካችንና ማንነታችን እንጨቃጨቃለን፡፡ ይህ ሲታይ ከአድዋ ታሪክ የወሰድናቸው ነገሮች አሉ ለማለት አልደፍርም” ይላሉ፡፡

አቶ ሲሳይ በበኩላቸው፣ “በየዘመኑ ስልጣን ላይ የሚቀመጡ መንግስታትና ፖለቲከኞች አድዋን ባሰቡ፣ ባከበሩና ባገዘፉ ቁጥር የእነርሱ ክብር የሚደፈቅባቸው ስለሚመስላቸው ብዙ ትኩረት ሲሰጡት አይታይም” ሲሉ ይወቅሳሉ፡፡ ሚዲያውም ባለስልጣናቱን ተከትሎ ስለሚሄድ በተመሳሳይ ትኩረት አለመስጠቱንም ይተቻሉ፡፡ በመሆኑም የፌዴራል መንግስቱም በአግባቡ አስቦበት ሊያከብረውና መልዕክት ሊያስተላልፍበት፤ የክልል መንግስታትም ይህን መሰሉን ብሔራዊ በዓል ቢያንስ ከክልል በዓላት እኩል ቢያዩት ትልቅ ትርጉም እንዳለው ያብራራሉ፡፡

ለምሳሌ አጼ ምኒልክን የአንድ ጎሳ መሪ እንደነበሩና ሌላውን በቅኝ ግዛት ሲይዙና ሲጨቁኑ እንደነበረ ብቻ ነው የሚታየው እንጂ፤ አገር እንዳቀኑ፣ ጣልያንን አሸንፈው ለአፍሪካም ኩራት እንደሆኑ፣ ኢትዮጵያ የሚባል ካርታን መስርተው እንዳለፉ አይደለም እየተነገረ ያለው፡፡” የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ይሄንኑ ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡ ሆኖም ከዚህ አይነቱ አስተሳሰብ ወጥቶ ታሪክ በጥሩነቱም ሆነ በመጥፎነቱ ህዝቡ እንዲያውቀው ቢደረግ ከመጥፎው እንዲማር፤ ጥሩውን ደግሞ እንዲያዳብረው የሚያስችል መሆኑን ይመክራሉ፡፡

በኢትዮጵያውነታችን ለሚያኮራንና በብዙ መስዋዕትነት ለተገኘው ድል ተገቢውን ክብር ሰጥቶ ትውልዱን በማስተማር እንዲሁም የታሪክ ሙሁራን ተገቢውን መረጃ በመሰብሰብ ታሪኩን በመሰነድ እንዲተላለፍ በማድረግ ትውልዱ ትክክለኛ ታሪክ እንዲይዝና ከታሪኩ ተምሮም የተሻለ አገራዊ ድርሻውን እንዲወጣ ማድረግ እንደሚገባ ነው ሙሁራኑ የሚመክሩት፡፡

 

ወንድወሰን ሽመልስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829521
TodayToday1151
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7241
This_MonthThis_Month29701
All_DaysAll_Days2829521

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።