ኢትዮጵያ ብረትና ኤሌክትሮኒክስ Featured

21 Dec 2016

- ለዓለም ገበያ ታቀርባለች

- ከዓለም ገበያ ትገዛለች

 

ዜና ትንታኔ

ኢትዮጵያ በ2006 .ም የብረታ ብረት ኢንጅነሪንግ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን ከዓለም ገበያ ለመሸመት 12 ነጥብ ስድስት ቢለዮን ብር ወጪ አድርጋለች። እየተመዘገበ ካለው ፈጣን ዕድገት ጋር ተያይዞም የዘርፉ ምርት ፍላጎት በየዓመቱ በከፍተኛ መጠን እያደገ ስለመሆኑና ወደፊትም እንደማይገታ ጥናቶች ያመለክታሉ። አገሪቷ የዘርፉን ምርት በአገር ውስጥ ምርት ለመተካትና እያወጣች ያለውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት ግብ ጥላ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነች መሆኑም ይታወቃል፡፡ ለመሆኑ ይህ ግብ ሊሳካ የሚችለው ምንና እንዴት ቢሰራ ይሆን?

የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወርቅነህ ደለለኝ እንደሚናገሩት፤ ባለፉት ዓመታት በተደረገው ርብርብ በብረታ ብረትና ኮንስትራክሽን ምርት ከውጭ የሚገባውን ምርት የሚተካ አቅም ተፈጥሯል። ይሁን እንጂ የመንግሥትም ሆነ የግል ድርጅቶች ተመሳሳይ ምርት ከውጭ አገር እየገዙ በማስገባት ሀብት እያባከኑ የአገር ውስጥ የማምረት አቅምንም እያዳከሙ ናቸው። ለምሳሌ በአንድ ወር ውስጥ ብቻ 40 ሺህ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ። የአገር ውስጥ ተሽከርካሪ ፋብሪካዎች ደግሞ ገበያ በማጣት ከአቅማቸው ከ15 እስከ 20 በመቶ ብቻ እያመረቱ ናቸው።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻም፤ የጥራት ችግር ነው እንዳይባል በአንዳንድ ምርቶች ከአገር ውስጥ ገበያ አልፎ ለዓለም ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ተጀምሯል። ባለፈው ዓመት ከዘርፉ 22 ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል። ዘንድሮም በአምስት ወራት ውስጥ የብረታ ብረት ኢንጅነሪንግና ኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን (ሞበይል ቀፎ፣ የእርሻ መሳሪያዎች፣ ጌጣጌጦች፣ የቤት እቃዎች፣የአሌክትሪክ ገመድና ሌሎች) ወደ አፍሪካ፣ አውሮፓ፣ መካከለኛው ምስራቅና አሜሪካ (29 አገራት) በመላክ ዘጠኝ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። ከውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ባሻገር ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያን ገጽታ በመቀየር በኩል ያለው ፋይዳ ቀላል አይደለም፡፡

በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የኤሌክትሪካልና መካኒካል ምህንድስና ዲኑ ዶክተር ሱልጣን ፈይሶ፤ የአገር ውስጥ ፍላጎትን በአገር ውስጥ ማሟላትና ከዚህ አልፎ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘቱ ይበል የሚያስብል ነው ይላሉ። ነገር ግን የአገር ውስጥ የብረት የነፍስ ወከፍ ድርሻ በጣም አንስተኛ በመሆኑ ገና ብዙ መሥራት ያስፈልጋል ባይ ናቸው። በተጓዳኝም በዓለም ገበያ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት የአገር ውስጥ ሸማቾችንም ፍላጎት ለማርካት በምርት ጥራት በኩል ቀሪ የቤት ሥራ አለ ብለው ያምናሉ።

የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ወርቅነህ የጥራት ችግር አለ የሚለውን እንደማይቀበሉ ይገልጹና የብረት የነፍስ ወከፍ ድርሻ አነስተኛ ነው የሚለውን ይቀበላሉ። ከሁለት ዓመት በፊት የኢትዮጵያውያን የብረት ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ድርሻ 12 ኪሎ ግራም እንደነበረና ባለፈው ዓመት ወደ 33 ኪሎ ግራም ማደጉን ያመላክታሉ። በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ማጠናቀቂያ ላይም ድርሻውን 81 ኪሎ ግራም ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነም ይናገራሉ።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻም፤ በዘርፉ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የብረት ማዕድንን በአገር ውስጥ ለማውጣት፣ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ ምርታቸውን እንዲያሳድጉ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የዘርፉ አልሚዎች በአገር ውስጥ ገብተው እንዲያመርቱ እየተደረገ ነው። በዚህም እስከ 100 ሺ ቶን ያመርቱ የነበሩ ፋብሪካዎች አሁን ምርታቸውን በማሳደግ በዓመት እስከ አንድ ሚሊዮን ቶን ማምረት ጀምረዋል።

አቶ ወርቅነህ ምንም እንኳ በዘርፉ እድገት ቢኖርም፤ የተነሳሽነት ችግርና በእቅድ ያለመመራት፤ የኢንዱስትሪዎችና ዩኒቨርሲቲዎች ተቀናጅቶ አለመሥራት፤ የቴክኖሎጂ፣ የግብዓት፣ የግንዛቤ ችግርና የሚያስፈልገውን ያህል ገንዘብ አለማገኘት የዘርፉ ፈተናዎች መሆናቸውን አውስተዋል ፡፡ ለችግሮቹም አቅጣጫ ተቀምጦ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ዶክተር ሱልጣን ደግሞ፤ በአፍሪካ በተለይም በቀጣናውና በአገር ውስጥ ትልቅ ገበያ አለ። አሁን ያለውን ጅምርም በጥራት፣ በፍጥነትና በቴከኖሎጂ ማሻሻል እየዳበረ ከሄደ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም ገበያ አሸናፊ መሆን እንደሚቻል ይገልጻሉ። ለዚህም ከጥሬ እቃው እስከ ገበያውና ተጠቃሚው ድረስ በጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረተ ሥራ ማከናወን ይገባል ባይ ናቸው።

ቀደም ሲል የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ምሁሩ የነበሩትና ሰሞኑን በአዲስ መልክ በተዋቀረው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ካቢኔ ውስጥ የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ጌትነት በጋሻው በበኩላቸው፤ ለዘመናት ለውጭ አገር ምርቶች ጥገኛ ሆና የኖረች አገር ዛሬ እዚህ ደረጃ መድረሷ በእራሱ ትልቅ ድል ነው ይላሉ። የበለጠ ውጤት ለማምጣትና በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪና አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት የገበያ ስልት መንደፍ፣ ዘርፉን በጥናትና ምርምር መደገፍ የግድ ነው ሲሉ ይመክራሉ።

የዶክተር ወርቅነህ ምከረ ሀሳብ ደግሞ፤ በዘርፉ ፖሊሲና ስትራቴጂ ዙሪያ ባለድርሻ አካላት ጥብቅ ቁርኝት በመፍጠር በእውቀት ላይ ተመስርተው ተግባራዊ ማድረግ ከቻሉ በዘርፉ እየታየ ያለው አበረታች ውጤት የበለጠ ስኬታማ ማድረግ ይቻላል የሚል ነው፡፡

ዶክተር ጌትነት በበኩላቸው፤ የዘርፉን የሰው ኃይል በክህሎትና በእውቀት በመገንባት ጥራት ያለው ምርት እንዲያመርቱ ማድረግ፤ ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡና አገር በቀል ባለሀብቶችም እንዲያለሙ ማስተዋወቅና መደገፍ ዋናው ተግባር መሆን እንደሚገባው ያመለክታሉ።

እርሳቸው እንደሚሉትም፤ ዜጎች የአገር ውስጥ ምርቶችን በመግዛት ባለሀብቶችን ማበረታታት አለባቸው፡፡ ህዝቡ የአገር ውስጥ ምርትን መግዛት ኩራትም እድገትም መሆኑን እንዲገነዘብ ማድረግ ያስፈልጋል። ከአገር ውስጥ በተጨማሪ በአፍሪካና በጎረቤት አገሮች ተሰብሮ ሊገባበት የሚችል ሰፊ ገበያ ስላለ በጥራትና በዋጋ አሸናፊ ለመሆን የሚቻልባቸውን አማራጮችን ማቅረብ ያስፈልጋል።

ዋና ዳይሬክተሩ በባለሙያዎቹ ምክረ ሀሳብ ይስማማሉ፡፡ በተጨባጭም በዘርፉ ያሉት ፋብሪካዎች በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ይላሉ። የመንግሥት ተቋማትም ሆኑ ሌሎች አካላት የአገር ውስጥ ምርቶችን ምርጫቸው ቢያደርጉ አሁን ካለውም በላይ ውጤት ማስመዝገብና አገሪቷን በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ ማድረግ ይቻላል፡፡

 

አጎናፍር ገዛኽኝ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829517
TodayToday1147
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7237
This_MonthThis_Month29697
All_DaysAll_Days2829517

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።