ብዙህነትን ያስተናገደችው ኢትዮጵያ በፅኑ መሰረት ላይ መገንባቷን ፕሬዚዳንቱ ገለፁ Featured

08 Dec 2016

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፤

 

«የፌዴራላዊ ሥርዓቱ ባለፉት 22 ዓመታት ተግባራዊ በሆነው ሕገ መንግሥት መሰረት ብዙህነትን በአግባቡ በማስተናገዱ አዲሲቷን ኢትዮጵያ በፅኑ መሰረት መገንባት ከመቻሉም በላይ፤ ለአገራችን ህዳሴ ጉዞ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል» ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለፁ።

ፕሬዚዳንቱ ሕገ መንግሥቱ የፀደቀበትን 22ኛ ዓመትና የ11ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን በማስመልከት ትናንት በሰጡት መግለጫ እንደገለፁት፤ የብዙ ማንነቶች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ሃይማኖቶችና ታሪኮች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ብዙህነቷ የስጋትና የጦርነት ምንጭ ሳይሆን የውበት፣ የትልቅ ህዝብ፣ የትልቅ አገር፣ የጠንካራ አቅምና ጉልበት ምንጭና የሰፊ ገበያ ዕድልም መሆኑ በተጨባጭ ማሳየት ተችሏል።

ሕገ መንግሥቱ የፈጠረውን ምቹ ዕድል በመጠቀምም የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀደም ባሉት ዘመናት በመካከላቸው የነበረውን የተዛባ ግንኙነት በማረም፣ በመከባበር፣ በመቻቻልና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ሕብረብሔራዊ አንድነት እየጎለበተ እንደሚገኝም ፕሬዚዳንቱ አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሕገ መንግሥታዊ የጋራ እሴቶችን በመጠበቅ እጅግ በርካታ ስኬታማ ውጤቶችን በማስመዝገብ የትሩፋቱ ተቋዳሽ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

22ቱ የሕገመንግሥት ዓመታት አገሪቱ በርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ስኬቶች ማስመዝገቧን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲሁም የሃይማኖት አክራሪነት ዋና ዋና የሕዳሴው ጉዞ ተግዳሮቶች እንደነበሩ አውስተዋል። ችግሮቹ ለአገር ዕድገትና ለዘላቂ ልማት እንቅፋት በመሆናቸው፤ የተጠናከረ የሕዝቦች ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ትግል እንደሚጠይቅም ተናግረዋል።

በአገሪቱ ከጥቂት ወራት በፊት ይንፀባረቁ የነበሩት ክስተቶች አንዳንድ ፀረ ሰላም ኃይሎች ሕዝብ ከሚያነሳቸው ዴሞክራሲያዊና ሠላማዊ ጥያቄዎች በስተጀርባ መንግሥትንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ኢላማ አድርገው መንቀሳቀሳቸውን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመው፣ «ብዙህነታችንን የችግር ምንጭ በማስመሰል በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል ልዩነት ለመፍጠር፣ሰላማቸው ደፍርሶ እርስ በርስ እንዲጋጩ፣ በአጠቃላይ አገራችንን ከህዳሴ ጉዞ ለማደናቀፍና ወደ ድህነት አረንቋ ተመልሳ እንድትገባ ለማድረግ ከውጭ አፍራሽ ኃይሎች ጋር በግልፅ ሲደራደሩ ተስተውሏል» ብለዋል። ይህንን አፍራሽ ተልዕኮ በጋራ መታገል እንደሚገባም አሳስበዋል።

የዘንድሮው የብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች በተለመደው ጥንካሬ፣ሞራልና የሀገር ፍቅር ግለት የህዳሴውን ጉዞ ቀጣይነት ለማረጋገጥ ቃላቸውን ዳግም እንዲያድሱ ጥሪ አቅርበዋል።

 

ደረጀ ትዕዛዙ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0001009533
TodayToday2234
YesterdayYesterday2891
This_WeekThis_Week2753
This_MonthThis_Month49783
All_DaysAll_Days1009533

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።