የገዳ ሥርዓት በዩኔስኮ በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት ተመዘገበ Featured

01 Dec 2016

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው 11ኛው የዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች ጥበቃ የበይነ መንግሥታት ኮሚቴ ጉባኤ በትናንት ውሎው የኦሮሞ ሕዝብ ባህላዊና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የሆነው የገዳ ሥርዓት በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገብ አፀደቀ።

24 አገራት አባል የሆኑበት የበይነ መንግሥታት ኮሚቴ ጉባኤ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ገምጋሚ ቡድን በቀረበለት ሪፖርት ላይ ከተወያየ በኋላ የገዳ ሥርዓትን በማይዳሰሱ የዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ በሙሉ ድምፅ አፅድቆቷል።

የገዳ ሥርዓት ከዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች መመዝገቢያ መስፈርቶች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የሆኑትን ባህሉ በትክክል መኖሩና ህብረተሰቡ ባህሉን ተቀብሎ ለትውልድ መተላለፉን፣ ባህሉን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር የሚያስችሉ ሥራዎች መሠራታቸውና ቅርሱ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ የሚፈልገው የቅርሱ ባለቤት ህዝቡ ራሱ መሆኑን ማረጋገጥ የሚሉት መስፈርቶችን አሟልቶ በመገኘቱ ለመመዝገብ በቅቷል።

ከምዝገባው መፅደቅ በኋላ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም እንደተ ናገሩት፤ ባህላዊው የገዳ ሥርዓት በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች የራሱ የሆነ በጎ አስተዋጽኦ ስላለው ኢትዮጵያ ቅርሱን ከትውልድ ወደ ትውልድ ጠብቆ ለማቆየት ልዩ ጥበቃና ጥንቃቄ ታደርጋለች።

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው፤ የገዳ ሥርዓት ለበርካታ ምዕተ ዓመታት የኦሮሞ ህዝብ ተወዳጅ ባህል ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰው፤ ቅርሱን ጠብቆ ለማቆየት ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የገዳ ሥርዓት በዩኔስኮ በማይዳሰሱ ቅርሶች መመዝገቡ ለኦሮሞም ሆነ ለሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልፀዋል፡፡ ሥርዓቱ በአስተዳደር፣ በልማት፣ በዴሞክራሲ በሰላም ጉዳዮች ላይ ያለው አወንታዊ አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

የገዳ ሥርዓትን በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር የተለያዩ ተግባራትን ማከናወኑ ይታወሳል።

ገዳ የኦሮሞ ሕዝብ ለበርካታ ዘመናት ሲጠቀምበት የነበረ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ ሥርዓት ሲሆን የዴሞክራሲ ሥርዓት ከመጀመሩ አስቀድሞ በየስምንት ዓመቱ የስልጣን ሽግግር የሚከናወንበት አገር በቀል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው።

በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ እስካሁን 336 ዓለም አቀፍ ቅርሶች መመዝገባቸው ይታወቃል።

 

ደረጀ ትዕዛዙ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829524
TodayToday1154
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7244
This_MonthThis_Month29704
All_DaysAll_Days2829524

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።