About Us

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

 

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተቋቋመበትን ቀንና ዓመተ ምህረት የሚገልጽ መረጃ አልተገኘም። ነገር ግን ድርጅቱን የሚመራና የሚያስተዳድር ዋና ሥራ አስኪያጅ መሾሙን የሚገልጸው የነጋሪት ጋዜጣ ከወጣበት ከ1962 .ም ጀምሮ እንደ ድርጅት መቋቋሙን በርካቶች ተቀብለውታል።

ድርጅቱ ከተቋቋመበት ከ1962 .ም ጀምሮ እስከ አሁን የተለያዩ አደረጃጀቶችና አወቃቀሮችን አሳልፏል። በ1969 የማስታወቂያና የማከፋፈያ ተግባራት ለሌላ መምሪያ ተሰጥተው «የኢትዮጵያ ፕሬስ መምሪያ» በሚል መጠሪያ በመምሪያ ደረጃ ለማስታወቂያ ሚኒስቴር ተጠሪ ሆኖ ተደራጀ። በድርጅት ደረጃ እስከ ተዋቀረበት 1987 .ም ድረስ የህትመት ውጤቶችን በማዘጋጀት ማለትም በኤዲቶሪያል ሥራው ብቻ ተወስኖ ቀርቷል። የማስታወቂያና የሥርጭት ሥራዎች በሌላ መምሪያ እየተከናወነ በጐንዮሽ ግንኙነት የኤዲቶሪያል ሥራው በአንድ በኩል የአድቨርቶሪያልና የስርጭት ሥራ በሌላ በኩል ሲከናወን ቆይቷል።

በዚህ ወቅት የግዥ፣ የሰው ኃይል የበጀት ወዘተ. ሥራዎች የሚከናወኑት በማስታወቂያ ሚኒስቴር ስለነበር አደረጃጀቱ ደረጃውን ዝቅ ከማድረጉም በላይ አንድ የህትመት ሚዲያ ተቋም ሊይዝ ይገባው የነበረውን አደረጃጀት ካለመያዙም ባሻገር ስራውን በተቀላጠፈ አግባብ ከመነሻ እስከ መድረሻ ለማከናወን ሲቸገር ቆይቷል። በመሆኑም የማስታወቂያና የሥርጭት ሥራው ተገንጥሎ አስፈላጊ ግብአቶች በሌላ አካል እየቀረ በለት ውስብስብ በሆነ ችግር ውስጥ እስከ 1987 አጋማሽ ዘልቋል።

1987 .ም የፀደቀው የኢፌዲሪ ዲሞክራሲያዊ ሕገመንግሥት በስራ ላይ መዋል ለመረጃ ነፃነት ትግበራው አዲስ መንገድ ከመክፈቱ ባሻገር ድርጅቱ ያሉበትን ችግሮች በመገንዘብ አዲስ አደረጃጀት እንዲፈጠር በር ከፍቷል። በዚሁ መሠረት በመንግሥት ባለቤትነት ስር ያሉ የመገናኛ ብዙሃን በኅብረተሰቡ መካከል ሃሳቦችና አመለካከቶች መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ እንዲሁም የተቋምና የአሠራር ነፃነት እንዲኖራቸው ለማድረግ አዋጅ ቁጥር 113/1987 ተደነገገ። በኋላ ይህንኑ አዋጅ በማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 75/1989 ላይም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአዲስ መልክ ተቋቋመ።

የድርጅቱ አወቃቀር ሥራ አመራር ቦርድ፣ ዋና ሥራ አስኪያጅና አስፈላጊ የሆኑ ሠራተኞች ሲኖሩት የቦርዱ ተጠሪነት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ይህ አዋጅ በወቅቱ በርካታ ለውጦች አምጥቷል። እስከ አሁንም አሥራ ስምንት ዓመት በሥራ ላይ ውሏል። ከአሥራ ስምንት ዓመት በኋላ አገራችን እየተገበረችው ካለው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አንፃር እንዲሁም ሁሉን አቀፍ በሆነው የህዳሴ ጉዞ የሚታየው ፈጣን ዕድገት የህትመት ሚዲያው ዘርፍ የሚመጥን ሆኖ አልተገኘም። ስለሆነም አዋጁም ሆነ የህትመት ሚዲያው አደረጃጀትና አሠራር እንደገና መቃኘት ያለበት መሆኑ ታምኖበታል።

በተጨማሪም በድርጅቱ ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 6 እና 11 ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ የህትመት አገልግሎቶችን ማቋቋም እንደሚችል እና የፕሬስ አገልግሎት ስለሚስፋፋበትና በተስማሚ ቴክኒዮሎጂ የሚደራጅበትን ሁኔታ በማጥናት ሃሳብ አቅርቦ እንደሚያስፈቅድ በግልጽ የተደነገገ በመሆኑ ይህንኑ መነሻ በማድረግ ኮርፖሬት የህትመት ሚዲያ አዋጭነት ጥናት ለማካሄድ ጥረት ተደርጓል።

በአዋጁ ላይ በሚታዩ ክፍተቶች ምክንያት የድርጅቱ ሠራተኞች በሁለት የአስተዳደር መመሪያዎች መመራታቸው በሥራ ላይ ያሳደረው ተፅእኖ፣ የበጀት አጠቃቀም በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ፈቃድ ሥር መሆኑ ገቢን ለማዳበር የሚታይበት እጥረት እና የተገኘውን ገቢ በአስፈላጊ የሥራ መሣሪያዎች ላይ ለማዋል አለመቻሉ በሕግ ማዕቀፉ የሚታዩ ችግሮች ሲሆኑ ድርጅቱ ለህትመት የሚያወጣው ወጪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ መምጣቱ ተከትሎ ከፍተኛውን የገቢ ድርሻ ለማሳተሚያ እንዲያውል አስገድዷል። ጋዜጦች ሰዓትን ጠብቀው አለመታተማቸው፣ የህትመቶቹ ጥራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ መምጣቱ ክህሎታቸው፣ እያደገ የመጡ በሳል ሙያተኞች ከስራ መልቀቃቸውና፣ የተሻለ ዕውቀት ያላቸውን ጋዜጠኞች ለመቅጠር አበረታች ስርዓት አለመዘርጋቱ እና ሌሎችም ተያያዥ ችግሮችም ለኮርፖሬት ህትመት ሚዲያ አወጪነት ጥናት መነሻ ሆነው ተገኝተዋል።

 

. ዋና ዓላማ

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ዓላማ በመተግበር ላይ ያለውን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት አገሪቱ በያዘችው የህዳሴ ጉዞ የሚመጥን ጠንካራ የህዝብ የህትመት ሚዲያ ተቋም፣ ለመፍጠር ነው።

. ዝርዝር ዓላማዎች

ዘመኑ የደረሰበትን የህትመት ቴክኒዮሎጂ በመጠቀም በሙያው የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት የህትመት ውጤቶችን ጥራት፣ ተነባቢነትና ተደራሽነት በማሻሻል ቫይብራንት (Vibrant) የህዝብ ሚዲያ ተቋም ለማቋቋም፤

በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚፈጸሙ አበይትና ወቅታዊ ጉዳዮችን፣ ትምህርታዊና አዝናኝ ዝግጅቶችን በመቀመር የህዝቡን የመረጃ ጥማት ለማርካት እና መሪ የህትመት ሚዲያ ሆኖ ለመገኘት፤

ከማስታወቂያ አገልግሎት እና ከህትመት ውጤቶች ጋር የተያያዙ የተለያዩ የገቢ ምንጮችን በማፈላለግ አዳዲስ የህትመት ሥራዎችን በማከናወን አስተማማኝ የገቢ አቅም ለመፍጠር፤

በህትመት ሚዲያ ዘርፍ የሚታየውን ውስንነትና የአቅጣጫ ክፍተት ለመፍታት የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ማከናወን የሚያስችል የስልጠና ማዕከላትን ማቋቋም ናቸው፤

 

መረጃ የማግኘት መብት መከበሩ

መረጃ ለግለሰብ፣ ለቤተሰብ፣ ለአካባቢ በየደረጃው ለሚገኘው የስልጣን እርከን፣ ለአገር ፣ ለአህጉርና ለዓለም ወሳኝ ግብአት ከሆነ ዘመናት ተቆጥረዋል። ሰው ያለመረጃ፤ ዓለም በመረጃ አልቦ ይኖራሉ ተብሎ አይታሰብም። በተለይ ዘመኑ የመረጃ ነው በሚባልበት በአሁኑ ወቅት የአየርና የምግብ ያህል አስፈላጊነቱ እየተነገረ መሆኑን በየአጋጣሚው ሁሉ የምንታዘበው ጉዳይ ሆኗል።

ይህን መረጃ በመቀበልና መልሶ በመስጠት ረገድ ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን ከፍተኛውን ድርሻ ለመውሰድ ባህሪያቸው ይፈቅድላቸዋል። ፋብሪካዎች ግብአቶቻቸውን ተጠቅመው ምርት ሲያቀርቡ መገናኛ ብዙሃን ደግሞ መረጃን አድቅቀው ሰልቀው መዝነው ለአንባብያን ለአድማጮችና ለተመልካቾች ያቀርባሉ። መገናኛ ብዙሃን ያለመረጃ ሕይወት አልባ ናቸው የሚባለውም ከዚህ ዕውነታ በመነሳት ነው።

በመገናኛ ብዙሃንና መረጃ ተዋህደው በተለይ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ በልማትና የኅብረተሰብ ሽግግር (Transformation) ውስጥ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው። simon and pichard (2009) “Open Government” በሚለው መጽሐፋቸው እንደሚያስረዱት በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውስጥ ግልፅነትና ተጠያቂነት ዋነኛዎቹ መሰሶዎች ናቸው። እነዚህን መሠረቶች ለማቆም ወሳኙ ጉዳይ የመረጃ ነፃነት ተግባራዊ ሲሆን ይህም በሚዲያ መስፋፋትና መጠናከር ይበልጥ እውን እንደሚሆን ነው የገለጹት።

ሕዝቡም መገናኛ ብዙኃንን የሚጠቀመው የዓይኑ ማረፊያ እንዳያጣ፣ ቤቱ እንዳይቀዘቅዝ እንደዚሁም ጋዜጦችን ለእቃ መጠቅለያነትና ለግድግዳ መሸፈኛነት ለመጠቀም ሳይሆን መረጃ ለመከታተል ብቻ እንደሆነ ይታመናል። በሰለጠነው ዓለም አይደለም የመንግሥትና የሕዝብ መረጃ ቀርቶ ምን እንደሚለበስ፣ የአመጋገብ ሁኔታና መሠል ጉዳዮችን አስመልክቶ መረጃ የሚገኘው ከመገናኛ ብዙሃን ነው።

በሌላ በኩል መገናኛ ብዙሃን ተገቢውን ትክክለኛውንና ወቅታዊውን መረጃ ለተከታዮቻቸው ለመስጠት እንቅፋት የሆኑባቸው ጉዳዮች አሉ። አንደኛው መረጃ የማግኘት መብትን በማፈን መገናኛ ህዝቡ የሚፈልገውን መረጃ ሳይሆን ራሳቸው ያሰቡትን ብቻ ለክተው በመስጠት እንዲተላለፍ የሚፈልጉ መንግሥታት ይጠቀሳሉ።

እ ኤ አ በ2012 በወጣው መረጃ መሠረት በአፍሪካ ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ 8 አገሮች መረጃ የማግኘት መብትን ሲያከብሩ የተቀሩት ይህን መብት ጨፍልቀው እየተጓዙ ይገኛሉ። በዓለማችን በአጠቃላይ 93 አገሮች ድንጋጌውን ተቀብለውት እየሠሩ ናቸው።

በኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ መረጃ የማግኘት መብት በሕገመንግሥቱ ተከብሯል። አን 293ኸለ

 

«የሕዝብን ጥቅም የሚመለከት መረጃ የማግኘት ዕድል»

 

ተገቢውን መረጃ ከተገቢው ቦታ በማግኘት፣ በተቋም ደረጃም ለአጠቃላይ ሕዝብ መጠቀም እንደሚቻል በግልፅ ሠፍሯል። ከዚህ በተጨማሪም በኢፌዴሪ በመንግሥት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ስትራቴጂ ተከታዩ ሀሳብ ሰፍሯል።

 

«ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ ያለው ዜጋ የዴሞክራሲ ትልቅ

እሴት ነውና ሚዲያ እንደዚህ አይነት ዜጋ እንዲኖር በማድረግ

ረገድ የላቀ ሚና መጫወት ይገባዋል።»

 

ከዚህ የመንግሥት አቋም የምንረዳው መረጃ ለሀገር ዕድገት ቁልፍ ሚና የሚጫወት ለተግባራዊነቱ የሚሠራ መሆኑን ነው። የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000 ፀድቆ ተግባራዊ መደረጉም ለዘርፉ አመቺ ሁኔታን ፈጥሯል።

ይህ ምቹ ዕድል በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዓይነት ራዕይ ላላቸው የሚዲያ ተቋማት መጠናከር ጉልበት ይሆናል። በየደረጃው ካሉት የመንግሥት አካላት ተገቢውን መረጃ በመውሰድ የመጠቀም መብቱ በዋናነት ለመገናኛ ብዙሃን የተተወ ነው። በመሆኑም በመረጃ የበለፀገ መገናኛ ብዙኅን መረጃ የታጠቀ ሕዝብ ለመፍጠር የሚያግዝ በመሆኑ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ምቹና ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር መረጃን አሟጥጦ በመጠቀም ሕዝብንና መንግሥት ተጠቃሚ የሚያደርግ፤ ልማትን የሚያፋጥንና ድህነትን ታሪክ የሚያደርግ ተግባር ለማከናወን አጋዥ ሀይል ሆኖ እንዲሰለፍ የሚያስችለው ሌላው ምቹ ዕድል ተደርጐ ይወሰዳል።

 

ተቋሙ ለሕዝብ ተጠሪ መሆን

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አሁን ባለው ሁኔታ ተጠሪነቱ ለአስፈፃሚው አካል አይደለም። በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ይህ ደግሞ መንግሥት ሳይሆን ሕዝብ የሚቆጣጠረው መሆኑን ያሳያል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአባላቱና ከተለያዩ ተቋማት በሥራ አመራር ቦርድ ውስጥ የሚወክላቸው ዜጎች ድርጅቱን በበላይነት ይከታተላሉ።

ድርጅቱ አደረጃጀቱንና አሠራሩን ለመቀየር በጥናት ላይ ተመስርቶ እንዲሟላለት የሚፈልገውን ነገር በመጠየቅ የሚያስፈቅደው የሥራ አመራር ቦርዱን ነው። ቦርዱ እስከአሁን ባለው አሠራር ድርጅቱ ለሥራው የሚመቸውን አቅዶ ሲጠይቅ የሚፈፅም ከመሆኑም ባሻገር በተለይ የለውጥ ሚዲያ እንዲሆን ሳቢና ተነባቢ የሕትመት ውጤቶች ባለቤት በመሆን ተልዕኮውን በአጥጋቢ ሁኔታ እንዲፈፅም በየአጋጣሚው ሁሉ የላቀ ፍላጐቱን የሚያንፀባርቅና የሚተጋ ነው።

በእስከአሁኑ ሂደትም ቦርዱ ድርጅቱን ወደፊት አንድ እርምጃ ያስጓዘ ተግባርም ለማከናወን የተቻለበት ክስተት ታይቷል። ለ70 ዓመታት የራሱ ሕንፃ ሳይኖረው የቆየ፣ በየጊዜው ዕቃውን እየሸከፈ ከቦታ ቦታ ሲንከራተት የኖረው ይህ ተቋም የራሱ ሕንፃ እንዲኖረው የተደረገው ጥረት ተሳክቷል። እነሆ ባለ 6 ፎቅ ሕንፃ ተገንብቷል። ተቋሙ ሥራውን ይበልጥ ለማሳካት ያግዘኛል ብሎ ያዘጋጀውን አዲስ የሠራተኞች የደመወዝ ማሻሻያ በማፅደቅ ወደተግባር ተሸጋግሯል።

ከዚህ በተጨማሪ ቦርዱ የድርጅቱን የሕትመት ውጤቶች ለማሻሻል የሚረዱ አሠራሮችን ለመቀመር ከድርጅቱ አመራር ጋር በመሆን በውጭ የሚገኙ ተመሣሣይ ተቋማትን አሠራር ጐብኝቶ በመመለስ ልምዳቸው እንዲቀመር አድርጓል። የአዲስ ዘመን ጋዜጣና የኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ የስታንደርድ ቅርፅ እንዲኖረው፣ በከፊል የቀለም ሕትመት እንዲዘጋጁ የቀረበለትን ሃሳብ በማፅደቅ አጋዥነቱን አሳይቷል።

ቦርዱ አሁንም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ተልዕኮውን በትጋት እንዲፈፅፍም ሳይፈራ ሳይሸማቀቅ ወደ አንድ ወገን ሳያደላ በነፃነት በመሥራት ጥራት ያላቸውን የሕትመት ውጤቶችን በሠፊው በማዳረስ ዓላማውን በብቃት የሚወጣ ተጠቃሽ የሕትመት ሚዲያ እንዲሆን ከልብ የመነጨ ፍላጎቱን እየገለጸ፤እየወተወተ ይገኛል።

ስለዚህ ተቋሙ ወደኮርፖሬት የሕትመት ሚዲያ ተሸጋግሮ ችግሩን ራሱ እየፈታ ፣ ሀብት እያመነጨ በዋናነት ሕዝብ የሚወዳቸውን ሰውን የሚያረኩ የሕትመት ውጤቶችን እያዘጋጀ ውጤታማ ተቋም እንዲሆን ሀሳቡን ከማመንጨት ጀምሮ ግፊት የሚያደርግ ሥራ አመራር ቦርድ ያለው በመሆኑ አደረጃጀቱን ለመቀየር ሌላው በጥሩ መደላድልነት የሚጠቀስ ምቹ ሁኔታ ሆኗል።

በድርጅቱ የሚታተሙ ጋዜጦች ዕለታዊ መሆን

በየዕለቱ የሚወጡ ጋዜጦች ወቅታዊ መረጃዎችን ከኤሌክትሮኒክ ሚዲያው በተለየ መልኩ በጥልቀት በመተንተን ስለሚዘጋጁ ለተደራሹ ቅርብ ናቸው።ደጋግሞ ለመመልከት መረጃውን በራስ ማህደር ለማኖር ይመረጣሉ። የሕትመት ውጤቶቹ በጥራት ከተዘጋጁ በየዕለቱ እየተናፈቁ አንባቢያን እጅ የሚገቡበት ዕድል ሠፊ ይሆናል። ይህ ደግሞ በገቢያቸው ለመተዳደር የሚያደርጉትን ጥረት ያሳካዋል። የጋዜጦች ቁጥር ከሀገሪቱ ዕድገት ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ሁኔታ ፍላጎቱ ስለሚጨምር ያንን ጥያቄ በማስተናገድ ደንበኛን ማርካት ይቻላል።

የኢትዮጵያን ሀሳብ፣ አቋም ለማወቅ በአንድ ወይም በሌላ አጋጣሚ የሚያሰፈስፉትን ሀይሎች አመለካከት ለመቀየር በተከታታይ በመዘገብ ያልተሰሙ፣ ያላወቋቸውን እንዲገነዘቡ በማድረግ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያደርጉ ጫና ለማሳረፍ ዕለታዊዎቹ ጋዜጦች የማይተካ ሚና አላቸው።

ከዚህ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ምንጭ በማድረግ፣ በአካባቢው፣ በአህጉሪቱ ዙሪያ ልዩ ዘገባዎችን በማዘጋጀት ለማሰራጨት በየዕለቱ የሚወጡ ጋዜጦች የተሻለ ዕድል አላቸው።

መረጃን በወቅቱ በጥልቀትና በጥራት በማስተላለፍ፣ ገቢ በማሳደግ፣ የአንባቢና የደንበኛን እርካታ ለመጨመር ዕለታዊ ጋዜጦች ሌላ ምቹ ሁኔታ ሆነው ይጠቀሳሉ። በዚህ ረገድ የድርጅቱ የህትመት ውጤቶች የስርጭት አድማስና ተፈላጊነት ገና ማደግ ቢኖርበትም ዕለታዊ መሆናቸው ለሽግግሩ አንድ አመቺ መነሻ ይሆናል።

 

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አሁን የደረሰበት ተቋማዊ ገፅታ

 

የተቋሙ አመሠራረትና ጉዞው

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ብቸኛ የመንግሥት የኅትመት ሚዲያ ተቋም ነው። የድርጅቱ ታሪካዊ አመጣጥ በኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ አጀማመርና የሕትመት ቴክኖሎጂ ወደ አገሪቱ መግባት ጋር በእጅጉ ይያያዛል።

ኢትዮጵያ የራሷ ቋንቋና ሆሄያት ያላት ብቸኛ አፍሪካዊት አገር ናት። ለሕትመት ዘርፍ መሠረት የጣሉ የበርካታ እሴቶች ባለቤት ነች። በብራና የተፃፉ መፃሕፍትን ጨምሮ በእጅ እየተፃፈ በየሳምንቱ በአራት ገፅ ይወጣ የነበረው የአዕምሮ ጋዜጣ ለአሁኑ የሕትመት ሚዲያ ዘርፍ አሻራቸውን ጥለዋል።

ጋዜጣና መጽሔቶችን መጽሐፍትንና ሌሎች ዕትሞችን በእጅ ፅፎ ማሰራጨት እጅግ ከባድ ሥራ በመሆኑ ሥራውን የሚያቀል የሕትመት መሣሪያዎች ወደ አገራችን መግባት ግድ ሆኖ መገኘቱ በተለያየ ጊዜ በተለያየ የአገራችን ክፍል ቀላል የማተሚያ ማሽኖች መግባታቸው በእጅ ይፃፈ የነበረውን በእጅ የሕትመት መሣሪያ እንዲከናወን መደረጉ ለአገራችን የሕትመት ሚዲያ ከፍተኛ አስተዋፅዎ አበርክቷል።

በአንዳንድ ጥናቶች ተመዝግበው የሚገኙት የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱት በ1857 የእጅ ሕትመት መማሪያ መግባቱን በ1859 የመጀመሪያው የፕሪንት ሚዲያ በሀገራችን መጀመሩን በ1874 ኩሪያለ አፈትሪ የተሰኘ መጽሔት ለመጀመሪያ ጊዜ በኢጣሊያ ቋንቋ መታተሙን የዘገቡ ሲሆን በ1893 አባማሪ በርናርድ በተባሉ ሚሲዮናዊ ላ ሲሜዩኒ ዲ ኢትዮጵ የተባለ ሣምንታዊ ጋዜጣ በአማርኛና በፈረንሳይኛ ሐረር ውስጥ ሲያሳትሙ እንደነበር ተጠቅሷል።

«የዜና ማሰራጫ ዘዴ በኢትዮጵያ» በሚል ርዕስ በ1959 በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥነ-ጽሑፍ ማዘጋጃና በውጭ ቋንቋ በሚታተሙ ጋዜጦችና መጽሔቶች ክፍል የተዘጋጀ ጥናታዊ ጽሑፍ እንደሚያስረዳው አባ በርናርድ «ላ ሰሜዮኒ ዲ ኢትዮጲ» የተባለውን ጋዜጣ በሐረር ማሳተም ከጀመሩ ከሁለት ዓመት በኋላ እንድሪአስ ኤ ካቫዲ የተባለ የግሪክ ነጋዴ የመጀመሪያውን የአማርኛ ቋንቋ ጋዜጣ ማሳተም መጀመራቸው ተዘግቧል።

ይህ ጋዜጣ አዕምሮ የሚል መጠሪያ የነበረው ሲሆን በህትመት መሣሪያ በመታተሙ ቅጅው በየሳምንቱ ወደ ሁለት መቶ ከፍ ብሏል። የአገራችን የሕትመት ሚዲያ በዚህ መንገድ እያደገ መጥቶ «ኢትዮጲ ኮሜርሲያል»«ከሰቴ ብርሃን» «አጥበያ ኮኮብ» የተባሉ ሳምንታዊ ጋዜጦች እስከጣሊያን መረራ ሲታተሙ ቆይተዋል።

ከወረራው በኋላ የሕትመት ሚዲያው በመድከሙ ከባንዲራችን ጋዜጣ በስተቀር የቀሪዎቹ ሕትመት ቆሟል። ከድል በኋላ የሕትመት ሚዲያው እንደገና በማንሰራራት በትግርኛና በአረብኛ፣ በጣሊያንኛ፣ በአርብኛና በፈረንሳይኛ፣ በአማርኛ፣ በትግርኛና በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በአማርኛ የሚታተሙ በርካታ ጋዜጦች ከ1934 በኋላ ታትመዋል።

የሕትመቶቹ ባለቤት ጽሕፈት ሚኒስቴር፣ ማስታወቂያ ሚኒስቴር እና የአገር ፍቅር ማህበር ነበሩ። እነኝህን ህትመቶች አሰባስቦ እንዲያስተዳድር የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በ1962 .ም ተቋቋመ።

በውል ባልታወቀ ጊዜ (አንዳንዶች 1956 ይሉታል) ድርጅቱ በማስታወቂያና መርሐ ብሔር ሥር ሆኖ በመምሪያ ደረጃ ጋዜጦችና መጽሔቶችን ሲያስተዳድር ተጨማሪ ህትመቶችን ሲያዘጋጅና ሲያሳትም ቆይቶ በ1987 .ም በአዋጅ ቁጥር 113/1987 ሕጋዊ ሰውነት ያለው የሕትመት ሚዲያ ተቋም ሆኖ በመቋቋሙ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል።

የድርጅቱ ዋነኛ ዓላማ መንግሥት የሚያወጣቸውን አዋጆች ፖሊሲዎች እንዲሁም የሚፈጽማቸውን ተግባራት የማብራራት፣ ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎችና ፍትሃዊ ጥያቄዎች የማስተጋባት በሕዝብና መንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት የማጠናከርና ሕዝብን በማገልገል፣ የፖለቲካ ኃይሎች ፍትሐዊ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው።

 

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ህትመት ውጤቶች

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአሁኑ ወቅት በአራት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ እንግሊዘኛ፣ ኦሮሚኛና አረቢኛ ) አራት ጋዜጦችን-ሁለት ዕለታዊ (Broad sheet) እና ሁለት ሳምንታዊ ጋዜጦች (Tabloid) እንዲሁም አንድ መጽሔትን እያዘጋጀ ያሰራጫል። ወጥነት ባለው መንገድ ባይሆንም በህትመት ጋዜጠኝነትና አጠቃላይ አሰራሩ ላይ የሚያተኩሩ ጥናቶችን እያስጠና በ«ሕትመት ሚዲያ ጆርናል» ለህትመት እንዲበቁ ያደርጋል። ቋሚ ባይሆኑም መጽሔቶችና ዓመታዊ መጽሐፎችም በተቋም ደረጃ ይወጣሉ። ዋነኛ የህትመት ውጤቶቹ የሚባሉትን ወደመመልከት እናምራ።

 

የአዲስ ዘመን ጋዜጣ

የኢጣሊያ ፋሽስት ወረራ ጦር በአፄ ምኒልክ የጦር ሠራዊትና ለነፃነት ቀናኢ በሆኑት የኢትዮጵያ ጀግኖች በ1888 .ም በአድዋ ጦርነት የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል የሞሶሎኒ ጦር በ1928 .ም ዳግም ኢትዮጵያን ወረረ። ከ1928-1933 የኢትዮጵያ አርበኞች በዱር በገደሉ ተሰድደው ወራሪውን ጦር መፈናፈኛ እንዳያገኝ ካደረጉት በኋላ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት መገባደዱን ተከትሎ በእናትና አባት አርበኞች ተጋድሎ በመጨረሻም በእንግሊዝ የጦር ኃይል ስትራቴጂያዊ ድጋፍ ኢትዮጵያ ሙሉ ነፃነቷን ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ማረጋገጥ ችላለች።

በወረራው ምክንያት ስደትን የመረጡት የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ነፃነት መመለሱን ተከትሎ ዙፋናቸው እንደተረከቡ ካከናወኗቸው ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ተግባራት አንዱ መገናኛ ብዙኃን በማደራጀትና በማቋቋም ላይ ያተኮረ ነበር። በዚህም መሠረት ግንቦት 30 ቀን 1933 .ም አዲስ ዘመን በሚለው መጠሪያ የሚታወቀውን ብሔራዊ ጋዜጣ በይፋ ሥራ አስጀምረዋል። የጋዜጣው ስያሜ ንጉሡ አዲስ አበባ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 .ም በድል አድራጊነት ሲገቡ ይህ የአዲስቷ ኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን መጀመሪያ ነው' ማለታቸውን መሠረት ያደርጋል።

ጋዜጣው ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 1933 ባለሁለት ገጽ የመጀመሪያ ዕትም ለንባብ ማብቃቱን መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን የሥርጭቱ መጠን 10ሺ ቅጂ የጋዜጣው መጠንም አርበ ጠባብ /ታብሎይድ/ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። እስከ ሰኔ 30 ቀን 1937 .ም ድረስ በታብሎይድነቱ የቀጠለ ሲሆን በመካከሉ አርበ ሰፊ (Brood sheet) እስከሆነበት1940ዎቹ ድረስ በበርሊነየር / መካከለኛ መጠን/ በአራትና ስድስት ገፆች ሲታተም ቆይቷል።

ጋዜጣው በመጀመሪያው እትም ርዕስ አንቀጹ ' የአዲስ ዘመን ጋዜጣ መጀመር' በሚል ርዕስ ባስነበበው ጽሑፍ ' ይህ አዲስ ዘመን ተብሎ የተሰየመው ጋዜጣ ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የነፃነቱን ሥራ ይሠራ ዘንድ ተመሠረተ' በማለት የተቋቋመበትን ዓላማ ያስረዳል። ርዕስ አንቀጹ በመቀጠልም ' ይህ ጋዜጣ የፕሮፓጋንዳ ጋዜጣ ሳይሆን እውነትን አገልግሎትን ረዳትነትን መሠረት አድርጐ ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ በአዲስ ስራ ተመርቶ እንዲረዳ የቆመ ነው' ቢልም ' አገልግሎት ስንል የኢትዮጵያን ነፃነት ሲመለስ ራሳቸውን መስዋዕት አድርገው የነበራቸውን ጥቅም ሁሉ አስወግደው ለሕዝባቸውና ለአገራቸው ሲሉ የሰው አቅም ሊሸከመው የማይችለውን ድካም ተቀብለው ማናቸውም ሰው ሊያደርገው ያልቻለውን በኢትዮጵያ ሕይወት ውስጥ እስከ ዛሬ ያልታየውን ሥራ ከፍጻሜ ላደረሱ ለንጉሠ ነገሥታችንና ላቆሙት መንግሥት የሚያገለግል እንደሆነ ነው ' በማለትም በዋነኝነት የተቋቋመበትን ዓላማ በግልጽ ይተነትናል።

አዲስ ዘመን ከግንቦት 1933 እስከ ታኅሣሥ 1951 .ም ድረስ በሳምንታዊ መልክ / በአርበ ጠባብ በመካከለኛ በአርበ ሰፊ መጠን/ ሲታተም ከቆየ በኋላ በኢትዮጵያ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን መመሥረቱን ምክንያት በማድረግ በሳምንት ወደ ስድስት ቀን ወደሚታተም ዕለታዊ ጋዜጣነት ሊሸጋገር በቅቷል። ከመስከረም 1 ቀን 1993 .ም ጀምሮ ደግሞ ጋዜጣው ከሰኞ እስከ እሁድ በሳምንት ሰባት ቀናት ወደመታተም ተሸጋግሯል። ከታኅሣሥ 3 ቀን 2004 .ም በኋላም የጋዜጣው መጠን ወደ መካከለኛ ጋዜጣነት / በርሊኒየር/ ዝቅ ያለ ሲሆን / የፊትና ጀርባ ገጾችን በሙሉ ቀለም በማሳተምም ጋዜጣው ከ70 ዓመታት በኋላ መሠረታዊ የአቀራረብ ለውጥ ሊያመጣ በቅቷል። አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከታኅሣሥ 1987 ጀምሮ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሥር የሚታተም በኢትዮጵያ ብቸኛው ዕለታዊ ብሔራዊ ጋዜጣ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ40 በላይ ጋዜጠኞች አሉት።

 

የኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ

በድርጅቱ ከሚታተሙ የኅትመት ውጤቶች አንዱ የሆነው የእንግሊዝኛው «The Ethiopian Herald » ጋዜጣ መታተም የጀመረው በ1940 .ም ገደማ ነው። (ከአዲስ ዘመን 7 ዓመት ዘግይቶ ማለት ነው) በመካከለኛ ቅርጽ አራት ገጾችን ይዞ መውጣት የጀመረው ይህ ጋዜጣ እንደ አዲስ ዘመን ሁሉ የመንግሥት ዋነኛ ልሳን በመሆን አገልግሏል።

ከሦስት ዓመት ጉዞ በኋላ መጠኑ ወደ አርበ ሰፊ (Brood sheet) ከማደጉ ባሻገር ቋሚ አምዶችን በመክፈት ከሰኞ በስተቀር ሳምንቱን ሙሉ መታተም ቀጠለ። ሁለት ገጽ የዜና ገጽ ሁለት ገጽ ዓምድ እየያዘ በመውጣት እስከ 1990ዎቹ መጀመሪያ ድረስ ዘልቋል። ጋዜጣው ከዚያ ወዲህ ተጨማሪ ሁለት ዓምዶችን አከሉ ገጹን ወደ ስድስት ከማድረሱ ባሻገር ማስታወቂያዎችንም በስፋት እየያዘ አሁንም ከሰኞ በስተቀር በመታተም ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ ከአዲስ ዘመን ቀጥሎ በየዕለቱ እየወጣ ያለ የድርጅቱ የኅትመት ውጤት ከመሆኑ ባሻገር በውጭ ቋንቋ የሀገሪቱን ፖሊሲ የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫና የሕዝቡን ፍላጎት ለማንፀባረቅ የሚረዳ ኅትመት ነው። ማኅበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ አዝናኝና አስተማሪ ጽሑፎችን ይዞ በመውጣትም ይታወቃል። ዝግጅት ክፍል በአሁኑ ጊዜ 28 አዘጋጆች ያሉት ሲሆን በቀጣይ በይዘትና ሥርጭት ራሱን ለማሳደግ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።

 

ዘመን መፅሔት

ዘመን መጽሔት የተመሠረተችው በ1993 .ም ሲሆን በወቅቱም ያላት የገጽ ብዛት 36 ነበር። በወቅቱም መጽሔቱ በሦስት የኢዲቶሪያል ቦርድ አባላት የራሱ ሠራተኞች ሳይኖሩት ነበር የተጀመረው። ሥራዎቹም የሚሠሩት በየዝግጅት ክፍሎች ከነበሩ ጋዜጠኞች ነበር። የሽፋን ገጽም ከለር የነበረ ሲሆን ጠንካራ ሽፋን ነበረው። በይዘት ደረጃም የፖለቲካ የማኅበራዊ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚጋለጡባቸው እንዲሁም የኪነጥበብ ጉዳዮችን ዘግቦ ነበር።

ከዚያም በኋላ በዝግጅት ክፍል ደረጃ ተዋቅሮ ይሠራ የነበረ ሲሆን መጽሔቷ አንዴም በየሦስት ወሩ አንዴም በየሁለት ወሩ ትወጣ ነበር። በዋናነትም በፖለቲካ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ሚዛናዊ ዘገባ ለማቅረብ ሙከራዎች እየተደረጉ ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅትም ዋና አዘጋጁን ጨምሮ በዝግጅት ክፍል ደረጃ አራት አዘጋጆችና ከፍተኛ አዘጋጆች ያሉት ሲሆን በ5 የሰው ኃይል ይሠራል። መጽሔቱም በተለያዩ የለውጥ ጉዞዎች ላይ ያለፈች ሲሆን በየወቅቱ የመሻሻል ሁኔታዎች ታይተዋል። የመጽሔቷ የኮፒ መጠንም እንደሚታሰበው ያህል ሥርጭቱ ባይሰፋም በአንባቢያን ዘንድ የተሻለ ተፈላጊነት እንዳላት የሚያመላክቱ ምልክቶች ይታያሉ። ስለሆነም ድርጅቱ ይህችን መጽሔት ይበልጥ አጠናክሮ ለመጓዝ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል።

 

አልአለም ጋዜጣ

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአረቢኛ የሚታተም ብቸኛው መንግሥታዊ ጋዜጣ ሲሆን አዲስ ዘመን መታተም ከጀመረ (1933) ወዲህ ባሉት አራት ዓመታት ውስጥ ሥራ ጀምሯል። ይሄውም ንጉሱ ከእንግሊዝ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በሱዳን በኩል ስለነበር ተከትለዋቸው የመጡ ሱዳናዊ ባለሙያዎች በጋዜጣ ዝግጅቱ ላይ ተሳትፈዋል። በወቅቱ 4 ገፅ ያላት ሳምንታዊ አርበ ጠባብ መጠን (ታብሎይድ) ጋዜጣ ሲሆን 2 ገፅ በአማርኛ2 ገፅ በአረብኛና የሚታተም ነበር። ዋና አዘጋጁም ሊባኖሳዊው ኒማር የሚባል ሰው እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

ጋዜጣው በዚህ ሁኔታ ሥራ ቢጀምርም የንጉሱ ስርዓት ሲወገድ መጠንና ለውጥ አሳይቷል። ይሄውም ከ1968 .ም አጋማሽ አንስቶ የገፅ ብዛቷን 8 ያደረሰች ሲሆን በአረብኛ ቋንቋ ብቻ መውጣት ጀምራለች። ከዚህም በላይ አዘጋጆቹ ግብፅ ሀገር ተምረው የመጡ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ይነገራል። የህትመት ስርጭቷም እስከ 2500 ቅጂ የደረሰ ሲሆን ያኔም ቢሆን ሳምንታዊ ጋዜጣ ነበር።

 

የዓልአለም ጋዜጣ ዛሬ በ7 ቋሚና 1 ጊዜያዊ ሠራተኛ የምትዘጋጅ ሳምንታዊ ጋዜጣ ነች። ዋነኛ የይዘት ትኩረቷም የመካከለኛው ምስራቅና የኢትዮጵያ ማህበረ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ናቸው። እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድና ዓረቡ ዓለም የሚታዩ ዘርፈ ብዙ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ላይ በማተኮር የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ አቋም እንዲንፀባረቅባት ጥረት ይደረጋል። ዋነኛ አንባቢዎችም በኢትዮጵያ የሚገኙ የአረብኛ ተናጋሪ ሀገራት ኢምባሲ ቆንስላዎች (ሠራተኞች)ና አረብኛ ተናጋሪ ዜጐች ናቸው። አሁንም ሳምንታዊ ጋዜጣነቷና አርብ ጠባብ መሆኗ አለመቀየሩ በቀጣይ ታይቶ የስርጭት አድማሱን ጭምር ለማስፋት ጥረት የሚደረግ ይሆናል።

 

በሪሳ ጋዜጣ

የበሪሳ ጋዜጣ በ1968 .ም በአክሲዎን ተደራጅተው በግል ያትሙት ከነበረው ግለሰቦች ተወርሶ በወቅቱ አጠራር በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥር መታተም ሲጀምር በ8 ገጽ 2,500 ቅጂ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። ጋዜጣው በዚህ ወቅት በሳባ ፊደል ይፃፍ እንደነበረና በነጭና ጥቁር ቀለም እንደሚታተም ለማወቅ ተችሏል።

በኋላ እንደሌሎቹ የድርጅቱ የህትመት ውጤቶች ሁሉ ስራው በፕሬስ ድርጅት ስር ሆኖ እስከአሁን የዘለቀ ሲሆን ስርጭቱም በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል ነው።

የጋዜጣው መጠን መጀመሪያ ሲጀመር በርሊነር በሚባለው የጋዜጣ መጠን የሚታተም ሲሆን በኋላ ላይ ከመስከረም 1ቀን 1985 .ም ጀምሮ ታኅሣሥ2ቀን 1985 ብሮድ ሺት ሆኖ ታትሟል።

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ ሎጐው ባለቀለም ሆኖ በታብሎይድ ቅርጽ በቁቤ (ላቲን አልፋቤት) እየተፃፈ በመታተም ላይ ይገኛል።

የህትመት መጠኑም በየጊዜው እየዋዥቀ የመጣ ሲሆን ዝቅተኛው 5,000 ከፍተኛው 16,500 ሆኖ ሲታተም ቆይቷል። ይሁንና ጋዜጣው በክልሉ ካለው ተፈላጊነት አንፃር ገና ብዙ መስራትን የሚጠይቅ ነው።

በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ጋዜጣው በሳምንት አንዴ አርብ አርብ ታትሞ ለአንባቢያን ሲቀርብ መቆየቱም ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሀገራችን ብቸኛና አንጋፋ የህትመት ሚዲያ ተቋም ነው። በታሪክ ሂደት ምንም እንኳን ሦስት የተለያዩ ባሀርያት ያላቸው መንግሥታትን ቢያልፍም ዛሬ የደረሰበት ታሪካዊ አጋጣሚ ደግሞ በለውጥ ጉዞ ላይ እንዲገኝ አድርጐታል። በአንድ በኩል የዜጐች የመናገርና የመጻፍ ነፃነት የተረጋገጠበት፣ ሕገ መንግሥት መጽደቅና ይህንኑ ይበልጥ ዕውን ለማድረግም የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000 ሥራ ላይ መዋል የፈጠረለት ምቹ አጋጣሚ አለ። በሌላ በኩል መንግሥትና የድርጅቱ ማህበረሰብ ለመለወጥ ያላቸው ፍላጐት በቁጥቁጥም ቢሆን በሁሉም መስኮች መሻሻሎች እየታዩ ነው።

 

ሀገሪቱ አሁን በተጨባጭ የደረሰችበት ሁኔታ፣ የዓለም የህትመት ሚዲያው ጉዞና የህዝቡ ንቃተ ህሊና ግን በመለስተኛ ለውጥ ብቻ መቆምን አይፈቅዱም። ይልቁንም እጅግ ፈጣንና ስር ነቀል በሆነ ለውጥ ሸግግር ማምጣትን ግድ የሚልበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ወደ ኮርፖሬሽንነት ከፍ ባለ ተቋማዊ አደረጃጀት አድጐ፣ በይዘት በጥራትም ሆነ ስርጭት ደረጃቸውን የጠበቁ ህትመቶችን ለህዝቡ ለማድረስ እየተዘጋጀ ያለው።

 

ድርጅቱን ወደ ኮርፖሬት የማሳደግ ራዕይ

 

ድርጅቱ ወደ ኮርፖሬትነት መቀየር አለበት። ቢያንስ ለፌዴራል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርና ሲቪል ሰርቪስ ሚኒሰቴር ተጠሪ መሆኑ ቀርቶ በራሱ ገቢና ትርፋማ ስልት እየተመራ ተወዳዳሪ ሚዲያ መሆን ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ አደረጃጀት፣ አሰራር፣ አመራርናብአቱን ይበልጥ አሟልቶና አቀናጅቶ፣ የኮርፖሬት ማቋቋሚያ ደንቡን አፅድቆ ስራ እንዲጀምር መደረግ አለበት። በስጋቱም ላይ እንደተገለጸው የማተሚያ ቤትና ገቢ ማግኛ ተዛማጅ ዘርፎችም በስትራቴጂክ ዕቅድ ተነድፈው በአጭር ጊዜ እንዲሟሉ (ከፕራይቬታይዜሸን ጋር በሸርክና ሊፈፀምም ይችላል) ጥረትደረግ አለበት። የኮርፖሬቱንውን መሆን ተከትሎም ከዚህ በታች የተጠቀሱ ተግባራት ይበልጥ ሰፍተውና ተጠናክረው ይተገበራሉ።

 

በመረጃ የዳበረ ሕብረሰበብ መፍጠር

ከሚዲያ ሙሉ ለሙሉ መረጃ የሚወስድና የሚጠቀም አንባቢን ማፍራት ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር ነው። በውጭ ሀገር በተለይ እንደ ቻይናና ደቡብ ኮሪያ ባሉት ሀገሮች የሚገኙ ሕዝቦች በመገናኛ ብዙኃን ተጠቃሚ ሆነዋል። እነዚህ ሀገሮች በአጭር ጊዜ ልማታቸው ምን ያህል እንደተፋጠነ ይታወቃል። በአንፃሩ ወደኛ ሀገር ስንመጣ 70 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ መረጃን ከጓደኞችና ከሌሎች ያልተረጋገጡ ምንጮች የሚጠቀም እንደሆነ ይነገራል። ይህ የጋራ መግባባት ለመፍጠርና በልማቱ ዕኩል ከመሳተፍና ከመጠቀም አንጻር ተፅዕኖ የሚፈጥር ሰለሆነ በዚህ ረገድ ተመራጭ የመረጃ ምንጭ ለመሆን ኮርፖሬቱ ይሰራል። በጥናት ላይ የተመሰረተ የተነባባሪነት አቅጣጫ ግልፅ አጀንዳ ቀረፃና አሳታፊ አቅጣጫን በመከተል ለውጡን መጀመርም ይቻላል።

 

የለውጥ ሚዲያ (vibrant media) ሆኖ ማገለገል

የልማት ጋዜጠኝነት መርህ በብቃት በመተግበር ኢትዮጵያን ከተመፅዋችነት ለማዳን ይሰራል። የተሳኩ የልማት ተሞክሮዎችን በተጨባጭ ሳቢ በሆነ አቀራረብ በመዘገብ ምርጥ ምርጥ ፎቶግራፎች በመጠቀም፣ በአጀንዳ የሚመሩ ዘገባዎች በማሳተም እንደዚሁም በሚፈለገው መልኩ የማይንቀሳቀሱ የልማት ተግባራትን ነቅሶ በማውጣት ለውጥ እንዲደረግባቸው በማሳየት አጋዥ ሆኖ መሥራት አለበት። የሕትመት ውጤቶች የተለያዩ ሃሳቦች በነፃነት የሚንሸራሸርባቸው የሕዝቡን አስተሳሰብ የሚቀርጹ ጉዳዮች ከተሟላ መረጃ ጋር የሚቀርቡባቸው ይሆናሉ። ሚዛናዊና የሁሉንም ወገኖች ድምፅ (ሀሳብ) የማስተናገድ ጉዳይም ትኩረት ይሰጠዋል።

 

የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን መዋጋት

ከኪራይ ሰብሳቢነት፣ ግብር ማጭበርበር፣ አለአግባብ ለመክበር መሯሯጥ፣ ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል አስተሳሰብን ሳይሰሩ መብላት፣ ግለኝነትን፣ ምንቸገረኝነትን፣ የመንግሥት ሀብትን ማባከን፣ የሕዘብ ጥቅም መደፍጠጥን፣ ያለውጤት ስልጣን መቆየትን፣ ስግብግብነትን፣ አድርባይነትን፣ ብልሹ አሠራርን፣ ሀገሬ ምን ሠራችልኝ አስተሳሰብን፣ በድሮ ታሪክ መኮፈስን፣ አሉባልታ፣ ጐጂ የሥራ ባህል፣ ጦርነት ናፋቂነትን፣ እብሪተኝነትን፣ የሃይማኖት ጽንፈኝነትን፣ ጐሠኝነትን፣ ትምክህትን፣ ጠባብነትን፣ ከሀገር ማስኮብለልን፣ በፖለቲካ ሳቢያ ማጭበበርን፣ ትንኮሳን፣ የሀገሪቱን የዕድገት ተጨባጭ ለውጥ አለመቀበልን፣ በሀገር ሉዓላዊነትና የዕድገት እቅዶች ውጥኖችን ለመድፈቅ የሚሠነዘሩ ተግባራትን ለማስወገድ ተከታታይ ሥራ ያከናውናል።

 

የዲሞክራሲ ስርዓትን ማጐልበት

በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚዲያ ሚና በእጅጉ ወሳኝ ነው። ከዚህ አንፃር ኮርፖቱ ለሀገሪቱ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አጋዥ ኃይል ሆኖ በግንባር ቀደምነት ይሰራል።

«ፕሬስ ለመሠረታዊ ነፃነት፣ ሠላም፣ ለዴሞክራሲ፣ ለፍትህ ለእኩልነት፣ ለማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መፋጠን የቆመ ነው። /የፕሬስ ነፃነት አዋጅ 3211 85 አንቀጽ 4/ ከዚህ አንፃር በሀገሪቱ የተለየ ታሪክ የተመዘገበበትን የሕዝቡን ዴሞክራሲያዊ መብት ያረጋገጠውን ሕገ መንግሥት ተግባራዊነት በመከታተል፣ ስለ ሕገ መንግሥቱ የበላይነት ሰለ ነፃ ምርጫ፣ ስለ ዜጐች መብት፣ ሰለ እኩልነት፣ ስለ ነፃ አስተሳሰብ፣ ፓርቲዎች እንዲጠናከሩ በኃላፊነት ስሜት እንዲንቀሳቀሱ የመናገር፣ የመፃፍ መብትን የተመለከቱ ጉዳዮችን ወዘተ. በጥልቀትና በተከታታይ በመዘገብ በሀገሪቱ የተጀመረውን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለማፋጠን ይሠራል።

 

የኢትዮጵያን ሕዳሴ ዕውን ማድረግ

የኢትዮጵያን የልማት ውጥኖች ለማሳካት በየጊዜው በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚያዙ እቅዶች ጋር የተሳሰሩ ተግባራትን በማስተዋወቅ፣ አፈፃፀማቸውን በመከታተል የሀገሪቱን የህዳሴ ጉዞ ዳር ለማድረስ ኮርፖሬሽኑ ይተጋል፤ ጠንክሮ ይሰራል።

 

ትልልቅ ፕሮጀክቶች፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በመንገድ ልማት፣ በኃይል አቅርቦት፣ በትራንስፖርት፣ በኢንቨስትመንት፣ በአየር ትራንስፖርት፣ በገጠር መንገድ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ ግንባታ ወዘተ. እየተከታተሉ በሳቢ አቀራረብ ለውጥና ዕድገቱን ማስተጋባት የዴሞክራሲና የልማት ግንባታውን የሚመራው ልማታዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ አስተሳሰብ ልዕልና እንዲያገኝ ኮርፖሬሽኑ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ያከናውናል። በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዳሴ መረጋገጥ የተጣለውን መሰረት በፅኑ መሠረት ላይ ለመቆም በሚደረገው ጥረት ውስጥ ግንባር ቀደም የህትመት ሚዲያ ዘርፍ ብዙ ተቋም ሆኖ መውጣት አለበት።

 

 

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልዕክት

 

                  የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት  አቶ ሰብስቤ ከበደ

 

በአገራችን ዲሞክራሲን ህያው በማድረግ ፈጣንና ዘላቂ ልማት ለማረጋገት እንዲቻል ወቅታዊና አስተማማኝ መረጃዎችን መሰብሰብ መቀመርና ማስተላለፍ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ቀዳሚ ተግባር ነው፡፡

ድርጅታችን የመረጃ ተደራሽነቱን በላቀ ደረጃ በማረጋገጥ ልማታዊ አስተሳሰብ ታጥቆ የአገሪቱን ፖሊሲዎች ስትራቴጂዎች የዕድገትና የልማት ዕቅዶችን በባለቤትነት የሚፈጽም ዜጋ ለማፍራት ተግቶ ይሰራል ፡፡

በአገር ገጽታ ግንባታና ብሄራዊ መግባባት ስራ ውስጥ አጋዥ የሆነ ህብረተሰብ ከመፍጠር አኳያ በህትመት ውጤቶች የሚከናውናቸው ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የአገልግሎት አሰጣጡን ማዘመንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት ጊዜ የማይሰጠው የድርጅቱ ሃላፊነት በመሆኑ ከመደበኛ የድርጅቱ ዕቅድ በተጨማሪ በየዓመቱ የለውጥና የመልካም አስተዳደር ዕቅድ እየነደፈ ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሄ እየሰጠ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ወቅታዊና አስተማማኝ መረጃ ከመስጠት በተጨማሪ የማስታወቂያ አገልግሎት ስራው ቀልጣፋ ፈጣንና ውጤታማ እንዲሆን የማስታወቂያ ፖሊስ አዘጋጅቶ የደንበኞቹን እርካታ እየመዘነ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ሲሆን ዜጎች በማንኛውም ተቋማት ፈጣን ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት እንዲያገኙ መንግስት ያለውን ቁርጠኛ አቋም በመከተልና ፈላጊዎች መብታቸውን አውቀው ቀልጣፋ አገልግሎት የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት ይህን የዜጎች ቻርተር አዘጋጅቷል፡፡

በዚህ ዜጎች ቻርተር በአገልግሎት አሰጣጣችን ቅንነትና ታማኝነትን ለማስፈን የተለያዩ የለውጥ መሳሪያዎችን ተግባራዊ በማድረግ በተለይም የአገልግሎት አሰጣጥ ሰርዓታችንን ማሻሻል ያስችላሉ ያልናቸውን መንገዶች ሁሉ ሰራተኞቻችን ለዚህ ቻርተር አተገባበር ዝግጁ አድርገናል፡፡

ይህም ሆኖ አንዳንድ እንከኖች ይጠፋሉ ተብሎ ስለማይገመት አገልግሎት ተቀባዮቻችን የሚሰቱን አስተያየት መስታወታችን ስለሆነ አስተያየት ከመስጠት እንዳይቆጠቡ አደራ ጭምር እጠይቃለሁ፡፡

                                                                  አመሰግናለሁ

 

 

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አገልግሎት

አሰጣጥ ቻርተር /የዜጎች ቻርተር/

 

መግቢያ

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአዋጅ ቁጥር 113/1987 እና በአዋጅ ቁጥር 75/1989/ እንደተሻሻለው / የህዝብ የህትመት ሚዲያ ሆኖ የተቋቋመና ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነ ተቋም ሲሆን፣ አገሪቱ ከድህነት ለመውጣትና መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ በምታደርገው ሁለንተናዊ ጥረት ውስጥ የህብረተሰቡን ንቁ ተሳትፎ የሚያጎለብቱ፣ አገራዊ ገጽታን የሚያጎሉና የህዳሴ አስተሳሰብን ለማስረጽ የሚረዱ ፈጣን፣ ወቅታዊ፣ ሚዛናዊና ተዓማናኒት ያላቸው መረጃዎችን በተለያዩ ቋንቋዎች የማሰራጨት ተልዕኮ አንግቦ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡

ድርጅቱ በአዋጅ የተሰጠውን ተልዕኮና ተግባር በለውጥ ማዕቀፍ ውስጥ ገብቶና የተለያዩ የአሰራርና አደረጃጀት ስርዓቶችን ዘርግቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡በቀጣይም የተጀመረው የለውጥ ሂደት ስር እየሰደደ እንዲሄድና የበለጠ እንዲጠናከር እንዲሁም የአልገሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ይህ ቻርተር አዘጋጅቶ ወደ ተጨባጭ ስራ መግባት አስፈላጊና ወቅቱ የሚጠይቀው የአሰራር ስርዓት ሆኖ በመገኘቱ ይህ የዜጎች ቻርተር ተዘጋጅቷል፡፡

 

 

 1. የቻርተሩ ዓላማ
 • የዜጎችን/የደንበኞችን/ መረጃ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ፣
 • ለዜጎች ወቅቱን የጠበቀ ፣ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት፣
 • የግልጽነትና ተጠያቂነት መርህን ለማስፈን /ለማክበር፣
 • ዜጎች ከድርጅቱ ምን አይነት አገልግሎት በምን የጥራት ደረጃና ፍጥነት ማግኘት እንደሚችሉ ለማሳወቅ
 • ዜጎች በድርጅቱ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የባለቤትነት ስሜት ተሰምቷቸው ግብዓት የሚሆኑ አስተያየቶችና ጥቆማ የሚሰጡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት

 

 1. የተቋሙ ራዕይ

በ2020 ዓ.ም ወቅታዊና ሚዛናዊ መረጃ በማስተላለፍ በሀገር ውስጥና በአፍሪካ ተመራጭ  የህትመት ሚዲያ ሆኖ ማየት፡፡

 

 1. የተቋሙ ተልዕኮ

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትክክለኛ ሚዛናዊ ዘገባዎችና አመለካከቶችን የሚያንጸባርቅ በተለያዩ ቋንቋ የሚሰራጭ ተዓማኒ ሚዲያ በመገንባት በልማት፣ በዲሞክራሲና በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ህብረተሰቡ የተጋ ተሳትፎ እንዲያደርግ የሚያግዝ ተወዳጅ ሚዲያ መሆን ነው፡፡

 

 1. የተቋሙ ዕሴቶች

ለተልዕኳችን ስኬት እንሰራለን

 • ፈጣን፣ወቅታዊ፣ተዓማኒና ሚዛናዊ መረጃ ማሰራጨት መለያችን ነው፡፡
 • ለተገልጋይ እርካታ እንተጋለን፣
 • ለህትመት ሚዲያ ዘርፉ ተጠቃሽ ለመሆን እንሰራለን፣
 • ሙያዊ ብቃት፣ውጤታማ ክንውን፣
 • ለአዳዲስ ሀሳቦችና ለውጦቸ ዝግጁ ነን፣
 • የዜጎች ገንቢ አስተያየት ለተቋማችን ለውጥ ወሳኝ መሆኑን እንገነዘባለን፣

 

 1. አጠቃላይ የአገልግሎት ጥራት መርሆች
 • ለዜጎች /ለደንበኞች / ደንብና መመሪያና መሰረት ያደረገ አገልግሎት በቅልጥፍና መስጠት፣
 • ድርጅቱ ላስቀመጣቸው እሴቶች ተገዢ መሆን፣
 • ሁሌም ለጥራት መትጋት፣
 • ለተገልጋይ አገልግሎት አሰጣጥ በግልጽነትና ተጠያቂነት መርህ መከናወን፣
 • ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት፣

 

 1. የድርጅቱ ተገልጋዮችና ባለድርሻ አካላት
 • የተወካዮች ምክር ቤት
 • መንግስት
 • ዜጎች

የክልል መንግስታት

 • የመንግስት የልማት ድርጅቶች
 • መንግስታዊ ያልሆኑ ደርጅቶች
 • የሃይማኖት ተቋማት
 • የግል ድርጅቶች
 • የሲቪክ ማህበራት
 • አሳታሚ ድርጅቶች
 • የአገር ውስጥ ሚዲያዎች
 • የፖለቲካ ድርጅቶች
 • የህትመት ስርጭት ወኪሎች
 • ባለሀብቶች

 

 1. የአገልግሎታችን ተጠቃሚዎች መብቶች
 • ስለ አገልግልት አሰጣጣችን በቂ መረጃ የማግኘት
 • ስነ ምግባር የተላበሰ ፈጣን አገልግሎት የማግኘት
 • በአገልግሎት አሰጣጣችን ቅሬታ ሲኖር ለሚመለከታቸው አካላት በአግባቡ የማሳወቅና ፍትሀዊና ፈጣን ምላሽ የማግኘት
 • ስል አገልግሎት አሰጣጣችን አስተያየትና ግብዓት የመስጠት
 • የተቋሙን የእቅድና አፈጻጻም መረጃ የማግኘት

 

 1. በድርጅቱ የሚሰጡ አገልግሎቶች
 • የማስታወቂያ አገልግሎት
 • የህትመት ውጤቶች ስርጭት /ሽያጭ
 • የመንግስት መ/ቤቶችና ሌሎች ድርጅቶች የዜና ሽፋን ጥያቄና ቅበላ በጋዜጦቻችን ለዜጎች ታስቦ በተዘጋጀው ነጻ የአስተያየት መስጫ አምድ ላይ የሚሰት አገልግሎት
 • የፎቶግራፍ መረጃ አገልግሎት

 

 1. ለተገልጋዮች የምንገባው ቃል
 • የተገልጋዮቻችንን ፍላጎት ለማርካት እንሰራለን፣
 • አገልግሎታችንን ፈልገው ወደ እኛ ሲመጡ በቻርተሩ ባስቀመጥነው የአገልግሎት አሰጣጥ መሰረት ልናገለግሎት ቃል እንገባለን፣
 • ግልጽነትና ተጠያቂነት የተሞላበት አገልግሎት እንሰጣለን፣
 • ሁሉም ቀልጣፋ፣ፍትሃዊና ያለ አድልዎ አገልግሎት ለመስጠት እንትራለን፣
 • ለምንሰጠው አገልግሎት ሃላፊነት እንወስዳለን፣

 

 1. ዜጎች/ለተገልጋዮች አስተያየትና ቅሬታ የሚሰጡበት አግባብ

ለምንሰጠው አገልግሎት ጥራት መሻሻል የእናንተ ገንቢ አስተያየትና ግብዓት ወሳኝ በመሆኑ ተገልጋዮቻችን ለሚሰጡን አስተያየት ከፍተኛ ዋጋ እንሰጣለን፡፡ ግንኙነታችንን የበለጠ ለማጠናከርም የናንተን አስተያየት መሰረት አድርገን ያገልግሎት አሰጣጣችንን በየአመቱ እንከልሳለን፡፡

 

 1. ከተገልጋዮች አስተያየትና ቅሬታ የምንቀበለው በሚከተሉት ዘዴ ነው፡-
 • ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀው አስተያየት መስጫ መዝገብ
 • በአስተያየት መስጫ ሳጥን
 • በደብዳቤ
 • በአካል
 • በድርጅቱ ዌብሳይት
 • በኢሜይል
 • በስልክ
 • በቴሌ ፋከስ
 • በፖስታ

 

 1. የዜጎች የቅሬታ አቀራረብና አፈታት

በቻርተሩ በተቀመጠው መሰረት አገልግሎት ያላገኘ ዜጋ ቅሬታ የማቅረብ መብት አለው፡፡ በቅሬታው አቀራረብና አፈታት ስርዓቱም በሚከተለው አግባብ ይሆናል፡፡

 • ድርጅቱ በሚሸጣቸው ምርቶችና አገልግሎቶች ቅሬታ የተሰማው ዜጋ ቅሬታውን በቀጥታ አገልግሎት ለሰጠው ፈጻሚ በቃል፣ በጽሁፍ፣ በስልክ፣ በፋክስና ኢሜይል መግለጽ ይችላል፣
 • ቅሬታው የቀረበለት ፈጻሚም ቅሬታውን አጣርቶ ለቅሬታ አቅራቢው ተገቢውን ምላሽ መስጠት አለበት፣
 • በተሰጠው ምላሽ ያልረካ ባለጉዳይ ቀጥሎ ላለው የቅርብ ኃላፊ ቅሬታው እንዲፈታ ማቅረብ ይችላል፣
 • በዚህ ሁኔታ ቅሬታ የቀረበለት የቅርብ የሥራ ሃላፊ ቅሬታውን አጣርቶ ወዲያውኑ ምላሽ መስጠት አለበት፣
 • በሥራ ክፍሉ ሃላፊ ምላሽ ያልረካ ተገልጋይ ቅሬታውን ለቅሬታ ዴስክ ባለሙያ ማቅረብ ይችላል፡፡የቅሬታ ዴስክ ባለሙያውም ቅሬታውን በማጣራትአፋጣኝ ምላሽ ይሰጣል፡፡
 • በቅሬታ ዴስክ ባለሙያው ውሳኔ ያልረካ ተገልጋይ ቅሬታውን ለድርጅቱ የበላይ ኃላፊ ማቅረብ ይችላል፣ የበላይ ኃላፊውም ቅሬታው እንዲጣራ በማድረግ አፋጣኝ መልስ ይሰጣል፡፡
 • በመጨረሻ ተገልጋዩ እነዚህን ደረጃዎች ሁሉ አልፎ በተሰጠው ውሳኔ ካልረካ ለሚመለከተው አካል የማቅረብ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡

 

 1. ቻርተሩን በማስፈጸም ሂደት የድርጅቱ የክትትልና ግምገማ ስርዓት
 • የድርጅቱ የበላይ አመራርና በየደረጃው ያለ መካከለኛ አመራር በቻርተሩ ላይ በተቀመጠው አግባብ ተገልጋዮች አገልግሎት ማግኘታቸውን ያረጋግጣል፣
 • በየደረጃው ያለ አመራርና ፈፃሚ ድርጅቱ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች መፈጸማቸውን በየሳምንቱ በለውጥ ሰራዊት አግባብ ይገመግማሉ፡፡ በየወሩም የተጠናከረ ሪፖርት ለድርጅቱ የበላይ አመራር ያቀርባሉ፣
 • የተቋሙ የበላይ አመራር በየወቅቱ በሚቀርቡት የክትትልና የግምገማ ሪፖርቶች ላይ በመመስረት የእርምትና የማስተካከያ እርምጃ ይወስዳል፡፡
 • የድርጅቱ የበላይ አመራር የቅሬታ ማስተናገጃ ስርዓት ይዘረጋል፣ በአግባቡ ይከታተላል፡፡

 

 

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002829489
TodayToday1119
YesterdayYesterday1980
This_WeekThis_Week7209
This_MonthThis_Month29669
All_DaysAll_Days2829489

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።